መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን

ክፍል አራት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ጥር ፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ከዚህ ቀደም ከክፍል አንድ እስከ ክፍል ሦስት ድረስ ስለ መልካም አስተዳደር፣ የመልካም አስተዳደር እጦት  በቤተ ክርስቲያን እና ያስከተለው ጉዳት ወይም ተጽእኖ በጥቂቱ አስነብበናችኋል፡፡ በዚህ በመጨረሻው ክፍል አራት ደግሞ የመልካም አስተዳደር መስፈን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞችን  በከፊል ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ!

በቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ጥቅሙም ለአንድ ወገን ብቻ አይደለም፡፡  ለቤተ ክርስቲያን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለምእመናን፣ ለካህናት እንዲሁም ለሀገሪቱም ጭምር ነው፡፡

፬.፩. ለቤተ ክርስቲያን የሚኖረው ጥቅም፡-

  • ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንድትወጣ፣ አስተምህሯን ለመላው ዓለም ለማዳረስ፤
  • ሲኖዶሳዊ አንድነቷንና ቀኖና ቤተ ክርስተያንን ለማስጠበቅ፤
  • የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለማስቀረት፣
  • ሀብት ንብረቷን የሚቀራመቱ ዘራፊዎችን ለመቆጣጠር፣ ወንጌልን ለማስፋፈት. . . ወዘተ…

፬.፪.. ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚኖረው ጥቅም፡-

ቅዱስ ሲኖዶስ የመንግሥትንም ሆነ የሌላን አካል አጀንዳ ከመቀበልና በምእመናን ዘንድ ከመወቀስ ያድነዋል፡፡ ውሳኔው ተፈጻሚ እንዲሆንና በሌሎች ላይ በጎ ተጽእኖ የሚያሳድር፣ የታፈረና የተከበረ፣ ሁሉ የሚገዙለትና የሚታዘዙለት እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ አሉቧልታና ትችት የራቀ እንዲሆን፣ አንድነቱን አስጠብቆ ለመሄድ፣ ሥርዓት አልበኞችን ለመገሠጽ፣ ዓቅምና ድፍረት ያገኛል፡፡ በዚህም በቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ላይ የተሰጠውን አደራ በአግባቡ እንዲወጣ፣ ማዕድን ከማገልገል ይልቅ ለቃሉ እንዲተጋ ያደርገዋል፡፡ (ሐዋ. ፮፥፪)

፬.፫. ለካህናት የሚኖረው ጥቅም፡-

ካህናት የእግዚአብሔር ዐይኖች ናቸው፡፡ በምእመናን ላይ የተሾሙ የመንጋው ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ካህናት ማሰብ አይቻልም፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦትና የቅዱስ ሲኖዶስ ክብር፣ ልዕልና መጉደል ጉዳቱ ለካህናትም ነው፡፡ ምክንያቱም የተጠሩለት ክህነት መገኛ ካልተከበረ ሊከበሩ አይችሉምና፡፡

ቤተ ክርስቲያንም መልካም አስተዳደር ከሌላት በቅንነት፣ በትጋትና በፍጹም መንፈሳዊነት ሊያገለግሉ፣ መንጋውን ሊጠብቁ፣ ምድራዊና ሰማያዊ ዋጋቸውን ሊያገኙ አይችሉም፡፡ ክብራቸው፣ ሕይወታቸው፣ መታፈር፣ መከበራቸው ከቤተ ክርስቲያንና ከጉባኤው ውጭ የሚገኝ ስላልሆነ መልካም አስተዳደር ለካህናት ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡

በመልካም አስተዳደር እጦት ከሚጎዱት አካላት በዋናነት ካህናት ናቸው፡፡ ፍትሐዊ የሆነ የአገልግሎትና ተገቢ ክፍያ ባለ መኖሩ ቤተ ሰባቸውን ለመምራት፣ ልጆቻቸውን ለማስተማር የሚቸገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት በርካታ ካህናት ሥራ ለማግኘት ሲቸገሩም ይታያል፡፡ ስለዚህ መልካም አስተዳደርን በቤተ ክርስቲያን ማስፈን የበለጠ ካህናትን የሚጠቅም ስለ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

