‹‹እግዚአብሔር መልካም ነው፤ በመከራ ቀን መሸሸጊያ ነው›› (ናሆም ፩፥፯)
መጋቢት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
እግዚአብሔር አምላክ የሰዎችን ደኅነትን የሚሻ መልካም አባት በመሆኑ ልጆቹን ከመከራ ይሸሽጋል፡፡ በዘመነ ኦሪት እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ሲኖሩ ከመከራ ሠውሯቸዋል፤ ነፃ ሊያወጣቸውም ፈቅዶ ነቢዩ ሙሴን እንዲህ አለው፤ ‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያንም ተገዥነት አወጣችኋለሁ፥ ከባርነታችውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ፤ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፡፡›› (ዘፀ. ፮፥፮-፯)
ከዚህም በኋላ በእስራኤል ላይ ነግሦ ሕዝቡን ያሠቃይ የነበረውን ንጉሥ ፈርዖንን እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት እንዲለቃቸው ቢነግረውም አሻፈረኝ አለ፡፡ በዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የተለያዩ መቅሠፍቶችን በእርሱ እና በሕዝቡ ላይ በመላክ እንዲሁም በመጨረሻም የእርሱ ጣዖታት በአስማታቸው በማይችሉት መቅሠፍት ግብፃውያንን አጠፋቸው፡፡ ሕዝበ እስራኤልን ግን መቅሠፍቱ እንዳይደርስባቸው ይጠብቃቸው ነበር፤ ‹‹እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሠፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁ…፤ ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለውም ደም ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ ከእናንተም አንድ ሰው ከቤቱ ደጅ እስኪነጋ ድረስ አይውጣ። እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም›› እንዲል፡፡ (ዘፀ. ፲፪፥፲፪-፳፫)
እስራኤላውያንም እንደታዘዙት አደረጉ፤ ጊዜውም ከተፈጸመ በኋላ መንጋዎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶችን ይዘው ከግብፅ ምድር ወጡ፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ‹‹ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው።›› ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ ስላጸና እስራኤላውያንን አሳደደ፡፡ ወደ ባሕሩ ዳር በብኤልሴፎን ፊት ለፊት ባለው ገላጣ መንደር አንጻር ሰፍረውም ባገኛቸው ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ ‹‹አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሠረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ።…›› ሙሴም እንደታዘዘው በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ፤ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም አደረቀው፥ ውኃውም ተከፈለ። እስራኤልውያንም በባሕሩ መካከል በየብስ አለፉ፤ በቀኛቸውና በግራቸው ውኃውም እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። (ዘፀ. ፲፫፥፲፰፣ ፲፬፥፰-፳፩ )
ግብፃውያንም ይህን ባዩ ጊዜም ሕዝቡን በማሳደድ በባሕሩ መካከል ገቡ፤ እግዚአብሔርም ውኃውም በግብፃውያንና በሠረገሎቻቸውም በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ ዘንድ ሙሴን እጁን በባሕሩ ላይ እንዲዘረጋ አዘዘው፤ የሙሴም እጅ በባሕሩ ላይ በተዘረጋ ጊዜ ውኃው ወደ ነበረበት ተመለሰ፤ ግብፃውያንም በባሕሩ መካከል ሰጠሙ፡፡ (ዘፀ.፲፬፥፳፪-፳፯)
ከዚህም በኋላ በነቢዩ ሙሴ መሪነት ወደ ሀገራቸው እስራኤል እስኪመለሱ ድረስ እግዚአብሔር አምላክ በርኀብና ጥማት እንዳይሞቱ ከአለት ውኃን እያፈለቀ ከሰማይም መናን እያወረደና እየመገበ ከደረሰባቸው መከራ ሁሉ ሠውሯቸዋል፡፡
