የቀና ልብ
ሐምሌ ፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ድሮ ድሮ ልቡ ሲቀና ሕሊናውን መግዛት ተስኖት፣ አእምሮውን ወጥሮ ሲይዘው፣ ሐሳቡን መሰብሰብና አቅንቶ ማየት ያቅትውና ይጨነቅ ነበር፤ ቀጥተኛውን መንገድ ጠማማ፣ ከፍተኛውን ኮረብታ ዝቅተኛ፣ አባጣ ጎርባጣውን ምቹ አድርጎ ሲመለከት ለመልካም ነገር መወሰን ይሳነዋል፤ ፍቅር ግን ይህን ሁሉ ቀየረለት፤ በትዕቢት የታወረውን ዓይኑን አብርቶ፣ ትምክህቱንና ጭንቀቱን አጥፍቶ የውስጥ ዕረፍት ሰጥቶታልና፡፡
አሁንስ ልቡ ምን ይሆን የሚሰማው? ፍቅር ወይስ ጥላቻ? ሐሳቡስ ምንድን ነው? መልካም ወይስ ክፋት? በምሬት ይኖራል አልያስ በምስጋና? ለፍቅር የሞተው ግን ይህን አወቀ፤ ልብ ሲቀና ለፍቅር ሲል ይታዘዛልና፤ በጎውን እንጂ ክፉን አያስብም፤ መልካምም ይሆናል፤ አያማርርም፤ አይጠላም፤ በምስጋናም ይኖራል፤ ምንም እንኳን መከራና ሥቃይ ቢበዛበት ታግሦ ያልፋል እንጂ ጥላቻ አያድርበትም፡፡
የቀና ልብ ፍቅርን አወቀ፤ በእውነት ከሆነ ስሜት ወደደ፤ እስከ ሞት ቢያደርሰውም ለፍቅር ምንም ምን ዓይነት መከራን ተቀበለ፤ በፍጹም ልቡ በተለየ ሁኔታ አፈቀረ፤ ደስ በሚል ሥቃይ ውስጥም መኖርን መረጠ፤ ፍቅር ኃያል ነውና ልቡን አቀናው!
ከዚያም የቀና ልብ መከራ ሲያበዙበት ታገሠ፤ ሲዘልፉትና ሲሰድቡት በትሕትና በጎውን መለሰ፤ ሲጠሉት ወደደ፤ ሲረግሙት መረቀ፤ ክፋት ሲያደርጉበት መልካሙን አደረገ። ፍቅርን ያላወቁ ልቦች ሲጠሙ ክህደትን አብዝተው በቀና ልብ ላይ እክል የመሆናቸው ነገር ግን ያስከፋል! ልቦች ሁሉ ቀንተው በብሩህ ሕሊና፣ በበጎነት፣ በአንድነትና በኅብረት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ተስፋን፣ መልካሙን ነገር ሁሉ መቋደስ እንደሚቻል ማን በነገራቸው?
በሽሙጥና በንቀት የጎሪጥ በዓይነ ልቦናቸው እየተመለከቱ፣ ቅስም በሚሰብር ምላሳቸው ስሜት የሚጎዳ ንግግር እየተናገሩና እየጎዱ፣ ተስፋ አጥቶ ቀናነቱን እንዲጠላ ሌት ከቀን ሲዳክሩ የሚውሉት ጠማማ ልቦች በጎው ሁሉ የራቃቸው ሆኑ፤ የጠመመ ልብ ደስታንም አያውቅምና ያወቁ መስሏቸው እራሳቸውን አከፉ፡፡
ልብ ግን ፍቅርንም ይሁን ጥላቻን፣ በጎውንም ሆነ ክፉን፣ ደስታን አልያም ኅዘንን፣ ምሬትን ወይም ምስጋናን፣ ጭንቀትን እንዲሁም ዕረፍትን ሁሉ በውስጡ የሚይዝ ሲሆን መጠኑን ግን አሳንሶ መፍጠሩ ያስደንቃል! ባማረው ቅርጹና አካሉ ውድ የሆነውን የሕይወት እስትንፋስ መያዙ እንዲሁም ሌት ከቀን ያለ ዕረፍት ትርታው የመምታቱ ምሥጢር ብዙዎችን ማስገረሙ አይቀሬ ነው፡፡