፬.፬. ለምእመናን የሚኖረው ጥቅም፡-

ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን የመኖር ምክንያት  ናቸው፡፡ ክርስቶስ በደሙ መፍሰስ፣ በሥጋው መቆረስ ሕይወትን፣ ልጅነትን ሰጥቶ፣ በመለኮታዊ፣ በመልአካዊና እና በሰዋዊ በካህናትና በነገሥታት ጥበቃ ያስጠበቃቸው ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር የሚገናኙባት፣ ተወልደው ልጅነትን ሞተው ትንሣኤን የሚያገኙባት፣ አዝነው የሚጽናኑባት፣ ታመው የሚፈወሱባት፣ በሞትም፥ በሕይወትም ቤታቸው ናት፡፡ ካህናትም ክህነታቸው፣ ጳጳሳትም ሹመታቸው ለመንጋው ጥበቃ ለምእመናን ደኀንነትና ድኅነት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን  አስተዳደር ችግር ሲቀረፍ፣ ሲኖዶሳዊ ክብር ሲጠበቅ ምእመናንንም ክብራቸው ይጠበቃል፡፡ አንድነታቸው ይጸናል፡፡ አገልግሎቱን በተሟላ መንገድ ያገኛሉ፡፡ በነፍስም በሥጋም ዕረፍትን ሰላምን ይጎናጸፋሉ፡፡

፬.፭ ለሀገር የሚኖረው ጥቅም፡-

መንግሥታት ሰላምን፣ ልማትንና ብልጽግናን በእውነት የሚሹ ቢሆን ቤተ ክርስቲያንን በደገፏት እንጂ ባልገፏት ነበር፡፡ በጣልቃ ገብነትም የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ባልሆኑ ነበር፡፡  ለምን ቢባል ሰላም ወዳድ፣ ሃይማኖተኛ፣ በምግባር የተገራ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ፣ ሀገሩን የሚወድ፣ አምራችና ጤናማ ዜጋ፣ አእምሮው የተሠራ ትውልድ የምታፈራ ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡ ከዚህ የተነሣ የመልካም አስተዳደር ችግሯ ከተፈታ፣ ለወንጌል አገልግሎት ከተፋጠነች፣ ትውልድ ግንባታ ላይ ካተኮረች፣ ሀገርም፥ መንግሥትም ይጠቀማሉ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ሲከበር አባቶቹን የሚያከብር፣ ለቃላቸው ተገዥ ሆነ፤ በፈቃዳቸው የሚያድር፣ የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ የሚሰማ፣ በመቻቻል፣ በአብሮነትና በመረዳዳት የሚያምን፣ ለሀገሩ ለወገኑ ክብር የሚሞት ማኀበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ መልካም አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን መስፈኑ ሀገራዊ ፋይዳው ትልቅ ነው፡፡

ማጠቃለያ፡-

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! ዓሣ ከባሕሩ ወጥቶ መኖር አይችልም፡፡ በሕይወት ለመኖር የግድ ባሕሩ አስፈላጊው ነው፡፡ እኛም በሕይወት እንኖር ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖር ግዴታችን ነው፡፡ የሕይወት መገኛና ማግኛዋ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ሕይወት ቃሉ ነው፤ ሕይወት ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነው፤ ሕይወት በጥቅሉ እግዚአብሔር ነው፡፡

