ሀልዎተ እግዚአብሔር
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥር ፳፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው እየበረታችሁ ነውን? በርቱ!
ልጆች! በዚህ ምድር ለመኖር ምግብ መመገብ የግድ ያስፈልጋል አይደል! ለመብላት ደግሞ ፈጣሪ አምላካችን አባታችን አዳምን እንዳዘዘው ‹‹ወደ መጣህባት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ ..›› (ዘፍ.፫፥፲፱) ባለው መሠረት ለመብላት ደግሞ መሥራት አለብን፡፡ አይደል! ለመሥራት ደግሞ መማር! አያችሁ ልጆች! ነገ ሠርታችሁ ራሳችሁንም እንድትጠቅሙ ቤተሰብንም እንድትረዱ ለሀገር ለወገን የምታገለግሉ እንድትሆኑ ዛሬ በልጅነታችሁ ጎብዛችሁ መማር አለባችሁ፤ ትምህርቱን እንዲገልጥላችሁና ማስተዋል ጥበብን እንዲሰጣቸሁ ደግሞ እግዚአብሔረን በጸሎት ልትጠይቁት ይገባል፤ መልካም!!!
ልጆች! ለዛሬ የምንማረው ስለእግዚአብሔር መኖር (ሀልዎተ እግዚአብሔር) በተሰኘ ርእስ ይሆናል፤ እንደተለመደው በአጽንኦት (በትኩረት ሆናችሁ) እንድትማሩ አደራ እንላለን፡፡
የእግዚአብሔር መኖር (ሀልዎተ እግዚአብሔር) እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ፣የሚመግበን፣ ከክፉ የሚጠብቀን አምላካችን ፈጣሪያችን ነው! ልጆች! የፈጣያችን እግዚአብሔር መኖር የሚታወቀው በምንድነው ቢባል አንደኛው ማስረጃችን የሚሆነው የፈጠራቸው ፍጥረታት ናቸው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍትረት ላይ ‹‹እግዚአብሔር ሰማይንና ምድር ፈጠረ..›› (ዘፍ.፩፥፩) ተብሎ እንደተጻፈልን በሰማይም በምድርም ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነው! በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ እንዲህ በማለት ፈጣሪ መሆኑን ነግሮናል
ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ምን ብሎ ዘመረ መሰላችሁ፤ ‹‹ከማኅጸን ጀምሮ በአንተ ተደገፍኩ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ ሁል ጊዜም ዝማሬዬ ላንተ ነው ..›› (መዝ.፸፥፮) በማለት እኛን የሰው ልጆች እንደፈጠረን መስክሮልናል፡፡ የሌሎችንም ፍጥረታት ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደሆነ ሲገልጽልን ጻዲቁ ኢዮብ ምን አለ መሰላችሁ ‹‹..እንሰሶችን ጠይቅ ያስተምሩሃል፤ ሰማይንም ወፎች ጠይቅ ይነግሩሁማል፤ ወይንም ለምድር ተናገር እርሷም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማነ ነው? የህያዋን ሁሉ ነፍስ የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናት፡፡ (ኢዮ. ፲፪ ፥፯) እንግዲህ የዓለም ፈጣሪ እንዳለ ከምንረዳበት (ከሚመሰክሩ ነገሮች አንዱ ፍጥረታት ናቸው ፤ ፍጥረታት ስንል ደግሞ በሰማይ ያሉቅዱሳን መላእክትን፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት ፣ ሰማያት ራሳቸው፣ በምድር ያሉትን እንሰሳቱን፣ አራዊቱን፣እጽዋቱን፣ ወንዞችን፣ ውቂያኖሶችን ሁሉ ማለታችን ነው፡፡ የምናመልከው፣ በምድር ከክፉ ነገር ጠብቆ እንዳንራብ እየመገበን ፣ እንዳንጠማ እያጠጣን፣ እያለበሰን የሚያኖረን በኋላም የክብር መንግሥቱን የሚያወርሰን እግዚአብሔርን ነው፡፡ የሚጠብቀን እርሱ ነው ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹..እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ የሚያሳጣኝም የለም፤ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል…›› በማለት እንደገለጸልን ጠባቂያችን እርሱ ነው፡፡ (መዝ.