ምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም
ሚያዚያ ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
በሀገራችን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን የግራኝ አህመድ ወረራ ጊዜ ነግሠው የነበሩት አፄ ልብነ ድንግልም ሆኑ እርሳቸውን የተኳቸው ነገሥታት በጦርነቱ ምክንያት በቅድስት ሀገር ለተቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናት ርዳታቸውን ሲያቋረጡ ካህናቱ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስና ምግብ ባለማግኘታቸው ገዳማቱን ግማሹን በአደራ ለአርመንና ለግሪኮች በመስጠት ሌሎቹን ደግሞ ዘግተው ወደ አውሮጳ ተሰደዱ፡፡ ከዓመታት በኋላ ተመልሰው ሲመጡ ግን ሁሉንም ለማግኘት ባይችሉም አሁን የቀሩትን ንዋያተ ቅድሳት ይዘው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ ግራኝ ድል ተደርጎ ጦርነቱ ከቆመም በኋላ አንድ ወጥ መንግሥት የነበረው ቀርቶ የዘመነ መሳፍንት አገዛዝ በመቀጠሉና አሁንም በቂ ርዳታ ማግኘት ባለመቻሉ ድርጎ፣ ልብስና የመሳሰሉትን ቁሳ ቁሳች የሚያገኙት ከአርመንና ከግሪክ ገዳማት ነበር፡፡ ከግራኝ አህመድ ወረራ በኋላ እስከ አፄ ዮሐንስና ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ በኢየሩሳሌም ያሉ ገዳሞቻችንን በቋሚነት የሚረዳቸው ባለመኖሩ አብዛኞቹን የግሪክ የአርመንና የግብጽ አብያተ ክርስቲያን ወሰዷቸው፤ በ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ የወገኖቻችንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ቋሚ ገቢ እንዲኖራቸው በማሰብ በዚያው ኢየሩሳሌም ውስጥ ሕንፃ ተሠርቶ የሚከራይበት መሬትና ተጨማሪ ሌላ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ በሽህ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓ.ም በመግዛት አበርክተዋል፡፡
አፄ ምኒልክ በ፲፰፻፹፭ ዓ.ም ለኢየሩሳሌም ገዳማት የሚተዳደሩበት ቦታ ገዝተው ሕንፃ ሠርተው ሲሰጡ መምህር ፈቃደ እግዚእ የተባሉ መነኵሴን በኢየሩሳሌም አለቅነት ሹመውና ታቦተ መድኃኒዓለምን ይዘው እንዲሄዱ አድርገዋል፤ በወቅቱ የትራንስፖርት አቅርቦት ባለመኖሩ እስከ ጂቡቲ ድረስ በእግር ከዚያ በኋላ በመርከብ ተጕዘው ኢየሩሳሌም ደርሰዋል፡፡ ታቦተ ሕጉም በዴር ሡልጣን መድኃኒዓለም ገዳም (የንጉሥ ገዳም) ለ፴፬ ዓመታት ሲቀደስበት፥ ሲወደስበት ኖሯል፡፡
በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ጣሊያን ኃይሏን አጠናክራ ሽንፈቷን ለመበቀል ኢትዮጵያን ስትወረር ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ወደ ጅቡቲ በባቡር፤ ከዚያም በእንግሊዝ የጦር መርከብ ሚያዚያ ፳፮ ቀን ከጅቡቲ ተነሥተው ሚያዚያ ፴ ቀን ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ደረሱ፡፡ በሰኔ ወር ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ደግሞ በእንግሊዝ የጦር መርከብ ተሳፍረው ከኢየሩሳሌም ወደ እንግሊዝ ሀገር በደቡብ ሐምፕተን ወደብ አድርገው ወደ ለንደን ከተማ በባቡር ተጉዘው የውኃ ማጠራቀሚያ ጣቢያው ጋር ደረሱ፡፡ ለጥቂት ቀናት ከሰነበቱ በኋላ ስዊዘርላድ ውስጥ ጄኔቫ በሚገኘው የመንግሥታቱ ማኅበር ስብሰባ ላይ ሰኔ ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም የኢጣሊያ መንግሥት በሀገራችንና ሕዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በመዘርዘር አስረዱ፤ ነገር ግን ለአቤቱታቸው የመንግሥታቱ ማኅበር ምንም ዓይነት አቋምና እርምጃ አለመውሰዱ እንዳሳዘናቸው ‹‹እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ›› በማለት ልብን የሚነካ ታሪካዊና ትንቢታዊ ንግግር አድርገው ወደ ኢንግላንድ ተመልሰው በ ‹‹ባዝ›› ከተማ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የስደት ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡
ንጉሡም በማኅበሩ ላይ ተስፋ በመቁረጥ ፊታቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ በማዞር በጾምና በጸሎት ለመማጸን በማሰብ እንዲሁም የሃይማኖት ችግር እንዳያገኘን የሚያድጉ ልጆቻችን የሃይማኖታቸውን መሠረት እንዳይለቁ በማለት በብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ፈቃድ ቀደም ሲል በአፄ ምኒሊክ ወደ ኢየሩሳሌም ዴር ሱልጣን ገዳም ተልኮ አገልግሎት እየሰጠ የነበረውን ታቦተ መድኀኒዓለምን ከኢየሩሳለም ወደ እንግሊዝ እንዲላክላቸው በዚያው ዓመት የመድኃኒዓለምን ታቦት ዴር ሱልጣን መድኃኒዓለም በሚል ተሰይሞ መምህር ፈቃደ እግዚእ በተባሉ መነኩሴ ወደ ኢየሩሳለም ልከው በዴር ሡልጣን ገዳም ለ፴፬ ዓመታት ሲቀደስበት ሲወደስበት ኖሯል፡፡ በጥር ወር ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. አባ ሐና ጂማን ከእንግሊዝ ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ላኳቸው፤ አባ ሐና ጂማማ ታቦቱን ከሌሎች ዐራት መነኰሳት (መምህር ገብረ ኢየሱስ፣ አባ ማርቆስ፣ አባ ኃይሌ ቡሩክ እና አባ ገብረ ማርያም) ጋር በመሆን ወደ እንግሊዝ ይዘው ተመለሱ፡፡ ጽላቱም ንጉሡ በሚኖሩበት ቤት ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ባዝ ከተማ ደርሶ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡ በዚህ ቤትም ስደተኞቹ የጸሎትና የቊርባን ሥርዓትን እየፈጸሙ፤ የሚማሩበትና የሚጽናኑበት ሆኖ ቆየ፤ ስሙም ‹‹በስደት ያለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን›› እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡
በዓለም ጦርነት ኢጣልያ ከጀርመን ጎን ስትሰለፍ እንግሊዝ አፄ ኀይለ ሥላሴን ለመርዳት ወሰነች፡፡ በሰኔ ፲፯ ቀን ፲፱፻፴፪ ዓ.ም ንጉሡን ወደ ግብጽ ከዚያም ወደ ሱዳን በመውሰድ፤ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ለሚደረገው የጦር ዘመቻ ዝግጅት እንዲጀመር አደረገች፡፡ በሱዳን የነበሩ ብዙ ስደተኛ ኢትዮጵያን እንዲሁም ሌሎች ከኢትዮጵያ በመምጣት በካርቱም አስፈላጊውን የጦር፣ ልምምድና ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ከእንግሊዞች ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ሱዳን ከደረሱ ከሰባት ወራት በኋላ ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ከሱዳን ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ኦሜድላ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሰቀሉ፡፡ ከዚያም በጎጃም ደብረ ማርቆስ አድርገው ወደ መሐል ሀገር (በወጡ በአምስት ዓመታቸው ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም) ወደ መናገሻ ከተማቸው አዲስ አበባ በመግባት በቤተ መንግሥታቸው ባንዲራችንን ሰቀሉ፡፡ በስደት የነበረው ታቦት መድኃኒዓለም ነሐሴ ፳፫ ቀን ፲፱፴፫ ዓ.ም እቴጌ መነን ወደ አዲስ አበባ በተመለሱ ቀን አባ ኃይሌ ቡሩክ ታቦቱን ይዘው ተመልሰው በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የአሁኑ የስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ጸሎት ቤት ውስጥ እያጠኑና እየጠበቁ ከቆዩ በኋላ ለተበደሉትና ላዘኑት ማረጋጊያ፥ ለሕሙማን መጽናኛ ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፴፭ ዓ.ም ‹‹የምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም›› ተብሎ ተሰይሞ በቀድሞ ቤተ ሳይዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥለሴ ሆስፒታል (አሁን የካቲት ፲፪ ቀን ተብሎ በሚጠራው ግቢ) ውስጥ ተተከለ፡፡ የምስካዬ ኅዙናን ትርጓሜ ለተበደሉትና ላዘኑት ማረጋጊያ ማጽናኛ ማለት ነው፡፡