የቀና ልብ ይህን ተረድቶ በአንድ ሕግ ታሠረ፤ ለኃያሉ ፍቅር ዘወትር ተንበረከከ፤ ተገዛም፤ በጉልበት አይደል በነጻነት፣ በማስመሰል ሳይሆን በእውነት፣ በፍጹም በጎነት እንጂ ከንቱ ውዳሴ ባልሆነ መውደድ ጌታውን አመለከ፤ በዚህ ጊዜ ንጹሕ ቅዱስ ሆነ፡፡
የቅድስና ጉዞውን እንደ ጀመረ ግን በመንገዱ ሁሉ መሰናክሎች ከፊቱ ተጋረጡበት፤ የተመቃኙ፣ የቀኑ እንዲሁም የከፉ ልቦች ተሰልፈው መጡበት፤ አንዱ በቀኝ፣ አንዱ በግራ፣ ሌላው ከፊት የመጨረሻውም ከኋላ ከበው መከራውን አጸኑ፡፡
ይህን ጊዜ ወደ ላይ ተመለከተ፤ የፈጠረውን አሰበ፤ ለመነ፤ ተማጸነም፤ ለፍቅር ሲል ለሞተው ጌታ ጥሪ አቀረበ፤ እንዲህ ሲል፤ “አቤቱ ጌታዬ ባሪያህን አስበው፤ አትተውም፡፡” ንጹሕ ቅዱስ ነውናም ጸሎቱ ደረሰ፤ በጌታ ፊት ተቀባይነትን አገኘ፤ ጠላቶቹን የሚያሸንፍበት ጥበብ በቅዱስ መንፈስ ተገለጠለት፤ ቅናታቸውንና ምቀኝነታቸውን በብልሃት፣ ጥላቻቸውን በፍቅር፣ ዘለፋ ስድባቸውን በትዕግሥት ማሸነፍ ቻለ፡፡
የሕይወት ውጣ ውረድ ሆነናም ለእንጀራው ሲዳክር ጠላቶቹ በሕልውናው መጡበት፤ ሠርቶ እንዳይበላ፣ ውሎ እንዳይገባ፣ መብል መጠጥ እንዳያገኝ ጋሬጣ ሆኑበት፡፡ በቀን አንዴም ይሁን ከቶም ሳይበላና ሳይጠጣ መዋል ማደርን ግን ጌታው አስተምሮታልና አላማረረም፡፡
የጠመሙት ልቦችም ሽንፈታቸው ገብቷቸው በሌላ መንገድ ሊያጠፉት መከሩ፤ ከምንም በላይ ሕይወቱን ሊያጠፉ ተስማሙ፡፡ መጥፎ ቅናታቸው ውስጣቸውን እያንገበገበ አላስቆም፣ አላስቀምጥ፣ አላስተኛ፣ አላስኖር ሲላቸው ዕረፍት ማግኘት ተሳናቸው፡፡
“ሆድና ግንባር አይደበቅም” እንዲሉ አባቶቻችን በግልጽ ፊት ለፊት ተገናኝተው፣ ጥላቻቸውንና ቅናታቸውን መደበቅ ተስኗቸው፣ እንደ ጠላት ተዋግተው ሊያጠፉት መጡበት፡፡ ጠላት፣ ፍቅር የማያውቁ፣ በጎነትና መልካሙን ሁሉ የሚጠሉ እነርሱ ሆነው ለፍቅር የቀናውን ልብ እንደ ጠላት መመልከታቸውና መውቀሳቸው ምን ይበላል? ድንቁርና ወይስ ትዕቢት?
የቀናው ልብ ግን አሁንም አልፈራም፤ በእምነቱም ጸና፤ ጌታው ለፍቅር መሞትን አስተምሮታልና፤ ልቡ ተንገብግባለታለችና የሥጋን ሞት ሳይፈራ በነፍሱ ድኅነት ወደ ፈጠረው ይሄድ ዘንድ ተቻኮለ፡፡
ጠላቶቹ ግን ይህን ባወቁ ጊዜ የባሰ ጠመሙ፤ ፈርቶና ተስፋ ቆርጦ እንዲክድና እንዲገዛላቸው የተለያዩ ማሠቃያ ዜዴዎችን ያሰሙት፣ ሥጋውን ቆራርጠው እንዳልነበረ የሚያደርጉ መሣሪያዎችን በዓይነት በዓይነት ያሳዩት ጀመረ፡፡ የቀና ልብ ግን የበለጠ ተደስቶ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ ለሥቃይም ተዘጋጀ፤ አምላኩን የሚያይበትንም ጊዜ ናፈቀ፡፡ ስለዚህም ተሠዋ፤ የጠላቶቹ ምክርና ሽንገላ እምነቱን ሳይለውጠው፣ ዛቻቸው ሐሳቡን ሳያስቀይረው፣ እንዲሁ ወደ ሰማየ ሰማያት ዓይኑን እንዳንጋጠጠ መከረውን ተቀብሎ ለፍቅር ሞተ!
ሎቱ ስብሐት!