በርግጥ እኛን እንደ እስራኤላውያኑ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር በመከራ ጊዜ በነቢያት ላይ አድሮ ትእዛዝ እየሰጠ እና እየገሠጸ ባይመራንም በአንድ ልጁ መሥዋዕትነት ባዘጋጀልን ሥርዓት ከመከራ የምንወጣባትን በመከራ ቀንም የምንሸሸግባትን ተዋሕዶ ሃይማኖትን ሠርቶልናል፡፡
በዚህች ሃይማኖታችንም በሕይወታችን ከሚያጋጥመን ከክፉ ነገር ሁሉ እንድናለን፤ ይህም በእምነት ጸንተን እስከ መጨረሻው እንድንጓዝ ይረዳናል፡፤ በዘመናት የነበሩ ቅዱሳን አባቶች የፈጣሪያቸውን ህልውና በልቡናቸው ተረድተው በሃይማኖታቸው ጥላ ከለላነት የመከራ ቀንን አልፈዋል፡፡ ስለዚህም በስመ ኦርቶዶሮክስ ተዋሕዶ የሚኖር ማንኛውም ሰው የሃይማኖትን ትርጕም በውል ተረድቶ በሥርዓቱ ሊኖር ይገባል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ በሃይማኖት ስንኖር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚነገሩትን የሚሰበኩትን አምስቱን አእማደ ምሥጢር፣ ሰባቱን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሌሎች ምሥጢራትንም በእምነት ተቀብሎ ለእግዚአብሔር በመታመን መተግበር አለብን፡፡ ምሥጢራቱም ወደ ማመን ሲያደርሱን ለሕገ እግዚአብሔር ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመገዛት በእርሱ ፈቃድ ተገዝተን መኖር እንችላለን፡፡ በዚህም የሃይማኖት ጽናትን ስለምናገኝ በመከራም ሆነ በችግር ጊዜ ከመፍራት ይልቅ ተቋቁመን እንድናልፍ፣ በመቅሠፍትም ሆነ በቸነፈር ወቅትም ከአሕዛብ መካከል ተጠብቀን እንድንኖር ያደርገናል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ የእርሱን ህልውና አውቀውና ተረድተው ሕጉን በመፈጸምና ትእዛዛቱን በመጠበቅ በእርሱ ፈቃድ ጸንተው የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ከመቅሠፍትም ይጠብቃል፤ ከጥፋትም ይታደጋልና፡፡
ሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩ ከሚደርስባቸው መከራና ሥቃይ እግዚአብሔር አምላክ ይታደጋል፤ በእኛም ትውልድ በተለይም በኃጢአታችን የተነሣ ከመጣብን ቸነፈር በመጠንቀቅ ሳይሆን በእምነት ጸንተው፣ ለሃይማኖታቸው ተገዝተው እና መሥዋዕት ሆነው የኖሩት ሰዎች ተጠብቀዋል፡፡ ለዚህም ምሳሌ በተለያዩ ዘመናት ተስፋፍተው የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ ወረርሽኞች እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ካንሠር፣ ኢቦላ፣ ሳርስ እንዲሁም የቅርብ ጊዜው ገዳዩ ቫይረስ ኮሮናን ጨምሮ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ በሽታዎች መቅሠፍት የመሆናቸው ማረጋገጫም በሽታዎቹ በሕክምና ሳይንስም ሆነ በባሕላዊው የሕክምና ዘርፍ ምርምር መድኃኒት ያልተገኘላቸው መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በሽታዎቹ በሚባዙበት ወቅት በተለይም ኮሮና በተሠራጨበት ጊዜ እህል ጨረሻ የአንበጣ መንጋም በገጠርማው የሀገራችን ኢትዮጵያ መከሠቱ የእግዚአብሔር ቁጣ እንደሆነ ማረጋጫ ነው፡፡ ስለዚህም ይህን የተረዱ ሰዎች እውነታውን በመቀበል በሳይንሱ አካሄድ ለመከላከል ከመጣር ይልቅ በእምነት ጸንተው ለእግዚአብሔር ታምነው መኖርን ስለመረጡ ፈጣሪያቸው ከበሽታው መቅሠፍት ታድጓቸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር አምላክ ሰዎችን ከሚደርሳባቸው ከመኪናም ሆነ ከአውሮፕላን እንደሁም ከተመሳሳይ የከፋ አደጋ በተለይም ሕፃናትን አትርፏል፤ ይህም የእርሱን መልካምነት ያሳየናል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ ከየትኛውም መከራ እንደሚጠብቀን በማመን በሃይማኖት ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