በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና
በተለያዩ መድረኮች ቤተ ክርስቲያን ከእምነት ውጭ የሆኑትን ለማሰቃየት የክፉ አድራጊዎች ጠበቃ የሆነች የሚያስመስሉ ጽሑፎች ይቀርባሉ፡፡ ድብቅ ዓላማ ያላቸው ወገኖች ቤተ ክርስቲያንንና ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ሰበብ በመፈለግ ጥፋተኛ እያስመሰሉ ያቀርባሉ፡፡ በመሠረቱ ይህ አስተሳሰብ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ታሪክ በመሰነድ፣ ትውልድ በምግባር ኮትኩታ ያቆየች ባለውለታ፣ ቅርሶቿ ለሀገር ልዩ መታወቂያ ጐብኝዎችን ማርኮ የሚያመጣ ሆኖ ሳለ ያለ ስሟ ስም መስጠቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከእውነት የራቀ ሐሳብ ይዘው ጥፋተኛ ሳትሆን፤ ጥፋተኛ ስለሆነችና ከአጥፊዎች ስለተባበረች መጥፋት ይገባታል እንበቀላት የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ለማጥፋት ምክንያት ፈላጊ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን እያቃጠሉና ምእመናንን እየገደሉ ለምን ሲባሉ ጥፋተኛ ስለሆነች ይላሉ፡፡ መቼ፣ የት፣ በማን፣ እነማንን ተብለው ሲየጠቁ መልስ የላቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠልና ምእመናንን መግደል የእምነቱ ተከታዮች ራሳቸውን ወደ መከላከል ከዚያም ወደ መጉዳት ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ መረዳት ይገባል፡፡ ለተፈጸመው ጥፋት አጸፋውን ቤተ ክርስቲያን ብትመልስ በሀገር ላይ ሊከሠት የሚችለውን ጥፋት አስቀድሞ መረዳትም ይጠቅማል፡፡ ጥናትን ሽፋን አድርጎ ለአጥፊዎች ዱላ የሚያቀብሉ አካላትም ከድርጊታቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ ከማቅረብ በተጨማሪ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን ከለላ መስጠት ይኖርበታል፡፡ አጥፊዎችም ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የመዘዙት ሰይፍ ወደ ራሳቸው እንዳይዞር እና የእርስ በእርስ መጠፋፋት ሊያስከትል እንደሚችል ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በሃይማኖትና በዘር ምክንያት የተቀሰቀሰ ግጭት መብረጃ እንደሌለው በየሀገራቱ የተፈጸሙትን ጥፋቶች ማየት ይገባል፡፡ ታሪክ መጥቀስ ብቻውን የዕውቀት ባለቤት አያደርግም ከታሪክ መማር እንጂ፡፡
ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውንና ከዛሬ ነገ እርምት ይወስድበታል በማለት በትዕግሥት ስትጠብቅ መኖሯን ከመግለጻችን በፊት ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት ስታዘጋጅ፣ በፍቅር ስባ፣ በትምህርት አለዝባ በእምነትም በምግባርም እንዲስተካከሉ በማድረግ ነው፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ሀገራችን ብቸኛ የራሷ ፊደል ያላት፣ ዘመን ተሻግሮ ከዘመናችን የደረሰ ቅርስ አበርክታ ሀገራችን በመላው ዓለም እንድትታወቅ ያደረች ባለውለታ ናት፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ኢትዮጵያውያን የቅኝ ግዛት ቀንበርን ሰብረው ጥለው፣ የነጭን ትምክተኛነት አስተንፍሰው ልጆቻቸው ቀና ብለን እንድንሔድ የመሪነቱን ሚና የተጫወተች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በውጭ ሀገራት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተጽፈው እምነት፣ ዕውቀት፣ ሥነ ምግባር የሚያስተምሩ መጻሕፍት ኢትዮጵያዊ በሆነ ብሂል ተተርጒመው ትውልድ እንዲማርባቸው፣ ሊቃውንቶቿ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ የኢትዮጵያን ባህል፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ በማስተዋወቅ የአምባሳደርነት ሚና እንዲጫወቱ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህን የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ‹‹የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት በኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጭ በመሔድ በታሪክ ሊታወስና ሊጠና የሚገባ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አካባቢ በሱዳንና በግብፅ፣ በየመንና በኢየሩሳሌም፣ በአውሮፓ በመሔድ እነሱም እየተማሩ፣ የውጭውንም ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋና ታሪክ፣ ሃይማኖትና ባህል እንዲያውቅና እንዲፅፍ አድርገዋል›› (አክሊሉ፤፹፩) በማለት ገልጠውታል፡፡