፳፪፥፩)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ የእግዚአብሔርን መኖር ከሚመሰክሩልን መካከል አንዱ የሆነውን ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትን ተመልክተናል፤ የትምህርታችን ዓላማው የዓለማት ፈጣሪ እግዚአብሔር እንዳለ ማሳወቅ ነው፤ በእርግጥ እግዚአብሔር እንዳለ አንዳንድ ሰዎች ባያምኑም የእነርሱ አለማመን የፈጣያችንን መኖር አያስቀረውም፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ አንዲህ በማለት ያስተምረናል፤ ‹‹…የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?..›› (ሮሜ ፫፥፫) ልጆች! እንግዲህ ሰዎች ቢቀበሉም ባይቀበሉም፣ ቢያምኑም ባየምኑም እግዚአብሔር ትላንትና ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ነበረ፣ ዓለምንም ከፈጠረ በኋላ አለ፣ ወደፊትም ዓምን አሳልፎ ይኖራል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው መገንዘብ ያለብን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በፈጠራቸው ፍጥረታት ይታወቃል ማለታችን የተፈጠሩት ፍጥረታት በሥርዓት በመኖራቸው የእግዚአብሔርን መኖር ይመሰክራሉ፤ ለምሳሌ ያህል ብንመለከት ቀን ፀሐይ በምሥራቅ አቅጠጫ ትወጣለች፤ ከዚያም ለእኛ ለሰዎች በፈጣያችን ቸርነት ስታበራልን ትቆይና የቀኑ ጊዜ ሲያበቃ በምዕራብ በኩል ትጠልቃለች፤ ከዚያም ልጆች እግዚአብሔር በሌሊት እንድታበራልን የፈጠራቸው ጨረቃም፣ ክዋክብትም ይወጣሉ ይህ የፍጥረታት በሥርዓት መመራት የሚያዛቸው ፈጣሪ እንዳለ ያስረዳናል፤ ነቢዩ ክቡር ዳዊት የእግዚአብሐየርን ሁሉን ቻይነት በገለጠበት በዝማሬው ውስጥ እንዲህ የሚል ኃይለ ቃል አለ ‹‹…ለፀሐይ ቀንን ያስገዛ ለጨረቃና ለክዋክብት ሌሊትን ያስገዛላቸው….›› (መዝ.፻፴፭፥፰)
አስተዋላችሁ ልጆች! ፀሐይ መውጫና መግቢያ አላት፤ በቀን ታበራለች፤ ጨረቃና ክዋክብት ደግሞ በሌሊት፤ ይህን ሥርዓት እንዲያከናውኑ የሚያዛቸው ደግሞ ፈጣሪ ነው፤ ሌላው አፍላጋት (ወንዞችን )፣ ባሕር ፣ ሐይቆችን፣ ብንመለከት የሚያዛቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ የእነዚህ ሥርዓታቸውን ወይም ገደባቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው፤ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በምሳሌው እንዲህ ይነግረናል፤ ‹‹..የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፣ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜና ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፣ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ…›› (ምሳ.፰፥፳፱)
እንግዲህ ልጆች! ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎቻችን ጥቂቱን ብቻ ለአብነት በመጥቀስ የሥነ ፍጥረታት በሥርዓት መመራት የእግዚአብሔርን መኖር የሚመሠክሩልን ማስረጃዎች እንደሆኑ ተመልክተናል፤ በዚህም በርካታ ቁም ነገሮችን እንደተማራችሁ ተስፋችን እሙን ነው!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ በዚህ ይቆየን በቀጣይ ደግሞ ስለ ሐልዎተ እግዚአብሔር ምስክር የሚሆኑትን ማስረጃዎች እንማማራለን፡፡ ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!