መልካሟ ርግብ
ሐምሌ ፴፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ከቀለማት ሁሉ በላይ በሆነው፣ የፍጹምነት መገለጫ፣ ሰማያዊ ክብር በሚገለጽበት በጸአዳ ብሩኅነት ደምቃ፣ የንጽሕናን ሞገስ ተከናንባና አሸብርቃ በሰማይ ትበራለች፡፡ ከውልደቷ ጀምሮ የፈጠራት ይህን ሰማያዊ ጸጋ ሲያላብሳት እርሷም “አሜን” ብላ ተቀብላ ሰማያዊ መናን እየተመገበችና በሰማያት ሠራዊት እየተጠበቀች ከምድር ከፍ ከፍ ብላ መብረርን ለምዳ ከቤተ ሰቦቿ ተለየች፡፡
ያን ጊዜ ተረካቢዎቿ ግራ ቢገባቸው ፍጥረቷን አድንቀው ማረፊያዋን ያዘጋጁ ዘንድ ተማከሩ፤ ወደ ጌታዋም አመለከቱ፤ በተቀደሰችው ስፍራ በሠራዊቱ ከቦ ሊያኖራት ሲሻም የእርሱ ለሆኑት ፍቃዱን ገለጠላቸው፡፡ መልካሟ ርግብም ማረፊያዋን ወደደች፤ ዘወትርም በፍጹም ትሕትናና ፍቅር ለጌታዋ ተገዝታ ኖረች፤ እርሷ ባለችበት ሰላም ይሰፍናል፤ ፍቅር ይጎለብታል፡፡
የመፀነሻዋ ጊዜ ደረሰናም ከተቀደሰው ስፍራ ወጥታ በአዲስ ጠባቂ ተጠበቀች፤ ወልዳም ታቀፈች፤ ይህን ጊዜ ጠላት ሸምቆ መጣባት፤ ቤቷን አፍርሶ ልጇን ሊገልባት መምጣቱን ሰማያዊው ጠባቂው ቢነግራት አንዲያ ልጇን ይዛ ወደ ጫካ ኮበለለች፡፡ በዱር በጫካው ስትጓዝም ከእርሷ ይልቅ ለልጇ ትጨነቅ ነበር፤ አንዴ በእቅፏ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጀርባዋ አድርጋ ይዛው ከነፈች፡፡
በፍቅር በሚንገበገብ አንጀቷ በስስት ዓይኗ እያየችው፣ ሲርበው ቃርማ አምጥታ አብልታ፣ ሲጠማው ልጇ ከዐለት ውኃን እያፈለቀ ውኃን አጠጥታ፣ ሲበርደው ታቅፋ በሙቀቷ አሙቃ ስትንከባከበው ከረመች፡፡ መከራና ሥቃይ የበዛበት ጊዜም አለፈና መልካሟ ርግብ ልጇን ይዛ ወደ ሀገሯ ተመለሰች፡፡
በዚያም ፈተና ቢገጥማት በትሕትና፣ በፍቅርና በንጽሕና መኖርን አላስታጎለችም፡፡ ልጇ እያደገ ሲሄድ ግን ፍራቻ አደረባት፤ ወጥቶ ተለይቶ እንዳይጠፋ፣ ጠፍቶም እንዳይቀር፣ አልያም በጠላት እንዳይገደልባት ትከታተለው ጀመር፡፡ ሆኖም ግን ወደ የሚፈልግበት ስፍራ ከመሄድ ይዛ ማስቀረት አልተቻላትም፤ እንደ ጌታዋ እርሱ በፈቃዱ ሁሉን ያደርጋል፤ እናት ናትና ግን በቅርብ ክትትል ትመለከተዋለች፤ ትንከባከበዋለች፤ ከሄደበትም ሲመለስ በፍቅር ተቀብላ ታኖረዋለች።
በክብር ላደገው ሙሽራ ልጇ መልካሟ ርግብ ያልከፈለችው መሥዋዕት የለም፤ እርሱ ሲያዝን በኅዘን ውስጧ እየተቃጠለ መሪር እንባን ስታነባ፣ አሳዳጆቹ መከራ ሲያበዙበት ጎንበስ ቀና እያለች ስትንገላታ ከርማ አብራው ኖራለች፡፡
የጠላቶቹ ቅናትና ምቀኝነት አቅሉን ባጣ ጊዜም ሤራ ያሴሩ ዘንድ አበሩ፤ ከፉ፤ ስለዚህም መከራን አመጡበት፤ በየሄደበት እያሳደዱም ሊጥሉት ይሞክሩ ጀመር፤ ማሸነፍ ባለመቻላቸውም ሊገድሉት ተማከሩ፤ ይህችን ቀን ስትፈራት የኖረችው መልካሟ ርግብ ነበረች፤ ሆኖም እርሱ ሞቱን ይጠብቅ ነበር፡፡
ሙሽራው ጊዜው ሲደርስ ቤቱ ይገባ ዘንድ የተገባ በመሆኑ እናቱን ለጊዜውም ቢሆን መለየት ግድ ሆነ፡፡ ጥላቻቸውን መደበቅ እስኪያቅታቸው የከፉበት ጠላቶቹም ሤራቸው ተሳክቶ ያዙት፤ እንደ እስረኛም አስረው አንገለታቱት፤ ተባብረው እጅጉን አሠቃዩት፤ እርሱ ግን ያለ በደሉ ሲወቅሱት፣ ሲወነጅሉትና ሲያሠቃዩት ዝምታን መረጠ፤ መከራንም በፍቅር ተቀበለ፡፡
ይህን ያየቸው መልካሟ ርግብ የእናትነት አንጀቷ ተንሰፈሰ፤ በየመንገዱ እየተከተለች እንባዋን አፈሰሰች፤ ከመሬት እየወደቀችና እየተነሣች ኅዘኗን አበዛች፤ ልጇ ሞተ ያሏት ሰዓት ግን መቋቋም የማትችለው ዓይነት ሆነባት፤ ለሦሰት ቀናትም እንዲሁ መብልና መጠጥ ሳትቀምስ ቆየች፡፡
በሦስተኛው ቀን ግን ልጇ ሲነሣ የእርሷ ደስታ እጥፍ ድርብ ሆነ፤ ዓይኑን በዓይኗ ልታየው በቃችና ልቧ ደስታን ተሞላ፡፡
ዳግመኛም ኅዘን ገጠማት፤ ተነሥቶ ከእርሷ ጋር አልቆየም፤ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎ በዚያው መኖሪያውን አደረገ፤ መልካሟ ርግብ ተለይታው ቀረች፤ ዘወትርም እርሱ ያለበት የምሄድበትን ቀን ታስብና ትጠብቅ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ልጇን በሕልም አየችው፤ ያለበትን ድንቅ ዓለምም አሳያት፤ ወደ እርሱም እንደሚወስዳት ቃል ገብቶላት ዳግም ተለያት፡፡
መልካሟ ርግብ ዕድላል ፈንታዋ በመሆኑ በሁሉ ዘንድ ለከበረ ልጇ እናት ሆናለች፡፡ እርሱ አስተማሪ ነውና፤ እርሱ ፈዋሽ ነውና፤ እርሱ መድኃኒት ነውና፤ እርሱ ቤዛ ነውና፤ እርሱ የዓለም ንጉሥ ነውናም እርሷ ንግሥት ሆነች፡፡
ቀኑም ደረሰና ልጇ መጥቶ እንደምትሞት ነገራት፤ መልካሟ ርግብ ሞትን ስትሰማ “ለምን?” ብላ ጠየቀች፡፡ እርሱም ሞቷ የከበረ እንደሆነ ቢነገራት አንዴ አይደለም ሰባቴ መሞትን ተመኘች፡፡ በከበረች ዕለትም ዕረፍቷ ሆነ፤ በዚህም ሳያባቃ እንደ ልጇ ተነሥታ በሰማያዊያኑ ሠራዊቶች ተክብባ ወደ ሰማየ ሰማያት በረረች፤ መጠቀች፤ ከልጇ ተገናኘች፤ ፍጹም ሐሴትንም አደረገች!
ጠቢቡ «ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት፥ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሷት፥ ንገሥታትና ቊባቶችም አመሰገኗት» በማለት ያመሰገነሽ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ እኛም እናመሰግንሻለን! (መኃ.፮፥፱)
ውዳሴና ምስጋና ለክብርት እመቤታችን!