መስቀል ብርሃን ለኵሉ ዓለም
ለ፭፼፭፻ ዘመናት የሰው ዘር በኃጢአት ሰንሰለት ታስሮና በጨለማ ተውጦ በነበረበት ዓመተ ፍዳ እግዚአብሔር ወልድ ለዓለም ድኅነት የተሰዋበት ግማደ መስቀሉን ‹‹መስቀል ብርሃን ለኵሉ ዓለም፤ መስቀል የዓለም ብርሃን ነው›› እያልን እንዘክረዋለን፡፡
በዘመነም ሥጋዌ ዕለተ ዓርብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ከለየ እና በትንሣኤው ከሞት በ፫ኛው ቀን ሲነሣ ተሰቅሎ የነበረበት የእንጨት መስቀል ሌት ተቀን በሙሉ ሳያቋርጥ እንደፀሐይ አበራ፡፡ የመስቀሉ ኃይልም አጋንንት ሲያባርር፣ ድውይ ሲፈውስና ሙት ሲያነሣ ሲያዩ ቤተ እሥራኤል አይሁድ በቅናት ተነሥተው በዓዋጅ ትልቅ ጉድጓድ በመቆፈርና በመቅበር የቤት ጥራጊና አመድ አንዲሁም ጠቅላላ የቆሻሻ መከማቻ አደረጉት፡፡ ከዚያ ዘመን ጀመሮ እስከ ሦስት መቶ ዘመን ድረስ የተከማቸው ቆሻሻ እንደተራራ ሆነ፡፡
በዚያን ጊዜም የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ የተባለች ደግ ሴት የጌታችን ኢየሱስ ግማደ መስቀል መስከረም ፲፯ ቀን ፫፻፳ ዓ.ም. ላይ በዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን አገኘችው፡፡ መስቀሉንም በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው፡፡ ይህ መስቀልም ከዚያ ዘመን ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ፣ ድውይ እየፈወሰ፣ አጋንንት እያባረረ፣ ሙት እያነሳ፣ ዕውራንን እያበራ ብዙ ተአምራትን አደረገ፡፡ስለዚህም በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ንግሥት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው፡፡
ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ በአስቀመጠው ጊዜ የኢየሩሳሌም ምእመናን የሮማውን ንጉሥ ሕርይቃልን ዕርዳታ በመጠየቅ እንዲመለስ አድርጉ፡፡ በኢየሩሳሌምም ብዙ ዘመን ሲኖር እንደገና ኃያላን ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ ‹እወስድ እኔ እወስድ› እያሉ ጠብ ፈጠሩ፡፡
በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም፣ የቁስጥንጥንያ፣ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣ የእስክንድርያ እና ከመሳሰሉት ሀገሮች የተሰበሰቡ የሃይማኖት መሪዎች እርቅ አወረዱ:: ከዚህም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የጌታችን ኢየሱስን ግማደ መስቀል ከ፬ ከፍለው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎቹ ታሪካዊ ንዋያት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪካ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡
ግማደ መስቀሉም ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖር በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው እየጠነከረ ሔደ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊ ዓፄ ዳዊት እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ፤ ‹‹ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግሥልን ብለው ጠየቁት፡፡›› ዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶአቸው ፳ ሽህ ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብጽ ዘመቱ፡፡ በዚህ ጊዜ በግብጽ ያሉ ኃያላን ፈሩ፤ ተሸበሩ፤ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልእክት ለእስላሞች ላኩ፤ ‹‹በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋዋለሁ፡፡›› የንጉሡ መልእክት ለእስላሞች እንደደረሳቸው ፈርተው እንደጥንቱ በየሃይማኖታቸው ጸንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡
መታረቃቸውን ዳግማዊ ዳዊት ሰሙ፤ በዚህም ጉዳይ ንጉሡ በጣም ደስ አላቸው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው፡፡ ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልከተው ደስ አላቸው፤ ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፡፡
‹‹በግብጽ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ፤ እንኳን ደስ አላችሁ! የላካችሁልኝን ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፤ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም፡፡ የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ፡፡ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ በኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው፡፡››
በእስክንድርያም ያሉ ምእመናን ይህ መልእክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ ‹‹ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅድሳት ጋር አሁን በመለሰው ፲፪ ወቄት፣ ወርቅ የብርና የንሐስ፣ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት›› ብለው ከተስማሙ በኋላ በክብር በሥነ ሥርዓት፣ በሠረገላና በግመል አስጭነው፣ ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቡአቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ፣ እያሸበሸቡ እና በግንባራቸው እየሰገዱ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ ይህም የሆነው መስከረም ፳፩ ቀን ነው፤ በኢትዮጵያም ታላቅ ብርሃን ሌት ተቀን ፫ ቀን ሙሉ ሲበራ ሰነበተ፡፡
ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓፄ ዳዊት ስናር ላይ ዐረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ እንደነገሡ ወደ ስናር በመሄድ ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅድሳት ጋር አመጡት፡፡ በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲጥሩ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ ወዳጄ ዘርዐ ያዕቆብ ሆይ! መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ›› የሚል መልእክት በራእይ ተነገራቸው፡፡ ንጉሡም በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ መስቀለኛ ቦታ በመፈለግ ከብዙ ቦታ ላይ አስቀምጠውት ነበር፡፡ ለምሳሌ በሸዋ በደርሄ ማርያም፣ በመናገሻ ማርያምና በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታ ያላገኙ በመሆኑ በራእይ እየደጋገመ ‹‹መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ›› እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡
ዓፄ ዘርዐ ያዕቆብም ለ፯ ቀናት ያህል ሱባዔ ገቡ፤ በዚያም ‹‹መስቀልኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምድ ብርሃን ይመጣል›› የሚል መልእክት ደረሳቸው፡፡ እርሳቸው ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ ዓምደ ብርሃን ከፊታቸው መጥቶ ቆመ፤ ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል ስፍራም መርቶ አደረሳቸው፡፡ በርግጥም ይህች ግሽን የተባለች አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረፃት የተዋበችና መስቀልኛ ቦታ ሁና ስለአገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው፡፡ በዚያችም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው፤ ዘመኑም በ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመን ነበር፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን፤ አሜን !!!
ምንጭ፤ መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መምህር አፈወርቅ ተክሌ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መስከረም
ወስብሐት ለእግዚአብሔር