‹‹ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር›› (ኢሳ. ፩፥፲፰)
መምህር ጳውሎስ መልክዐሥለሴ
በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ተጎሳቁለው ለእግዚአብሔር ባልተመቻቸ ስፍራ በመቆማቸው ምክንያት የደረሰባቸውን በደል መቋቋም ላቃታቸው እስራኤላውያን ከኃጢአት የሚያነጻው፥ የሚያጠራው እና ከሰይጣን ባርነት ነጻ የሚያወጣው እግዚአብሔር እንደሆነ ነቢዩ ኢሳያስ ነገራቸው፡፡ ለደረሰባቸው የጸጋ መገፈፍ እና የሕይወት መጎስቆል ሁሉ መፍትሔያቸው እግዚአብሔር መሆኑንም አሳወቃቸው፡፡ (ኢሳ. ፩፥፲፰)
ብዙ ጊዜ በሕይወት በሚገጥመን ፈተናና ችግር ምክንያት ራሳችንን በመመርመር እግዚአብሔርን መማጸንን የመሰለ መፍትሔ ወይም የድኅነት መንገድ የለም፡፡ እስራኤል ከእግዚአብሔር ርቀው፤ ወደ ቃሉ መጠጋት በአቃታቸው ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ የመጣባቸው መቅሠፍት የኃጢአታቸው ውጤት ስለነበረ እግዚአብሔር አጥቦ ቅዱሳን ልጆቹ ሊያደርጋቸው የተዘጋጀ አባት በመሆኑ ‹‹ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር›› አላቸው፡፡ (ኢሳ. ፩፥፲፰)
የሰው ልጅ በሕይወት ጎዳና ውስጥ ከፍተኛ የኃጢአት አዘቅት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚወድቀው እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ሳይረዳ ሲቀር ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቸርነት የተረዳ ሰው ኃጢአት ቢሠራ እንኳን እርሱ መሓሪ መሆኑን አውቆ ለንስሓ ወደ ፈጣሪው ይጠጋል፡፡ እስራኤል ግን ይህን ስላልተረዱ ሸሹ፤ እነርሱንም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደአለላ ብትሆን እንደአመዳይ ትጸዳለች፤ እንደደምም ብትቀላ እንደባዘቶ ትጠራለች፤›› በደጅ ለሚንከራተቱት እና ጎዳና በመከራ ለሚንከላወሱት አባት ሊሆናቸው እነርሱም ልጆች ይሆኑት ዘንድ እግዚአብሔር እንደጠራቸው አሳወቃቸው፤ እግዚአብሔር ያነጻው እና ያጠበው ብቻ ይነጻልና፡፡ (ኢሳ. ፩፥፲፰)
የሰው ልጅ ለመንፈሳዊ ንጽሕና በእግዚአብሔር ሊታጠብ ያስፈልጋል፤ እግዚአብሔር ካላጠበው ሰው ሕይወት የለውም፡፡ በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታ በሐዲስ ኪዳን የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ስለ ትሕትናው ‹‹ጌታ ሆይ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?›› አለው፤ ጌታ ግን መልሶ ካላጠብህሁ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም፤›› አለው፡፡ (ዮሐ. ፲፫፥፮-፱)
ቅዱስ ዳዊት በኃጢአት ጎስቁሎና አድፎ ‹‹በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ›› ብሎ እንደጸለየው በኃጢአት ያደፍን ወገኖች ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያጠራን ራሳችንን ያለመፍራት ወደ እርሱ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ እስራኤል ከእነ እድፋቸው ሲመላለሱ ኃጢአት አለብኝ ብለው መሸሽ ትክክል እንዳልሆነ፤ እግዚአብሔርም ከኃጢአት እንዲያነጻቸው ይቀርቡት ዘንድ አስተማራቸው፡፡ ሰዎች በኃጢአታቸው ተጸጽተው ከተመለሱ ወደ አምላካቸው መቅረብ እንጂ መሸሽ የለባቸው፡፡ እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላችሁ ብሏቸዋል፡፡ (መዝ. ፶፥፯፤ኢሳ. ፩፥፲፱)
የሰው ልጅ የመንፈሳዊ ሕይወት ስኬት ለእግዚአብሔር፣ ለሕጉም ከመታዘዝ ይጀምራል፡፡ እሺ ማለት፣ መታዘዝ እና ራስን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የሚገዛን ቸር አምላክ ነው፤ የፍቅር አባት በመሆኑ እርሱ ሲገዛን ጥሩ ልጆች እንሆናለን፤ እግዚብአሔር ሲመራን በእውነት መንገድ እንጓዛለን፡፡ እራሳችንን ለእርሱም የምናስገዛው እግዚአብሔርን ስናውቀው ነው፤ ክርስቲያኖች ፈጣሪያችንን ማወቅ አለብን፡፡ ክርስትናም ማመን፣ መታዘዝ፣ መገዛትና መጽደቅ፣ ለሰማያዊ ርስት፣ ለማያልፍ፣ ለማያልቅ፣ ለማያረጅ እና ለልጅነት በረከት መዘጋጀት ነው፡፡ ልባችን ለእግዚአብሔር የምናስገዛው ሁለንተናችን በፍቅር ሲነካ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሕይወት ጽልመት፣ ከኑሮ ጭጋግ እና ከሰብእና ውድቀት ሊጠብቀን ሲሻ ‹‹ልጄ ሆይ÷ ልብህን ስጠኝ÷ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ፤›› አለን፡፡ ልብ የሰውነታችን መሪ፤ ከአካል ክፍላችን ሁሉ በላይ ነውና፡፡ ሰው ዓይኑ ቢጠፋ በሕይወቱ ይኖራል፤ የልባችን መሥራት ካቆመ ግን ይሞታል፡፡ (ምሳ. ፳፫፥፳፮)
