ጽዮን ሆይ ክበቢኝ!
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ኅዳር ፳፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ያለ በጎ ምግባር ገነት ካልገባን
ጽድቅና መንግሥቱን ርስቱን ካልወረስን፣
የገባልሽ ኪዳን የሰጠሽ መሐላ
ከንቱ ነበረ ወይ የጨረቃ ጥላ?
በሥራችን ቢሆን የጽድቃችን መጠን
ገሃነም ጨለማው በርባኖስ ባልበቃን፡፡
እኛ ስለ በደልን ኃጢአት ስለ በዛ
ለርኵሳን ሐሳቦች ሰው ስለ ተገዛ፣
አይልክብን መቅሠፍት አይሰድብን ደዌ
ብዬ እንደተቀመጥሁ በአልዕሎ ልባዌ፣
ትዝ አለኝ ገሞራ ትዝ አለኝ ነነዌ፡፡
በነቢይ ስብከት በመላእክት ጥሪ
ተነግሮ ተመክሮ በዐዋጅ በነጋሪ
ልቡ ቢደነድን ሰዶም ባይመለስ
እሳት ሲበላቸው ግንቡ ሲፈራርስ
ጨው ሆነው ሲቀሩ ትእዛዙን የናቁ
የሺህ ዓመት ጥበቦች በዓይን ጥቅሻ ሲያልቁ
የምሕረትህ መርከብ የት ነበር መልህቁ?
ደብረ ዘይት ሆነህ ብፁዓንን ስትሰብክ
ወደ ሀገረ ሎጥ መላእክትን ስትልክ
እኔ በዚያ ነበርኩ በሰሊሆም ሥፍራ
ድውያን ስትፈውስ ዕውር ስታበራ
ፋሬስ ሲፈትንህ መንክራት ስትሠራ
ያን ሁሉ አይቻለሁ የእጅህን ተአምራት
ሁሉን አውቀዋለሁ የቃልህን ትምህርት፡፡
ሕይወት ግን የለኝም በሞትክልኝ መጠን
ምክንያት አታገኝም ለይቅርታ የሚሆን፡፡
እንደ አለላ ቢሆን የነፍሴ ቅላቷ
ደግሞም ጠቁሮ ብታይ የበፊት ንጣቷ
ከነዓን ና ስባል ተሰሎንቄ ብገኝ
ትዘነጋኛለህ ልብህ ተቀይሞኝ?
ጻድቃን ቅዱሳንን በበጎ ግብራቸው
ምሕረት ቸርነትህን ሕይወት ስትሰጣቸው
ምግባር የጎደለኝ የሰፈርኩ ከመሀል
እኔን ስትምረኝ መሐሪ ይሉሀል፡፡
ያለ በጎ ምግባር ገነት ካልገባን
ጽድቅና መንግሥቱን ርስቱን ካልወረስን
የገባልሽ ኪዳን የሰጠሽ መሐላ
ከንቱ ነበረ ወይ የጨረቃ ጥላ?
ስምሽን ፍለጋ በነሐሴ ጭቃ በቁርና ዝናብ
ተኝቼ ሳልምሽ ቆሜ ሳነበንብ
በታኅሣሥ ብርድ መሀል ማኅሌትሽን ቁሜ
ዝናብ ሳያግደኝ ጸሎትሽኝ ታድሜ
ንዒ ስልሽ ሌሊት በሠርክሽ ሳነባ
መዓዛሽን ስስብ እንደ አደይ አበባ
የተማርኩት ስምሽ አይደለም ለሹመት አይደለም ለካባ
ማርያም ሲባል ብቻ ልቤ የሚንቀጠቀጥ
በፍቅርሽ መዓዛ መንፈሴ የሚመሰጥ
ከቅዳሴው ሁሉ “ጐሥዓ” የሚበልጥብኝ
እመ ብርሃን ስልሽ ዕንባ ዕንባ የሚለኝ
አዘክሪ ድንግል የልጅ ዓይኔን ናፍቆት
በውድቀቴ መሀል መነሣቴን ሥሪያት
በአንዲት ዘማዊት ዓይን ግብሬ ቢልከሰከስ
ሥጋዬ ቢበላሽ ክህነቴ ብትፈርስ
ትተይኛለሽ ወይ እንዳልፈላ ጥንስስ?
የምግባሬ መጠጥ እየፈሰሰ ቢያልቅ
እንዳልነበር ሆኜ መውደቅንም ብወድቅ
ትተይኛለሽ ወይ ሲኦል እንድማቅቅ?
ያለ በጎ ምግባር ገነት ካልገባን
ጽድቅና መንግሥቱን ርስቱን ካልወረስን
የገባልሽ ኪዳን የሰጠሽ መሐላ
ከንቱ ነበረ ወይ የጨረቃ ጥላ?
በአጋንንት ፍላጻ ነፍሴ ብትወጋ
ምልጃሽ ነው ተስፋዬ ከጥላሽ ልጠጋ፡፡
ጽዮን ሆይ ክበቢኝ ለውዳሴሽ ልትጋ
የኃጢአት ጎዳናዬ መንገዴ ይዘጋ!