ልደተ ክርስቶስ
በዝግጅት ክፍሉ
ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ቅድስት ድንግል ማርያም ለአረጋዊው ዮሴፍ ከታጨች በኋላ ናዝሬት ገሊላ ከምትባል ከተማ ትኖር በነበረበት ከዕለታት በአንዱ ቀን ውኃ ቀድታ ስትመለስ መንገድ ላይ በመሄድ ሳለች የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሷ ቀርቦ እንዲህ አላት፤ ‹‹ትፀንሲ!›› እርሷም ድምጽን ሰምታ መለስ ብላ ብታይም ከአጠገቧ ማንንም ማየት ባለመቻሏ ‹‹አዳም አባቴን እና ሔዋን እናቴን ያሳተ ጠላት ይሆናል እንጂ ሌላ አይደለም›› ብላ አሰበች፡፡ ዳግመኛም ‹‹ትፀንሲ›› የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ ‹‹ይህ ነገር ደጋገመኝ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ከቤተ መቅደስ ሆነው ሊረዱት ይገባል›› ብላ ከቤተ መቅደስ ገብታ ወርቅና ሐር እያስማማች መፍተል ጀመረች፡፡ (ነገረ ማርያም)
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በአምሳለ አረጋዊ እንዲህ አላት ‹‹ደስ ይበልሽ÷ ጸጋን የተመላሽ ሆይ÷ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ፡፡›› ድንግል ማርያምም ‹‹እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንዴት ይደረግልኛል?›› ብላ ጠየቀችው፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹ማርያም ሆይ አትፍሪ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና፤ እነሆ ትፀንሺያለሽ፤ ወንድ ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፤ ይህ የሚወለደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ይህ ነገር እንደምን ይሆንልኛል፤ ወንድ ሳላውቅ?›› አለችው፡፡ መልአኩ ገብርኤልም ‹‹መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል፤ የልዑል ኃይልም ያድርብሻል›› አላት፡፡ እርሷም የመልአኩን ቃል ተቀብላ ‹‹እንደ ቃልህ ይደረግልኝ›› አለችው፤ በዚህ ጊዜ አካላዊ ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀነሰ፡፡ (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱፣ ኢሳ. ፯÷፲፬)
ከዚህ በኋላም ንጉሥ አውግስጦስ ቄሳር ሕዝቡን ቀረጥ ለማስከፈል እንዲያመቸው በእስራኤል ሀገር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን ለማወቅ ቆጠራ እንዲደርግ አዘዘ፡፡ ሕዝቡም ለመቆጠር ወደ ትውልድ ስፋራው መጓዝ ጀመረ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያምም የንጉሥ ዳዊት ዘር ሀረግ ስለነበራት ግዛቱ ወደ ነበረው ቤተ ልሔም ከአረጋዊው ዮሱፍ ጋር ሄደች፡፡ በዚያም ሳሉ እመቤታችን መውለጇ ቀን ደረሰ፡፡ ሆኖም ግን ከተማዋ ትንሽ ስለነበረችና ለመመዝገብ የመጣው ሰው ብዙ ስለነበረ ማረፊያ ቦታ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ አረጋዊው ዮሴፍም ከብዙ ድካም በኋላ ከብተቾች የሚያርፉበት በረት አግኝቶ እመቤታችንን በዚያ አስቀመጣት፡፡
በከብቶች በረት ውስጥ ሳሉ እመቤታችን የመውለጃዋ ጊዜ በመድረሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው፤ በጨርቅ ጠቅልላ በበረት ውስጥ አስተኛችው፡፡
በዚያን ሌሊት በቤተ ልሔም ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ የእግዚአብሔር መልአክ በእረኞቹ አጠገብ ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው በራ፤ በጣምም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፡፡ ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው፡፡ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ፤ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ፡፡›› (ሉቃ.፪፥፲-፲፫)