‹‹ልባችሁን ስጡኝ›› እንጂ ዓይናችሁን፣ እጃችሁን፣ እግራችሁን ወይንም ሌላ አካላችሁን ስጡኝ›› አላለም፡፡ ዋናውን አካላችንን እንድንሰጠው እና እርሱ ኃይል እንደሚሆነን ነገረን፤ እስራኤላውያን በተመሰቃቀለ መንገድ ላይ በመሆናቸው ሳቢያ በመቅሠፍት መመታታቸው ልባቸውን ስላልሰጡት እንደሆነ ነገራቸው፡፡ በችግር መደቆሳቸው፣ ጦርነት እና በሽታም ያጠቃቸው ልባቸውን ለእርሱ ባለመስጠታቸው መሆኑን አስረዳቸው፡፡
ዛሬም ሀገር በሰላም የምትተዳደረው ሰዎች ልባቸውን ለእግዚአብሔር ሲሰጡ ነው፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቅ፤ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ያለው ሰው ሁለንተናውን ሊሰጥ ይገባል፤ የሰው ልጅ ሕይወቱን ለፈጣሪው ሲሰጥ ድኅነትን ያገኛል፤ ይባረካልም፡፡ ካላንበት የኑሮ አዘቅት ውስጥ ስቦ የሚያወጣን እግዚአብሔር ልባችንን ስንሰጠው እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ፈጣሪያችን ሲመራን አንሰናከልም፤ አንሰበርም፤ አንታመምም፡፡ በእርሱ ዘንድ የማይጨልምበት ጌታ በድቅድቅ ጨለማ ወስጥ ብርሃን ይሆነናል፤ እግዚአብሔርን የምትወድ ነፍስ በብርሃን ትጓዛለች፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም ሁል ጊዜ ከአንተ ጋር ይኖራል፤ እንደ ነፍስህም ፍላጎት ያጠግብሃል፤ አጥንትህንም ያለመልማል፡፡ አንተም እንደሚጠጣ ገነት÷ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ›› እንዲል፡፡ (ኢሳ. ፶፰፥፲፩)
እግዚአብሔር የሚመራን ከሆነ ሀገር በበረከት ሕዝብ በታዛዥነት ይጓዛል፤ ከመሪ ጀምሮ እስከ ተመሪ ለፈጣሪ መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በቤታችን ሀብት ብናገኝም ጤና እናጣለን፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የለምና፤ በሰላም ውለን የምናድረው እርሱ ሲፈቅድ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ሀብቱ ቅዠት፤ ዕውቀቱ እብደት፤ ንግዳችን ኪሳራ ይሆናል፡፡
እግዚአብሔር የለም ብለው የሚያምኑ ሰዎችንም እንደ ምሁር መቁጠር ጀምረናል፤ ‹‹እርሱ እኮ ወጣ ያለነው እንላለን፤›› በእርግጥ የወጣ ነው፤ ከሕይወት ጎዳና የወጣ፣ ወደ ሞት ቁልቁለት የወረደ ማለት ነው፡፡ የክሕደት መርዛቸውን እየረጩ ብዙ ተማሪዎችን ሳይጨርሱ እንዲወድቁ ያደረጉ መምህራን አሉ፡፡ ዕውቀትና እድገት ይገኝበታል የተባሉ ትምህርት ቤቶች ዛሬ የዝሙት፣ የሴሰኝነት እና የርኩሰት መናኀሪያዎች ሆነዋል፡፡ ክፋት የሌለባቸውን ሕፃናት ከአቅማቸው በላይ ለሆነ ሐሳብ እየዳረግናቸው እንገኛለን፡፡
ከሕፃንነት ጀምሮ የመራንን አባት በእምነት እንከተለው፤ ጌታ ሆይ ከአማልክት መካከል እንዳንተ ያለ ማነው፤ አንተ ፈጠርከን፤ ስለወደድከን አሳደከን፤ ልጅህ አድርገህ አከበርከን፤ በመንፈስ ቅዱስ የምትመራን አንተ ነህ፤ ኑሮአችን፣ ሥራአችን፣ ትዳራችን በአንተ ይሁን፤ እንቅስቃሴያችን፣ ንግግራችን፣ ልባችንና ሁለንተናዊ ማንነታችን ለአንተ ይሁን፤ አንተን የሚመስል የለም እንበለው፡፡
በማጣት፣ በማግኘት፣ በመራብም፣ በመጥገብም፣ በማትረፍም፣ በመክሰርም፣ በመሾምም፣ በመሻርም፣ ክርስቲያን ተመስገን ማለት አለበት፡፡ምድራዊ ሕይወታችን የምንማርበት እንጂ የምናማርርበት ሊሆን አይገባም፤ ‹‹እግዚአብሔር ሊያስተምረኝ ፈልጎ ነው›› ብለን ተመስገን ማለት አለብን፡፡
ክርስቲያን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበደላችን ነጻ ሊያደርገን ሰው የሆነ፤ ለክብራችን የተዋረደ፤ ወድቆ ያነሳን፤ ታሞ የፈወሰን አባት እንደሆነም መዘንጋት የለበትም፡፡ በአኗኗራችን አንሰን፣ በበሽታ ተጎድተን፣ በሕይወት ጎስቁለን ብንኖርም ሕመማችንን የሚፈውስልን አባት እግዚአብሔር ‹‹ኑ›› ይለናልና ወደ እርሱ እንቅረብ፡፡
በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ እሺ ብሎ መታዘዝ ሰዎችን ለክብር ያበቃል፤ እንቢ ያልን ሰዎች ካለን ዛሬ እሺ በማለት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ፤ ዘወትር ለእኛ የሚያስብልን ጌታ፣ የማይተወን ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