ክርስቲያናዊ አንድነት
በዝግጅት ክፍሉ
ኅዳር ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ክርስቲያናዊ አንድነት በእምነት አንድነትና በአስተምህሮ ስምምነት የሚገለጥ ነው፡፡ በዚህም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሰዎች የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በማመን፣ ከሀብተ መንፈስ ቅዱስ በመወለድ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል በአጠቃላይ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመገዛት መኖር ማለት እንደሆነ እንረዳለን፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ባሕርይ አባቱ ወደ አብ እንዲህ ብሎ እንደጸለየ ተጽፏል፤ ‹‹ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተ አብ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም እንደ እኛ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፡፡ እኔም የሰጠኸኝን ክብር ሰጠኋቸው፤ እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ፡፡ እኔ በእርሱ እኖራለሁ፤ አንተም በእኔ፤ በአንድ ፍጽማን ይሆኑ ዘንድ፤ አንተም እንደ ላክኸኝና እንደ ወደድኸኝ እኔም እነርሱን እንደ ወደድኋቸው፡፡›› (ዮሐ. ፲፯፥፳-፳፫)
ጌታችን ኢየሱስ ስለወደደን ለእኛ ድኅነት ሲል በመስቀሉ ላይ ተሥውቶ እኛም እንደርሱ ለሌሎች ፍቅር እንዲኖረን አስተምሮናል፡፡ ‹‹አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደደው፤ ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡ የምትመስላት ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትለው ናት፤ ኦሪትና ነቢያት በእነዚህ ሁለቱ ትእዛዛት ጸንተዋል፡፡›› (ማቴ. ፳፪፥ ፴፯-፵)
ጌታችንም እንዳስተማረን ባልንጀራን እንደራስ መውደድ ወይንም ፍቅረ ቢጽ በአንድነት ለመኖር ይረዳናል፤ ምክንያቱም ሰውን እንደራሳችን መውደድ ከቻልን አንድ ዓይነት ሰብእና ስለሚኖረን ከልዩነት ይልቅ አንድነት ይኖረናልና ነው፤ ከጥል ይልቅም ስምምነት በመካከለችን ይፈጠራል፤ ደስታንንም ሆነ ኃዘንን በጋራ እናሳልፋለን፤ በኅብረትም እንኖራለን፡፡
በዚህም ሥርዓት ክርስቲያኖች በዘመናቱ በአንድነት ይኖሩ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተገልጿል፡፡ ለዚህም በሐዋርያት ሥራ ላይ የተመዘገበውን አንድ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹ያመኑትም ሁሉ አንድ ልብ አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ “ይህ የእኔ ገንዘብ ነው” የሚል አልነበረም፡፡ ሐዋርያትም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፡፡ በሕዝቡም ዘንድ ታላቅ ጸጋ ነበራቸው፡፡ ከእነርሱም አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ ቤትና መሬት ያላቸውም ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን ያመጡ ነበር፡፡ አምጥተውም በሐዋርያት እግር አጠገብ ያኖሩት ነበር፡፡›› (ሐዋ. ፬፥፴፪-፴፭)
በመሆኑም ትውልድ ሀረጋችን ቢለያይ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን ብንናገር፣ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በዕውቀት እንዲሁም በሀብት መጠን ብንለያይ እንኳን ተስማምትን በአንድነት ልንኖር እንደሚገባም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትመክራለች።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች አንድነት መገለጫ ናት፤ ልጆቿንም ሰብስባ ታኖራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንል የክርስቲያኖች መገናኛ፤ መሰብሰቢያ በዓት ማለት ሲገልጽ ‹‹ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ እንደተጻፈ የለምን? እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት›› አላቸው፤ ይህም ክርስቲያኖች በአንድነት የሚጸልዩበት፣ የሚሰግዱበት፣ ሥጋ ወደሙን የሚቀበሉበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታና የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ (ማር. ፲፩፥፲፯፣ ሉቃ.፲፱፥፵፮)
