ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

በሕይወት ሳልለው

በሸዋ ቡልጋ ክፍለ ሀገር ጌዬ በተባለ አካባቢ የተወለደችው ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አባቷ ደረሳኒ እና እናቷ ዕሌኒ በእግዚአብሔር ፊት የታመኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ ልጃቸውን የቤተክርስቲያን ሥርዓት፤ የብሉይና የሐዲስ ኪዳንን መጻሕፍት በማስተማር አሳደጓት፡፡ ዕድሜዋ ለአቅመ ሔዋን ሲደርስ ወላጆቿ የኢየሱስ ሞዓ ልጅ የሆነውን ሠምረ ጊዮርጊስን አጋቧት፤ ዐሥር ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች፤ እርሷም ልጆቿን በሥርዓትና በሕገ እግዚአብሔር አሳደገቻቸው፡፡

በዚያ ዘመን የነበረው ንጉሥ ዓፄ ገብረ መስቀል ደግ ሰው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ንጉሡ ስለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ቁንጅናና ደግነት በሰማበት ወቅት በግዛቱ ከተደነቁት ፻፸፬ ሴቶች መካከል አንዷ ስለነበረች ስለእርሷ ዝና አወቀ፡፡ ንጉሡም ያገለግሏት ዘንድ ፪፻፸፪ ያህል ብላቴናዎችን ላከላት፡፡ ነገር ግን ይህ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆን ወደ እግዚአብሔር ባመለከተች ጊዜ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በራዕይ ተገልጾላት፡፡ «ሰላም ላንቺ ይሁን የተወደድሽ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ፤ የእግዚአብሔር ቸርነት የሆነውን የሰማይ ኅብስትም ተመገቢ» ብሎም መገባት፡፡ በውስጧም መንፈስ ቅዱስ መላባት፤ ፈጣሪዋን አመሰገነች፤ ከንጉሡ የተላኩላትንም አገልጋዮች አስተባብራ ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዛት በስሙ ቤተክርስቲያን አሠራች፡፡ የመልአኩን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት በዚያ ስታገለግልና ስታስገለግል ኖረች፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ከአገልጋዮቿ አንዷ ላይ ርኩስ መንፈስ አደረ፤ አልታዘዝም ማለትም ጀመረች፡፡ ይህን ጊዜ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደጋግማ መከረቻት፤ ያቺ ብላቴና ግን ልትመከር አልቻለችም፤ በዚህም ሳቢያ ክፉኛ ብታዝንባት ብላቴናዋ ሞተች፡፡ እጅጉን ያዘነችው እናታችን «ይህማ የነፍስ ግድያ ይሆንብኛል» ብላ አምርራ አለቀሰች፤ ወደ እግዚአብሔር በጸለየች ጊዜ ፈጣሪ አገልጋይቱን ከሞት አስነሳላት፡፡ ውስጧም በሐሴት ተሞላ፤ እንዲህም አለች «በዓለማዊ ሕይወት ውስጥ ስኖር ይህን ተአምር ካደረገልኝ በምናኔ ሕይወት ብኖር ደግሞ ምን ያህል ድንቅ ሥራ ያደርግልኛል፤» ብላ ባለቤቷንና ልጆቿን እንዲሁም ወላጆቿን ትታ መነኮሰች፡፡ ነገር ግን የመጨረሻው ልጇን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በገባች ጊዜ አብራ ይዛው ሔደች፡፡ የአካባቢው ሰዎች ከሩቅ ቦታ እንደመጣች አውቀው አስጠጓት፤ እርሷም ልጇን በዚያው አስቀመጣ በገዳሙ ውስጥ በጸሎት፤ በጾምና በስግደት ስትተጋም ቆየች፡፡ ልጇ ግን እናቱን ባጣ ጊዜ አለቀሰ፤ተራበም፡፡ በደጃፉ ስታለፍ የነበረች አንዲት ሴት ልጁን ተጠግታ ልታነሳው ብትሞክር ቅዱስ ሚካኤል ፈጥኖ ደርሶ ነጥቆ ወሰደው፤ ወደ ገነትም አስገባው፡፡ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራም ወደ ልጇ በተመለሰች ጊዜ ሞቶ አገኘችው፡፡ መሪር ኃዘንም አዘነች፤ ይህን ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾ ልጇ በገነት እንዳለ ነግሮ አጽናናት፡፡ ወደ ጣና ባሕርም መርቶ ወሰዳት፤ በዚያም ለ፲፪ ዓመት በባሕር ውስጥ ገብታ ሰውነቷ ተበሳስቶ ዓሣዎች በውስጧ እስኪያልፉ ድረስ ቆማ ጸለየች፤ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾ ቃልኪዳን ሰጣት፤ ፲ አክሊላትም ወረዱላት፡፡ በጸሎትና በስግደትም መትጋት በቀጠለችበት ወቅት ቅዱስ ሚካኤልን፣ ቅዱስ ገብርኤልን፣ ቅዱስ ሩፋኤልንና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም ረዳት እንዲሆኗት ጌታችን ፈቀደላት።

እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ደግና ርኅሩኅ ነበረችና ጌታን እንዲህ ብላ ለመነችው «አቤቱ ፈጣሪዬ እኔን ባሪያህን ከክፉ ነገር ሁሉ ሠውረኸኛልና ዲያብሎስን ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡ ይኸውም ስለ አዳምና ስለ ልጆቹ በጠቅላላውም ስለ ሰብአ ዓለም ሥጋቸው ሥጋዬ ስለሆነ እንዳያስታቸው ክፉ ሥራ እንዳያሠራቸው ብዬ ነው ማርልኝ ማለቴ» አለችው፡፡ ጌታችንም «ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዕፁብ ድንቅ ልመና ለመንሽኝ! ሌሎች በኋላሽም የነበሩ በፊትሽም የሚመጡ ያልለመኑትን ልመና ለመንሽኝ» አላት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልንም ወደ ዲያብሎስ እንዲወስዳት አዘዘው፡፡

ሲኦል ሲደርሱ ምሕረትን የሚሻ ከሆነ እንድትጠይቀው ቅዱስ ሚካኤል ባዘዛት ጊዜ፤ «ሳጥናኤል» ብላ ጠራቸው፡፡ ዲያብሎስም መልሶ ሳጥናኤል ብሎ የጠራኝ ማን ነው? አለ፡፡ እርሷም «እኔ ነኝ» አለችው፡፡ ወደ እኔ ለምን መጣሽ ሲላት  «ከፈጣሪህ ጋር አስታርቅህ ብየ» አለችው፡፡ እርሱም አንቺን ከቤትሽ ከንብረትሽ ሳለሽ አስትሻለሁ ብየ ብመጣ ያጣሁሽ ሰው እኔን ልታስታርቂኝ መጣሽ? ግን ይህን ያደረገ ያ የቀድሞው ጠላቴ ሚካኤል ነው፤ ሲጻረረኝ የሚኖር ከክብሬም ያወረደኝ እሱ ነው እንጂ አንቺ ምን ጉልበት አለሽ ብሎ እጇን ይዞ ወደ ሲኦል ወረወራት፡፡

በዚያች ቅጽበት ቅዱስ ሚካኤል ሲኦልን በሰይፉ መታው፤ ተከፈተም፤ በውስጡም ብዙ ነፍሳት እርስ በርስ ሲነባበሩ አየች፤ ነፍሷም ታበራ ስለነበር ፲ ሺህ ያህል ነፍሳት መጥተው በላይዋ ሰፈሩባት፤ ከሲኦልም ይዛቸው ወጣች፤ እነዚያን ነፍሳት የማረላትንም ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡

ጌታችን ኢየሱስም ለእናታችን ክርስቶስ ሠምራ ማረፊያዋ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስተቀኝ እንደሚሆን እና ስሟም ከእንግዲህ በኋላ በትረ ማርያም ተብሎ እንደሚጠራ ነገራት፡፡ እመቤታችንም ተገልጻ «ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ፤ አንቺን የወለደች ማሕፀን የተባረከች ናት፤ አንቺንም አጥብተው ያሳደጉ ጡቶች የተባረኩ ናቸው፡፡ አንቺንም ያዩ ዐይኖች የተባረኩ የተቀደሱ ናቸው፤ አንቺንም የሚያመሰግኑ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፤ያንቺን ገድል የሚሰሙ፤ የሚያሰሙ የተባረኩ ናቸው»፤ አለቻት፡፡

ከዚህ በኋላ ሥጋዋ ከነፍሷ ተዋሕዶ ወደ መሬት ተመለሰች፤ በቁመቷ ልክ ጉድጓድ አስቆፍራ፤ በዙሪያዋ ጦሮችን አስተከለች፤ ይህም ወደፊትና ወደኋላ በምትልበት ጊዜ እንዲወጋት ነበር፤ ለ፲፪ ዓመትም እየሰገደች ኖረች፡፡

ጌታችንም እንዲህ አላት፤«አንቺን የሚወዱ፤ ስምሽን የሚጠሩ፤ ዝክርሽን የዘከሩና በዓልሽን ያከበሩ እስከ ፲፪ ትውልድ እምርልሻለሁ»፡፡ በመጨረሻም ነሐሴ ፳፬ ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታ መላእክት አሳረጓት፤ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የከበረ ዐፅም ጌዬ የተባለ ገዳም ውስጥ ተቀምጧል፤ ይህም ገዳም እርሷን መዘከርና መማጸን ለሚሹ ምእመናን የተሠራ ነው፡፡

ምንጭ፡- ገድለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ፤ ነገረ ቅዱሳን ቁጥር ፪ እና ዝክረ ቅዱሳን