እረኞቹም እርስ በርሳቸው ‹‹እስከ ቤተ ልሔም እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ›› ተባባሉ፤ ፈጥነውም ሄዱ፡፡ ድንግል ማርያምንና ዮሴፍንም በከብቶቹ በረት አገኙአቸው፡፡ ሕፃኑንም በአዩት ጊዜ የነገሩአቸው እውን መሆኑን ስላዩ በጣም ተደነቁ፡፡ እረኞቹም እንደነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው እያመሰገኑና እያከበሩ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ (ሉቃ.፪፥፲፭-፲፰)
ሰብአ ሰገልም የእግዚአብሔር ልጅ የተወለደበትን ዋሻ የሚያመለክት ኮከብ እየመራቸው ከምሥራቅ ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ አምላክ መወለድ አስቀድመው ያውቁ ነበርና፡፡ ስለሆነም ኮከቡን ተከትለው ልጁን ይፈልጉ ነበር፡፡ የይሁዳም ንጉሥ ሄሮድስ ሕፃኑን ስለሚሹት ጠቢባን ሰዎች ሲሰማ ቀደም ብሎ ወደ ቤተ መንግሥቱ ጋበዛቸው፡፡ እንደ እነርሱም ጌታችን ኢየሱስን ለማምለክ እንደሚፈልግ በመግለጽ ልጁን ሲያገኙት ወደ እርሱ ይዘውት እንደሚመጡ ጥበበኞቹን ጠየቃቸው፡፡ ሄሮድስ ግን ዙፋኑን ሊወስድ ይችላል ብሎ በመፍራት ጌታ ኢየሱስን ለመግደል ፈለጎ እንጂ ሊያመልከው አልነበረም፡፡
ሰብአ ሰገልም በኮከብ ተመርተው ቅድስት ማርያምን፣ ዮሴፍን እና ጌታ ኢየሱስን ወደ ነበሩበት በረት በደረሱ ጊዜ በጉልበታቸው ተንበረከኩ፤ አምላክነቱን በመረዳትም ለሕፃኑ ሰገዱለት፤ ዕጣን፣ ወርቅና ቀርቤንም የእጅ መንሻ አድርገው አቀረቡለት፡፡
ሆኖም ግን ወደ ሄሮድስ አልተመለሱም፡፡ ሄሮድስ ኢየሱስን ሊጎዳ እንደሚፈልግ የሚያስጠነቅቅ ሕልም አስቀድመው በራእይ አይተው ነበርና፡፡ ይልቁንም በተለየ መንገድ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፤ እርሱ ለእኛ መድኅን ነውና፡፡
የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የወረደበት፣ ከኃጢአት ባርነት ነጻ የወጣንበት፣ ድንቅ የተዋሕዶ ምሥጢር የተፈጸመበት ነው፡፡ ነቢያት ስለክርስቶስ የተናገሩት ሁሉ ተፈጽመ፤ ስለ ጌታችን መወለድ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው›› ብሎ ተናግሯል፡፡ (መዝ. ፴፩፥፮)
በጌታችን ኢየሱስ ልደት መላእክትና ሰዎች በአንድነት ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር›› እያሉ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ በኃጢአታችን ሳቢያ አጥተነው የነበረውን አንድነት የመላእክትና የሰው ልጆች አንድነት ከብዙ ዘመን በኋላ በጌታችን ልደት እንደገና አገኘነው፡፡
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ዘር በሙሉ ያዳነበትን ድንቅ ሥራ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረው እርሱ ሕፃን ሆኗልና፡፡ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ፡፡ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፡፡ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ፡፡ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት፤ ይህን ወዷልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ፷፮፥፲፯)
እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ሆኖ ለእኛ የድኅነት መንገድ ሆነ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም የገባለትን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ሰው ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ድኅነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ በመስቀሉ ተጣልተው የነበሩ ሰባቱን መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) አስታርቋል፡፡
በጌታችን ልደት ምክንያት እኛም ዳግም ተወልደን ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋገርን፤ ከጨለማ ወጥተን ብርሃን አገኘን፤ የእርሱ መወለድ የእኛም የክርስቲያኖች ሁሉ ልደት ነውና በዓሉን በክርስቲያናዊ ምግባር ታንጸንና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ልናከብር ይገባል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በዓሉን የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት ያድርግልን፤ አሜን!