ሕመምተኛው በጸሎት በመፈወስ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ የሚሳለመው ሕዝብ ቊጥር እየተበራከተ በመምጣቱ ሕዝቡ ይበልጥ እንዲሳብና የቅዳሴ ፍቅር እንዲያድርበት በማለት በአባ ሐና መሪነት፥ በአባ ኃይሌ ቡሩክ ኃላፊነት ሌሎች አገልጋዮች ተቀጥረው ጸሎትና ቅዳሴው ጠቅላላው ሥነ ሥርዓቱ ሁሉ በስደት ሀገር አገልግሎት ይሰጥበት በነበረው በአማርኛ ተደረገ፤ ይህ ነገርም በመደበኛነት የቤተ ክርስቲያን ልሳኗ ግእዝ ከመሆኑ አንጻር በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥም ሆነ ውጭ ባሉት አባቶች ቅሬታ አስነሣ፡፡
ከአምስት ዓመት በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቤተ ክርስቲያኑ አሁን በሚገኝበት ቦታ ላይ እንዲሠራ ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵ ዓ.ም የመሠረተ ድንጋይ አኖሩ፡፡ ቦታው ሲመረጥ በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶችን (የተፈሪ መነኰንን፣ የእቴጌ መነን፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን) ከግምት ውስጥ በማስገባት ተማሪዎች ከቀለም ትምህርታቸው ጎን ለጎን በጸሎትና ትምህርተ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
ሕንፃውም ለሁለት ዓመት በፍጥነት ከተሠራ በኋላ ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. ተሠርቶ ተጠናቅቆ ቅዳሴ በቤቱ ተከበረ፤ በዋይዜማው ሚያዚያ ፳፮ ቀን ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኑ ቡራኬ ሥነ ሥርዓትና የሰዓታት ጸሎት እስከ ንጋቱ ፲፪ ሰዓት ሲካሄድ አደረ፡፡ ታቦቱም ከቤተ ሳይዳ (የካቲት ፲፪) ሆስፒታል ግቢ ወጥቶ አዲስ ወደተሠራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገባ፡፡ ንጋት ልክ ፲፪ ሰዓት ተኩል ሲሆን አፄ ኃይለ ሥላሴ እቴጌ መነንና ንጉሣውያን ቤተሰቦች እንደደረሱ እና ብዙ ምእመናን በተሰበሰቡበት የቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ተጀመረ፡፡ በዕለቱም የቅዳሴው ሥነ ሥርዓት የተመራው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ አቡነ ቴዎፍሎስና፣ አቡነ ጢሞቴዎስ ነበር፡፡ ከቅዳሴውም በኋላ የገዳሙ አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ሐና የታቦቱን የስደትና የመመለስ ታሪክ የሚገልጽ ስብከት ለ፲፭ ደቂቃ ካሰሙ በኋላ በስደት ሀገር ሲዘመር የነበረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ መዝሙር ተዘመረ፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ የቡራኬ ጸሎት አድርገው ናዝዘው፣ ሠርሆተ ሕዝብ ካደረጉ በኋላ፣ ታቦቱ ወጥቶ ሥርዓተ ዑደት ተደርጐ የበዓሉ ፍጻሜ ሆነ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ (የገዳሙ) ቅዱሳት ስዕላት፤ ቤተ ክርስቲያኑ ተመርቆ አገልግሎት ከጀመረ ከስምንት ዓመታት በኋላ በውጭ ሀገር ሰዓሊ ከ፲፱፻፶ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፶፬ ዓ.ም በነበረው ጊዜ የተሣሉ ናቸው፡፡ ገዳሙ እንደታላላቅ ገዳማት ማኅሌት አይቆምበትም፤ የከበሮና የጸናጽል ድምፅም አይሰማበትም፡፡ ታቦቱ የሚነግሠውም በዓመት አንዴ ሚያዝያ ፳፯ ብቻ ነው፡፡
ምስካዬ ኀዙናን መድኃኒዓለም አፄ ምኒልክ ታቦቱን ወደ ቅድስት ሀገር ልከው ከዚያም በእንግሊዝ ሀገር በስደት ለብዙዎች መጽናኛ ሆኖ ቆይቶ ወደ ሀገራችን ተመልሶ እስከመጣበትና እስከ አሁንም ድረስ በታሪካዊ ሂደቱና በአገልግሎቱ የተለያዩ ሥራዎችን በመጀመር ለሌሎች ቤተ ክርስቲያናት አርአያ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ገዳም ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የምስካዬ ኀዙናን መድኃኒዓለምና ሌሎቹን ገዳሞቻችንን ይጠብቅልን ዘንድ በጸሎት መማጸን ይገባል! ሀገራችንንም በበረከቱና ቸርነቱ እንዲጎበኝልን ዘወትር እንጸልይ! ቸሩ መድኃኒዓለም የተበደሉትን፣ የተሰደዱትንና የሚጎሳቆሉትን ወገኖቻችንን ሁሉ ያጽናናልን!
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም