«ዕረፍተ ኅሊና»
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
እውነተኛ ዕረፍት በጎ ኅሊና ነው፤ ይውም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ዘላለማዊ ዕረፍት ነው፤ክርስቲያን ዕረፍትን ለመፈለግ ሲል መከራ ሸሽቶ አይሔድም።ይልቁንም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብሎ በሚደክመው ድካም ውስጥ እጅጉን ይደሰታል።በዚህ ወደ አምላኩ በሚወስደው መንገድ በመጓዝ በሚገጥመው ፈታኝ ጉዞ በሚደርስበት ሥጋዊ ድካም ውስጥ መንፈሳዊ ደስታ ያለበትን ምቾትን ያገኛል። ለዚህ ነው (ሲራክ ፮፥፳፫) ላይ «ልጄ ሆይ ስማኝ፤ በምክሬም ጽና፤ ምክሬን አታቃልል፡፡ እግሮችህን ወደ ቀንበርዋ አግባ፤ ዛንጅርዋንም ባንገትህ እሰር፡፡ጫንቃህን ዝቅ አድርገህ ተሸከማት። በእግር ብረትዋ አትበሳጭ፡፡ በፍጹም ነፍስህም ወደ እርሷ ተሰማራ፤ በፍጹም ኃይልህ መንገዷን ጠብቅ፤ ፍለጋዋንም ተከተል፤ ፈልጋት፤ ታገኛታለህም፤ በፍጻሜህም ዕረፍትን ታገኛለህ፤ደስታም ይሆንሃል»።
የዳኞችን ፍርድ በገንዘብ ማስለወጥ ይቻላል፤ ኅሊና ግን ከዚህ ልዩ ነው፡፡ ማንንም የማይገባውን ቅጣት ቀጥቶ አያውቅም፤ አስፈጻሚዎቹ እጅና እግር እና ሌሎች አካሎቻችን ፍርዱን ስለሚያበላሹበት ከኅሊና ፈቃድ ውጪ አይንቀሳቀሱም፡፡ ኅሊናው ሁልጊዜ በሰው ላይ እንጅ በራሱ አልፈርድለት ካለ ይህ ሰው እንስሳ ሆኗል ማለት ነው፤ (መዝ. ፵፰÷፳)፡፡ «ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቅም፤ልብ እንደሌላቸው እንስሳትም ሆነ፤መሰላቸውም» ብሎናል፤ ቅዱስ ዳዊት ዕራቁቱን የሚሄደው ሰው መብዛቱ፤ ቅጥ የሌለው ኑሮ በብዙዎቹ ዘንድ እየተለመደ መምጣቱም የዚህ ምልክት ነው፡፡
የኑሮ ውድነት ዘወትር ሲወራ የኅሊና ዋጋ ክርስትና ከሆነ በብር ለምን ይለካል? የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ምግብ የሚያቀርብ ድርጅት ተመሠረተ፤ የኅሊና ዕረፍት ላጡ እና ሕሊናቸውን ሸጠው ሰውነታቸው መቃብር ለሆነባቸው ሰዎችስ ምን ይደረግ ትላላችሁ? እኔ ግን አንድ ነገር እላችኋለሁ፤ የአምላካችን ቅዱስ ቃል መቃብራትን ይከፍታል፡፡ መቃብር የሆነ ልቡናችሁን ይከፍት ዘንድ ቅረቡ፤ (ማቴ ፳፯፥፶፪)«መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተው ከነበሩ ከቅዱሳን በድኖችም ብዙዎች ተነሡ፤ ይለናል” የሰው ልጅ በዓላማው፣ በአመለካከቱ፣ በመረዳት ችሎታው፣ በአኗኗር ዘይቤው፣ እንደሚለያይ ሁሉ በዓለም ሲኖር የሚገጥሙትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ችግሮች የመቋቋምና በትክክለኛ መንገድ የመጓዝ ችሎታውም ይለያያል፡፡ ሰዎች ለነገሮች የሚኖራቸው እይታ የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዱ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ቀለል አድርጎ ሲመለከታቸው ሌላው ደግሞ በጣም አክብዶና አጋኖ ሊመለከታቸው ይችላል፡፡ ሁለት ሰዎች አንድን ተመሳሳይ ክስተት የሚመለከቱበት ወይም የሚረዱበት መንገድ እንደሚለያይ ሁሉ የሚፈቱበት መንገድም ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸው ሁለት ሰዎች ከሥራ ቢሰናበቱ አንደኛው መታገሥን መርጦ የነገን ሲያልም ሌላኛው ግን ጨለማ ውስጥ እንደገባ መሥሎ ሊታየው ይችላል፡፡የአእምሮ ውጥረትን የመቋቋም ችሎታ በአጭር ጊዜ የሚመጣ ክሂሎት ሳይሆን በረጅም ጊዜ ልምምድ የሚመጣ ክሂሎት ነው፡፡
በኤልያስ ዘመን ፫ ዓመት ከመንፈቅ ሰማይ የነጠፈው ምድርም የተራቆተው (፩ ነገ.፲፯፥፩)፤ በሌላም ጊዜ ውሃን በማዝነም ፈንታ እሳትን እና ዲንን ያዘነመው (ዘፍ.፲፱፥፳፬፣፪፣፳፩፥፲፪)፤ በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን በለኪሶን ሜዳ በአንድ ሌሊት አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሽህ ሬሳ የተገኘው(ኢሳ.፵፯፥፵፮) በሞዓብ ሜዳ ከነበረው ሕዝብ መካከል ፳፫ ሺህ ሬሳ በአንድ ቀን የተገኘው (፩ ቆሮ.፲፥፰) የሰው ልጅ ድንበር በማፍረሱም አይደል?
ዛሬስ ምድር በሰቆቃ የተሞላች መሆን፤ ለዓለማችን ፈውስ በሌለው ቁስል መመታትና በረከት ማጣት ተጠያቂው ማን ይሆን? ምን አልባት በአእምሮአችን ሌላ መልስ አስቀምጠን ይሆናል እንጅ ክፉውም ሆነ ደጉ ነገር የሥራችን ውጤት ነው፡፡ የፈርኦን ባሪያዎች በግብፅ ለተቃጣው መቅሠፍት ሁልጊዜ ተጠያቂ የሚያደርጉት ሙሴን ነበር እንጅ አንድም ቀን ይህ የኃጢአታችን ደምወዝ ነው ብለው አያውቁም(ዘፀ.፲፥፯)
ዛሬም ያለው ትውልድ ለአየር ንብረት መዛባት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራትን ለታናናሽ ሀገራት የጦርነት ቀጠና መሆን፤ ኃያላን መንግሥታት ለድኃ ሀገራት አለመበልጸግ ቅኝ ገዥዎችን ምክንያት ማድረግ ልማዱ ነው(የእኛ ለእነርሱ የክፋት ድርጊት ራሳችንን አመቻችተን ማቅረባችንን አናስተውልም)፡፡ የሆነብንን ሁሉ እንደ ነቢይ አምነን ለምንቀበል ሰዎች ስለ ኃጢአታችንና ስለ በደላችን ይህ ሁሉ ሆነ ሳለ ያለ ሕግ የሚበድሉ ሁልጊዜም ያለሕግ ይቀጣሉና(ዳን. ፱፥፲፮-፲፯)፤
ይህን ገጽታውን በግልባጩ የተመለከትነው እንደሆነ ደግሞ ምድረ በዳ የሌለው የአጋንንት ማረፊያ ነው፤ (ማቴ. ፲፪፥፵፫) በጾም እና በጸሎት ከሰው ልጆች እንዲወጡ የተገደዱ አጋንንት ወደ ምድረ በዳው ይሰማራሉ፤ ማረፊያ የሌለው በመሆኑ ግን ተመልሰው ወደ መጡበት ቤት ይገባሉ፡፡ በእርግጥ አሁንም የሚሸጋገሩት ከምድረ በዳ ባዶ ወደሆነ ቤት ነው፡፡ ይህ ለእነርሱ ምቹና ባዶም በመሆኑ አጋንንት ያድሩበታል፡፡ የሥጋ ፍሬን ብቻ ስለሚያፈሩ የመንፈስ ፍሬን ረስተውታልና ስለዚህ ያድሩበታል፡፡ ሰው በገዛ ፈቃዱ ሕይወትን ትቶ የኮበለለ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን በሞት ወደ ተቀጣው የሰው ልጅ መጣ፡፡ የደከመውን የሰው ልጆች ባሕርይ ሊያበረታ መንገድ ከመሔድ ደክሞ ሊያርፍ ተቀመጠ ፤ ድካም ሳይኖርበት የሚታየውን እና የማይታየውን ዓለም የፈጠረ አምላክ ዛሬ ግን አዳምን ሊያድነው ወዶ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ለባሕርዩ የማይስማሙ ድካምና ሕማም የቃል ገንዘቦች ሆነው ተነገሩ፡፡«ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ» (ዮሐ.