አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውና መዘረፋቸው ተገለጸ
በሕይወት ሳልለው
በሲዳማ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት በሁላ ወረዳ ቤተክህነት ሥር ወይም በሁላና ቦና ዙሪያ ወረዳ ፫ አብያተ ክርስቲያናት በጥፋት ኃይሎች መቃጠላቸውና ፪ቱ ደግሞ መዘረፋቸው ተገለጸ፡፡ከሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በቆየው የሲዳማ ዞን ክልል ይሁንልን ጥያቄ ረብሻ ለአብያተ ቤተ ክርስቲያናት መቃጠልና መዘረፍ መንስኤ መሆኑም ተገልጿል፡፡
መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ፤ የሲዳማ፤ጌዴኦ፤አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ «ሀገረ ስብከቱ ከወረዳ ቤተክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ጥበቃቸውን እንዲያጠናክሩና ምእመናንም ተደራጅተው ራሳቸውንና አብያተ ክርስቲያናትን እየጠበቁና እንዲከላከሉ መልእክት የተላለፈ ቢሆንም የጥፋት ኃይሎቹ ከአካባቢው የፀጥታ ኃይልና ከምእመናን አቅም በላይ በመሆናቸው የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ ችለዋል» በማለት አስረድተዋል፡፡የደረሰው ቃጠሎ በመጀመሪያ በዶያ ቅዱስ ሚካኤል የ፲፰ አባወራዎችን ንብረት በማጥፋት፤ ፸፪ ንዋያተ ቅዱሳትን ሙሉ በሙሉ በእሳት አውድሟል፡፡ ቤተክርስቲያኗን ለማትረፍ ሲረባረቡ የነበሩትን ፲ ሰዎችም አደጋ እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በ፳፻፰ ዓ.ም. ተመሥርቶ ከኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጋታማ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ጥፋት ኃይሎች በእሳት ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሏል፡፡ ፵፫ አባወራዎች ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲቃጠል፤ በአይነት ፵፯ የሚሆኑ ንዋያተ ቅድሳት ሙሉ በሙሉ በእሳት ተቃጥለዋል፡፡
፵፫ የሚሆኑ አባወራዎች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በየሰው ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሉዳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የውስጥ ንዋያተ ቅድሳት በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ በር፤መስኮት እና መንበር ሲሰባበር፤ደጀ ሰላሙ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጽሙ በነበሩ ምእመናን ላይም የሀብት ዝርፊያ በቤታቸው ተካሔዷል፡፡ አቶ ሽፈራው ማሞ በተባሉት አባት ከፍተኛ የአካል ጉዳትም እንደደረሰ ምንጮች አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡
የጭሮኔ ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ሕጉ እስከ አሁን ያለበት ቦታ አልታወቀም፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንና ንዋያተ ቅዱሳቱን ያቃጠሉት ግለሰቦች የካህናትን ልብሰ ተክህኖና የሰንበት ተማሪዎች አልባሳትን ለብሰው፤ ቆብ አጥልቀውና መስቀል ይዘው በመዞር ከጨፈሩ በኋላ ተመልሰው ቤተ ክርስቲያኗን ማቃጠላቸውን የዐይን እማኞች አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በ፲፱፻፱ የተመሠረተው የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ደግሞ በደረሰው ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ተዘርፏል፡፡ አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ መቃብር ቤቶች በርና መስኮቶች ተሰባብሯል፡፡
ሦስት ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔት ተገድለዋል፡፡ ፪፻፶ ምእመናን ተሰደው ቦሬ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው ይገኛሉ፡፡በተፈጠረው ችግር የ፹፭ ዓመቱ አቶ ግርማ መልካ መንገድ ላይ ተገድለው ሲገኙ፤አቶ የኔነህ ተስፋዬ መገደላቸውን፤ እና ወጣት አድሱ የኔነህ ደግሞ አባቱን እያሳከመ እንዳለ መገደሉን ተገልጿል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ ሀገረ ስብከቱ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር በአካባቢው ላይ የነበሩትን ምእመናን ለመታደግ ችሏል፡፡ የተጎዱ ምእመናንን ለመደገፍና የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ ለማቋቋም ኮሚቴ መቋቋሙን የሐዋሳ ማእከል ገልጿል፡፡
በመሆኑም የኮሚቴው አባላት በጥፋቱ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት መረጃ በመሰብሰብ፣ ምእመናንን በማጽናናትና ከሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ድጋፍ በማሰባሰብ ተጎጂዎችን እየረዱ እንደሆነ ሀገረ ስብከቱ ገልጿል፤ ይበልጥ ለመደገፍ በባንክ አካውንት ቁጥር 1000290647936፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ከፍቶ ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