‹ቤተ› ማለት ወገን ኅብረት የሚለውን ትርጉምም እንደሚይዝ ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ ለምሳሌ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ አሮን ሲል የአሮንን፣ የእስራኤልን እንዲሁም የያዕቆብን ወገን ማለት ነውና፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ወገን ማለት ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ (የምእመናን አንድነት ጉባኤ) የሚጠራበት ስም ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ይህም የሚመለከተው ስብስቡን ብቻ ሳይሆን በዋናነት በመካከላችን ያለውን ፍቅር ትስስር ኅብረት አንድነት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ራስነት አንድ አካል የሆኑ የምእመናን አንድነት ናት፡፡ ‹‹እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው . . . አካሉ ስለሆነች ስለ ቤተ ክርስቲያን፥ ከክርስቶስ መከራ ጥቂቱን በሥጋዬ እፈጽማለሁ›› እንዲል፤ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለ መድረክ፣ ቈላ. ፩፥፲፰-፳፬)
ክርስቲያናዊ አንድነትን ጠብቆ እስከመጨረሻው ለመጓዝም ክርስቲያናዊ ተግባርን ያለማጓደል መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ክርስቲያኖች ለሕገ እግዚአብሔር መገዛት፣ በትእዛዙ መኖር እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ እንዳለባቸው ጠንቅቀው በመገንዘብም ከእራሳቸው አልፎ ለሌሎች ክርስቲያናዊ ሕይወት ስኬት መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ክርስትና ሕይወት ሁሌም በፈተና ላይ ናትና በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን እኛ ክርስቲያኖች ችግር መከራና ስቃይን ለመቋቋም መተሳሰብ እና መተዛዘን እንዲሁም ችግራችንን በጋራ መፍታት ይጠበቅብናል፡፡ ካልሆነ ግን ጠላታችን ዲያብሎስ በመካከላችን ጥላቻ በመፍጠር እና በድክመታችን በመጠቀም ኃጢአት ከማሠራት አልፎ እርስ በእርስ ሲያጣላን እንዲሁም ሲያጋድለን ይኖራል፡፡
ይህም በዘመናት በተለይም በእኛ ትውልድ የተከሰተ በመሆኑ ሁላችንም የታዘብነው ነገር ሆኗል፡፡ በሀገራችንም ጨምሮ ባለሥልጣናት ወይንም የተደራጁ ቡድኖች በማኅበረሰባችን ውስጥ የዘር፣ የሃይማኖትና የአመለካት ክፍፍል በመፍጠር ሰው ለሰው እንዳይዋደድ፣ እንዳይተሳሰብ ከዚያም አልፎ እንዲጠላላ እና እንደጠላት እርስ በእርስ በጦርነት እንዲጨራረስ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በክፍለ ሀገራቱም ባልረባ ነገር ሰዎች ላይ በመጨከን በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ ይፈጽማሉ፤ ከሰብአዊነት በወጣና ክብራቸውን በሚያሳጣ መልኩ ሬሳቸው ላይ አጸያፊ ነገረን ያደርጋሉ፡፡ በውስጣቸው ያለው ሰይጣናዊ አመለካከት እና እርኩስ መንፈስ በመልክም ሆነ በባሕርይ ከሚመስላቸው የሰው ዘር ላይ በደልና ግፍ እንዲፈጽሙ ይገፋፋቸዋል፤ ያለ ርኅራኄም በጭካኔ እንዲገድሏቸው ያደፋፍራቸዋል፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ሰዎች ከእግዚአብሔር አምላካቸው ርቀው እና ዓለማዊ ሕይወትን አስበልጠው ሲኖሩ በጥቅም በመያዛቸው እና የሥጋዊ ምኞትን ለማሳካት የሌላ ሰውን ሕይወት እስከማጥፋት በመድረሳቸው ነውና ክርስቲያኖች ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ልንርቅ ይገባል፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ከማይኖሩ መናፍቃን እና ዓለማቸው ክርስትናን እንደሁም ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚጥሩ ሰዎችንም መጠንቀቅም አለብን፡፡ ምክንያቱን እነርሱ ከራሳቸው አልፎ ሌሎችን ኃጢአት በማሠራት ለጥፋት ይዳርጋሉ፤ ዘረኝነትንን በማስፋፋት እና ማኅበረሰቡን በመከፋፈል አንድነት እንዳይኖር ያደርጋሉ፤ ፍቅር እና ሰላምንም እንድናጣ ሌት ከቀን ይጥራሉ፡፡ ሆኖም እኛ ክርስቲያኖች ሰላማችንም ሆነ አንድነታችን ከአምላካችን እግዚአብሔር ዘንድ ነውና ፈጣሪያችንን በፍጽም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ኀይላችን በመውደድ እንዲሁም ባልጃሮቻችንንም እንደራሳችን በመውደድ ልንኖር ይገባል፡፡
ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ ዘወትር በአንድነት ጾም እና በጸሎት መትጋት አለብን፤ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በየትኛውም ስፋራ የክርስቲያንነታችን መገለጫ የሆነውን በጎ ምግባር በኅብረት በመተግበር በጽድቅ ጎዳና እንጓዝ፤ ክርስቲያናዊ ምግባር መፈጸማችን አንድነታችንን ያጠነክርልናልና ከልዩነት ይልቅ አንድነታችንን እናጽና፤ እንዲህ ከበረታን እግዚአብሔር አምላክ በሥራችን ደስ ይሰኝብናልና በጉዛችን እንዲሁም በሕይወታችን ሁሉ ርዳታው አይለየንም፤ በዚህም በተስፋ ከፈጣሪያችን ጋር በአንድት ኖረን ወደ ዘለዓላማዊ ሕይወት እንጓዛለን፡ ስለሆነም ክርስቲያናዊ አንድነታችን ልናስጠብቅ ይገባል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በፍቅር፣ በሰላም እና በአንድነት እንኖረ ዘንድ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፤ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ›› በሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ በ፲፱፻፸፰ ዓ.ም. የታተመ