ወዮልኝ!
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ጥቅምት ፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
በኃጢአት ተፀንሼ በዐመፃ ተወልጄ
ከቃልህ ሕግ ወጥቼ በዝንጉዎች ምክር ሄጄ
በኃጢአተኞች መንገድ ቆሜ በዋዘኞች ወንበር ተቀምጬ
በውኃ ማዕበል ሰጥሜ የሞት ጽዋን ጨልጬ
ጥርሴ ጦር ፍላፃ ቁጣዬ እንደ እባብ መርዝ አንደበቴ ምላጭ ሾተል
ልቤ በክፋት ቀንቅኖ ውስጤ በበደል ነቅዞ ሰውነቴ ሁሉ ጎብጧል
ወዮልኝ!
- በሰውነቴ መደርጀት በቀስቴ ታምኛለሁ
ለእግሮቼ ወጥመድን ለሕይወቴ ጉድጓድን ቆፍሬያለሁ
ወዮልኝ! - እንደ ገደል ላይ ሣር ሳይነቀል እንደሚደርቅ እቅፍ እንደማይሞላ
ኃጢአቴ ሚዛን ደፍቶ በምግባሬ ቀልያለሁ ስለወጣሁ ከጥበቃህ ከለላ
በወይን ጠጄ ላይ መርዝ ደባልቄ ወርቅ እና ብሬን አዝጌ
ከኃጢአቴ የተነሣ አንገቴን የብረት ጅማት ግንባሬን ናስ አድርጌ
ወዮልኝ! - በጭንጫ መሬቴ ላይ ዘርህን ዘርቼ
የሠርግ ልብሴን ሳልለብስ ከሠርግህ ቤት ገብቼ
የሰጠኸኝን አንድ መክሊት በመሬት ውስጥ ቀብሬ
የጽድቅ እና የዕውቀት መክፈቻን በጨለማ ውስጥ ሠውሬ - ወዮልኝ!
መንግሥተ ሰማያትን በሰዎች ፊት ስዘጋ
የልብሴን ዘርፍ አስረዝሜ አሸንክታቤን ስዘረጋ
የነቢያትን መቃብር ስሠራ የጻድቃንን መቃብር ሳስጌጥ
ትንኝን ሳጠራ ግመልን እንዳለ ስውጥ
በምኩራብ ፊተኛ ወንበር በማዕድ በክብር ስፍራ ስቀመጥ
ወዮልኝ!
- የእናት አባቴን መስፈሪያ አቁማዳ ስሞላ
የመበለቶችን ጥሪት ንብረት ገንዘባቸውን ስበላ
ከአዝሙድ እና ከእንስላል ዐሥራትህን ሳወጣ
መምህር ሆይ! እየተባልኩ ወደ ገበያ ስወጣ
የሙታንን አጥንት ተሞልቶ እንደ ተለሰነ መቃብር
ውስጤ ዐመፅ እና ቅሚያ አቤት ውጭዬ ግን ሲያምር
ወዮልኝ! ወዮልኝ!
- በሥራዬ ተቆጥቶ ከመንበረ ሥልጣኑ ወርዶ እረኛዬ ይጠራኛል
አዳም ሆይ ወዴት አለህ ከትእዛዜ ወጥተህ ከበለሷ ቀጥፈሃል
በኃጢአት ውስጥ ተሸሽገህ የበደልን ቅጠል አገልድመሃል
ፍሬን ፈልጌ ስመጣ እሾህን አብቅለሃል፤ ኩርንችትን አፍርተሃል
ወደ ዕረፍት ውኃ መርቼ በለመለመ መስክ ባሰማራህ እረኝነቴን ንቀሃል
በዓለም ፍቅር ተነድፈህ ቀራንዮን ረስተሃል፤ ከመንጋው ወጥተህ ሄደሃል
ጻፎች እና ፈሪሳውያንን መስለህ እንደ ይሁዳ ከድተኸኝ በሥራቸው ተባብረሃል
ስለዚህ ና! ወደ እኔ ከበረቱ ተቀላቀል ከመንጋው ጋር ይሻልሃል
እያለ እረኛዬ ይጠራኛል፤
ወዮልኝ…! ወዮልኝ…!
- እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ብመለስ ነበር ለእኔስ የሚሻለኝ
የራስህ ላይ አክሊል ወድቆ ሕጌ ከልቡናህ ከስሎ ደርቆ
ስምህ ከሕይወት መጽሐፍ ተደምስሶ ከመዝገቤ ተፍቆ
ና ወደ መንጋው! ና ወደ እኔ! እያለ ይጠራኛል፤ ለካስ ይወደኛል
ዘጠና ዘጠኙን በዱር ትቶ “አዳም ሆይ ወዴት አለህ?” እያለ ደጋግሞ ይጠራኛል
“ከእንቅልፌ እንድነቃ ውዴ ሆይ ክፈትልኝ!” እያለ ደጄን ከውጭ ቆሞ ይመታል
ወዮልኝ…! ወዮልኝ…! ወዮልኝ…!
እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ብመለስ ነበር ለእኔስ የሚሻለኝ፡፡