ሕይወት የሚሰጠውን ቃሉንም፣ ሥጋውንና ደሙንም ማግኘት የሚቻለው በቤቱ በመኖር ነው፡፡ ዓሣውን ከባሕር አውጥተው ሊበሉት ብዙ ዓሣ አጥማጆች መረባቸውን እንደሚጥሉ ሁሉ እኛንም ባሕረ ጥበባት ከሆነች ቤተ ክርስቲያን ሊያስወጡን ብዙ መረብ ጣይ ጠላቶች አሉን፡፡ ጠላት እኛን ለማጥመድ እንደ መረብ ከሚጠቀማቸው ስልቶች አንዱ የቤተ ክርስቲያንን የመልካም አስተዳደር እጦት እያነሣ፣ ምግባረ ብልሹ አገልጋዮችን እየጠቀሰ፣ ቤተ ክርስቲያንንና የቤተ ክርስቲያንን ሰዎች እያደባለቀ በስሜት በመኮርኮር፣ ብዙዎችን ከባሕሩ አስወጥቶ ሕይወት አልባ ወደ ሆነው ዓለም ወስዷቸዋል፡፡

እግዚአብሐርን ያህል ጌታ፣ ቤተ ክርስቲያንን ያህል ቦታ አሳጥቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖናዋ ፍጹም ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጡ ግን ሥጋዊ፥ ደማዊ ሰው የሚመራው እንደ መሆኑ ፍጹም አይደለም፡፡ ከላይ ስንዘረዝር የነበረውም የመልካም አስተዳደር እጦት ከዚሁ የሚመነጭ ነውና ለይተን ማሰብ አለብን፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦትን ሰበብ አድርገን ከቤተ ክርስቲያን መውጣት ቀርቶ፣ ርቆ መቆም በራሱ ትክክል አይደለም፡፡

አንድ አስተዋይ ሰው የቱንም ያህል ጎዶሎው ቢበዛ ከቤቱ የትም ሊሄድ እንደማይችል ሁሉ እኛም ከቤተ ክርስቲያን የትም ልንሄድ አንችልም፡፡ ‹‹ካንተ ወደ ማን  እንሄዳለን?  አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ›› እንዳሉ ሐዋርያት፡፡ የአስተዳደር ችግርን የሚፈጥረው ሰው ነው፤ (ዮሐ.፮፥፷፰) የሚያስተካክለውም ሰው ነው፡፡ ለብልሽቱም ድርሻ አለን፤ ለመፍትሔውም ባለቤቶች ነን፡፡

ስለዚህ የመልካም አስተዳደር ችግር የማይነሣባት፣ እንደ ጥንቱ ገንዘብን የተጠየፉ፣ ለአገልግሎት የማይታክቱ፣ የተጠሩበትን ዓላማ የማይዘነጉ፣ ዕለት ዕለት የአብያተ ክርስቲያነት ሁሉ ሐሳብ የሚከብድባቸው (፪ቆሮ.፲፩፥፳፰) አገልጋዮች ለክብሯ ዘብ፣ ለህልውናዋ አጥር የሚሆኑ ምእመናን፣ ባሕረ ጥበባት፣ ስንዱ እመቤት ከሆነች ቤተ ክርስቲያን እየወጡ የሚጠፉ ምእመናንና አገልጋዮች ጭምር አንዳይኖሩ እገሌ ወእገሊት ሳንባባል በጋራ መትጋት፣ አብዝቶ መሥራት የሁላችንም ግዴታ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል፡፡

እያንዳንዱ ሰው የእኔ የሚለው ቢኖርበት እንጂ የማይጸድቅበትን ጊዜያዊ ቤቱን እንኳን ከውጭ ወራሪ፣ ከውስጥ ሰርሳሪ ተግቶ እንደሚጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ግዴታ ለካህናት ወይም ለጳጳሳት ወይም ለተወሰነ የማኀበረ ሰብ ክፍል የሚተው አለመሆኑን እና “ያገባኛል” የማለት እሳቤን ማሳደግ ይገባናል፡፡ ያን ጊዜ አብረን መንግሥቱን እንወርሳለን፡፡ ከዚህ ውጭ ለእኛ የሚበጀን ሌላ መንገድ የለምና፡፡

‹‹ጌታ ሆይ፥ ካንተ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ!!!››

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!