የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን ተቃጠለ
መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን መንሥኤው ባልታወቀ እሳት መቃጠሉን የገዳሙ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ በመጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም የጀመረውን እሳት ለማጥፋት ርብርብ ቢደረገም ከሰው ዐቅም በላይ በመሆኑ ማጥፋት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ የገዳሙ መነኰሳት፣ ከሐረር፣ ድሬዳዋና አሰበ ተፈሪ የተሰባሰቡ ምእመናን እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ቃጠሎውን ለማስቆም ቢሞክሩም ጥረታቸው ባለመሳካቱ ደኑ በመቃጠል ላይ ይገኛል፡፡ አካባቢውም ንፋሳማ በመሆኑ በተለይም ምሽት ላይ የሚነፍሰው ኃይለኛ ንፋስ ቃጠሎውን በማባባሱ እሳቱ ደኑን ጨርሶ ወደ ገዳሙ በመድረስ እንዳያቃጥለውም ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያም አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም ቃጠሎው ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ እየተዛመተ ስለሆነ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባና መንግሥትም በተቻለ ፍጥነት ገዳማውያኑን፣ የአካባቢ ኖዋሪዎችንና ምእመናን ከጥፋት ሊታዳግ እንደሚገባም የገዳሙ አበምኔት አሳስበዋል፡፡
በቅድስት ሥላሴ ገዳም ዙሪያ ውስጥ የመነኰሳት መኖሪያ ሲሆን የአገልጋዮቹ መኖሪያ ደግሞ ገዳሙን በመሠረቱት በአባ ሳሙኤል ዘወገግ ገዳም ዙሪያ በመሆኑ የመነኰሳቱን፣ የመነኰሳይያቱን፣ መናንያኑን፣ የባሕታውያን እና የአብነት ተማሪዎችን ህልውና ለመጠበቅ ይህን ገዳም ከቃጠሎ መታደግ እንዳለብን አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
በመጨረሻም ገዳሙም ሆነ በዙሪያው ያሉት የተፈጥሮ ሀብቶች በእሳት ቃጠሎ እንዳይወድም አበው የሃይማኖት አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን በሙሉ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመጮህ እንዲማጸኑም አሳስቧል፡፡