‹‹በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ›› (ማቴ.፫፥፲፫)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥር ፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ! እንኳን አደረሳችሁ! የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል እንዴት አለፈ? ልጆች! አሁን ያላችሁበት ወቅት የዓመቱ አጋማሽ የፈተና ወቅት ነው! ፈተናውን በደንብ አድርጋችሁ መሥራት አለባችሁ! መቼም በርተታችሁ ስታጠኑና ያልገባችሁን ስትጠይቁ ስለነበር በፈተና የሚቀርቡላችሁን ጥያቄዎች በትክክል እንደምትመልሱ አንጠራጠርም! ምክንያቱም የምትጠየቁት የተማራችሁትን ስለሆነ በአንዳች ነገር እንዳትዘናጉ!
ታዲያ ልጆች! ፈተናውን የምትሠሩት ጥሩ ማርክ ለማምጣት ብቻ ሳይሆን ለእውቀትም መሆን አለበት፡፡ ዕውቀት ማለት በተግባር መተርም መሆኑን እንዳትዘነጉ! መልካም! ልጆች ዛሬ ስለ ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት እንማራለን፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ከአምላካችን ዐበይት በዓላት አንዱ ጥምቀት ነው፤ በዓሉን የምናከብርበት ምክንያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ዮሐንስ ያጠምቅበት ከነበረው ባሕረ ዮርዳኖስ በመሄድ የተጠመቀበት ነው፡፡ ጌታችን በትሕትና ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ሄዶ ተጠመቀ፤ ቅዱስ ዮሐንስም ጌታችንን ‹‹እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጂ፤ አንተ ወደ እኔ እንዴት ትመጣለህ?›› ቢለውም ጌታችን ለእኛ ትሕትናን ሊያስተምር ከቅዱስ ዮሐንሰ ዘንድ ሄዶ ተጠመቀ፡፡ (ማቴ.፫፥፲፬-፲፭)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን የተጠመቀው ለእኛ አርአያ ለመሆን ነው፤ እኛም መጠመቅና የልጅነት ፀጋ ማግኘት እንደሚገባን ሲነግረን ተጠምቆ አሳየን፤ እርሱ መጠመቁ ለእኛ ነው፡፡ ጌታችን ከሁሉም ወንዞች መርጦ ዮርዳኖስን ለመጠመቂያነት መምረጡ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛ በነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡ ‹‹…ባሕር አየች፤ ሸሸችም፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡›› (መዝ.፻፲፬፥፫) ሌላው ደግሞ ጠላታችን ሰይጣን አባታችን አዳምንና እናታችን ሔዋንን በባርነት ሊገዛቸው ‹‹አዳም የዲያቢሎስ ባርያ፣ ሔዋን የዲያቢሎስ ባርያ›› በማለት ያጻፈቸውን የዕዳ ደብዳቤ ነበር ያንንም አንዱን በባሕረ ዮርዳኖስ ደብቆት ነበርና ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ ደመሰሰልን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የጥምቀት በዓል ሲከበር ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው በዝማሬ በእልልታ ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሄዳሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ጌታችን ለመጠመቅ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ መሄዱን ለማዘከር ነው፡፡ ታቦታቱ የጥምቀት ዋዜማ ዕለት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ፣ አድባራቱ ወጥተው ልበሰ ተክህኖ በለበሱ አባቶች ጳጳሳት፣ ቆሞሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ዩኒፎርም በለበሱ በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በምእመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመሄድ በዚያ ያድራሉ፡፡ ስብሐተ እግዚአብሔር (ምስጋና)፣ ጸሎተ ቅዳሴ ሲደርስ ይታደርና በነጋታው በእልልታ በዝማሬ ታጅበው ወደ መንበረ ክብራቸው ይመለሳሉ፤ ምእመናን ለበዓሉ የሚሆን ልብስ ለብሰው በእልልታ በዝማሬ ከርቀት ሆነው ታቦታን ያጅባሉ፤ ታቦታቱ በሄዱበት ቦታ ሁሉ አካባቢውን ይባርካሉ፡፡ ይህ በዓል የዕዳ ደብዳቤያችን የተደመሰሰበት፣ ጠላታችን ዲያቢሎስ ያፈረበት፣ የፈጣሪያችን የቅድስት ሥላሴ ሦስትነት የታየበት ነው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ወልድ በባሕረ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ፣ እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይሄ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ ምስክርነት ሲሰጥ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሣል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ ታየ፤ በዓሉ ይህንን ሁሉ የምናዘክርበት በዓል ነው፡፡ (ማቴ.፲፯፥፭)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዓሉን ስናከብር የጌታችንን ውለታ እያዘከርን፣ የእርሱን አርአያ በመከተል ትሁታን ሆነን፣ ለሰዎች መልካም በማድረግ መሆን አለበት፤ ጌታችን እኛን ከወደቅንበት ሊያነሣን በትሕትና በቤተልሔም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከጠላታችን ዲያቢሎስ ባርነት ነጻ አወጣን፤ እኛም ይህን ውለታውን እናዘክራለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እኛም ጌታችን በጥምቀት ወቅት ያደረገውን ትሕትና አርአያ አድርገን በሕይወታችን ታዛዦች፣ ለሰዎች የምናዝን፣ መልካም ነገርን የምናደርግ አስተዋይና ብልህ ፣ቅን ልጆች ልንሆን ይገባናል፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት የምናገለግል አብረን እየዘመርን ካልሆነም ደግሞ ከወላጆች ጋር ሆነን በሥርዓት በዓሉን እናክብር! በዓሉ ሰላማችን፣ ነጻነታችን የታወጀበት፣ ከዕዳ ነጻ የሆንበት ነው፡፡ በሰላም፣ በፍቅር፣ ሆነን ጸሎት መጸለይ ሳንዘነጋ ለዚህ ያረሰንን ፈጣሪ እያመሰገንን እናክብረው፡፡
አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት በረከቱን ይክፈለን (ይስጠን) አሜን!!! ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!