፬፥፮) ተብሎ ለኃያሉ አምላክ ሲነገርለት እንደምን ይገርማል፡፡ መላእክትን ያለ ዕረፍት ሌሊት እና ቀን እንዲያገለግሉ ኃይል የሆናቸው ጌታ እኮ ነው (ራዕ.፬፥፰) ዛሬ ግን ደከመ፤ በእርሱ ድካም ፍጥረት እንዲበረታ ይህ ሁሉ ሆነ፡፡ ያውም ጊዜው ቀትር ነበር፤ የሚያቃጥል ፍጥረት ሁሉ ጥግ ፍለጋ እንዲሸጐጥ የሚያደርግ አስቸጋሪ ሰዓት!ማንም ሰው በኃጢአቱ እንዲሞት የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። (ሕዝ. ፲፰፥፴፪)
ክርስቲያን በእምነት ሕይወት ውስጥ ዕረፍትን ያገኛል እንዳለን ነቢዩ ኤርምያስ ፮፥፲፮ ላይ «በመንገድ ላይ ቁሙ፤ ተመልከቱ፤ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ፤በእርሷም ላይ ሒዱ፤ ለነፍሳችሁ ዕረፍትን ታገኛላችሁ»። እንዳለ እውነተኛ ዕረፍት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ስለሆነ እኛም ወደ እርሱ በመቅረብ የማያቋርጥ ዕረፍትን እናገኛለን፡፡ እንዲሁም ለምናከናውነው ሥራ ሁሉ ስልቹ አንሆንም፤ ምክንያቱም የምናመልከው አምላክ ዘለዓማዊ ዕረፍትን ስለሚሰጠን ሥራን ሙሉ ለሙሉ በማቆም ማረፍ ሳይሆን መሰላቸትን በማቆም መንፈሳዊ ሥራንና ማኅበራዊ በጎ ሥራ በማከናወን ማረፍ ማለት ነው።
ልዑል እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በሥርዓትና በሕግ እንዲመራ አድርጎታል። ለአኗኗሩ ሥርዓት አበጅቶለት ፍጥረታትን እንዲገዛ አዞና ሥልጣን ሰጥቶት በገነት እንዳስቀመጠው እውነት ነው። ስለሆነም የእግዚአብሔር ሕግ ስንልም ከእግዚአብሔር ፈቃድ የመነጨ፣ በእግዚአብሔር የተሰጠ፣ አምላካዊ ድንጋጌ ነው። በመጽሐፈ ሔኖክ ፲፱፥፳፪ ላይ የሰው ልጅ እንደ ንጹሐን መላእክት ሃይማኖቱን አውቆና ጠብቆ ፈጣሪውን በመፍራትና በማምለክ እንዲኖር ነው። በመዝሙር ፩፥፪ ላይ፤ «የእግዚአብሔር ሕግ ብቻ ፈቃዱ የሆነ፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ፤ እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች፤ ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ፤ ቅጠሏ እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፣ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል»።
አስተውል! ያንተ ሕይወት ማለት እኮ እስከ ሞት የሚፋለም ባለቤት ያላት የናቡቴ ርስት ናት፡፡ ሕይወትህ በተቃራኒው የቆመች ምድረ በዳ ብትሆንብህም እንኳ አትፍራ፤እግዚአብሔር የምድረ በዳውም ፈጣሪ ነውና ለአርባ ዘመናት የመራውን ሕዝብ የውርጭ መና ከደመና አውርዶ የመገባቸው፤ውኃውንም ከዐለት ላይ አፍልቆ ያጠጣቸው፤ በምድረ በዳ መሆኑን አትርሳ፤ (መዝ ፸፯፥፳-፵) አንተም መናና ውኃ የተባለ የእግዚአብሔር ቃል ተመግበህና ጠጥተህ ምድረ በዳ የሆነ ሕይወትህን ልታለመልምበት ይገባል፡፡ ትናንት ከትምህርት ምድረ በዳ የነበረችውን የእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ሕይወትና የእነ ቅዱስ ያሬድን ሰውነት በልብህ ተመልከታት፤ትውልድ በልቶ የማይጨርሰው የዘለዓለም ስንቅ ተገኝቶባታልና፡፡