እውነተኞቹ ተመራማሪዎች ያለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን ማሰብ እንደሚከብድ በምርምራቸው አረጋግጠው እውነቱን ከሐሰት፣ ብስሉን ከጥሬ፣ የሚጠቅመውን ከሚጐዳው፣ የተፈጸመውን ካልተፈጸመው ለይተው ከጥንካሬያችን እንድንማር ከስሕተታችን እንድንጠበቅ ያደረጋሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከም ዓላማችንን ያሳካልናል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ደግሞ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ፈልገው ቅስማቸው ተሰብሮ እንዲመለስ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ስለተረዱ ስሟን ለማጥፋት፣ ታሪኳን ለመበከል የጻፉትን አሉባልታ እውነት አድርገው በመውሰድ ታሪክ ሲያበላሹ፣ በተቀመጡበት የኃላፊነት ቦታ ጥፋት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ሰውን በሰውነቱ እኩል ማገልገል ሲገባቸው በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በጎጥ፣ በቡድንና በባህል በመከፋፈል ሥልጣንን ለክፉ ተግባር ይጠቀማሉ፡፡ ሕዝብን ለማገልገል የተሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን የማሳደድ ተልእኮ ይፈጽማሉ፡፡ ሀገር ሰላም ካልሆነችና ዜጎቿ በሰላም ወጥተው ካለገቡ አጥፊዎችም ችግር እንደሚገጥማቸው አልተረዱትም፡፡
በካናዳ፣ በቫቲካን፣ በጀርመንና በሌሎችም ሀገሮች የኢትዮጵያ ጥናት ተቋማት እንዲከፈቱ፣ ተመርምሮ የማያልቅ ዕውቀት የያዙት የብራና መጻሕፍት ለዓለም እንዲተዋወቁ ያደረጉት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምራ «ሑሩ ወመሀሩ» ብላ ያሰማራቻቸው ሊቃውንት ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ሀገራችን እንግዳ ተቀባይ የሆነችውና ዓለም ፊቱን ያዞረባቸውን የመሐመድ ተከታዮች ሳይቀር መጠጊያ እንድትሆን ያደረጋት ቤተ ክርስቲያን በእምነት ኮትኩታ፣ በምግባር አንፃ ያስተማረቻቸው እነ ንጉሥ አርማህ ርኅሩኆች ብቻ ሳይሆኑ አስጠጉኝ ብሎ የመጣባቸውን አሳልፈው ለመስጠት ሰብአዊነት የተለያቸው ስላልነበሩ ጭምር ነው፡፡
ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር እንዲሉ ይህን ውሉ ውለታ ለዋለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልስ ነው፡፡ የደረሱበት መረጃ ካለ ማስረጃን መሠረት አድርጎ እውነት ማሳወቅ አንድ ነገር ነው፣ ሐሰትን እውነት እያስመሰሉ ማቅረብና ሰውን ለብጥብጥ መጋበዝ ግን ጤነኛ አእምሮ ያለው፣ በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው የሚፈጽመው አይደለም፡፡ በየጊዜው ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃጥሉት፣ ክርስቲያኖችን የሚገድሉት፣ ንብረታቸውን የሚቀሙትና የሚያሳድዱት ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መንግሥት እርምት ይወስዳል ቢባልም ምንም ነገር እንዳልተፈጸመ እየታለፈ፣ የማዘናጊያና የማረሳሻ ተግባር እየተፈጸመ ነው፡፡
ከምዕራባውያን የተኮረጀው ሥርዐተ ትምህርት ባልነበረበት ዘመን የሀገራቸው አምባሳደር የነበሩ፣ የውጭ ዲፕሎማት ሲመጣ አስተርጓሚ ሆነው ሲያገለግሉ የኖሩ ሊቃውንትን ያፈራችን ቤተ ክርስቲያን ከዋለችበት ላለማሳደር፣ ካደረችበት ላለማዋል እየተፈጸመ ያለው ግፍ መቆም አለበት፡፡ የሊቃውንቱን አስተዋጽኦ አክሊሉ ሀብቴ ‹‹ሆኖም እዚያ (ኢየሩሳሌም) የተደራጀው የመነኮሳት ማኅበር ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ኢጣሊያም፣ ወደ አርመንም፣ ወደ ቊስጥንጥንያም፣ በመሔድ ግንኙነት ፈጥሮ እንደነበርና ምን አልባትም ከአርመኖች ጋር በነበረው የቅርብ ግንኙነት አርመኖች ፊደላቸውን ሊቀረፁ የቻሉት ከኢትዮጵያ ፊደል እንደሆነም ይነገራል፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም በሚመላለሱበት ዘመን እግረ መንገዳቸውንም ከሱዳንና ከግብፅ ክርስቲያኖች ጋር የቅርብ ግንኙነት መፍጠራቸው ይታመናል፡፡ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት ፈር ቀዳጅ አስተዋጽኦ እንዲሁ መጠናት የሚገባው ነው›› (አክሊሉ፣ ፷፪) በማለት ገልጠውታል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ሰው አክባሪ፣ ሀገር ወዳድ፣ የሥራ ፍቅር ያላቸው፣ የራሳቸውን የማያስነኩ፣ የሌላውን የማይፈልጉ አድርጋ ስታሳድጋቸው ጠብ አጫሪነትን፣ በጉልበታቸው የሚመኩ መሆንን እንዲጸየፉ በማድረግ ነው፡፡ ጠላታቸውን በጽናትና በትዕግሥት እንዲቋቋሙ፣ ሀገርና ሃይማኖት ሊያጠፋ የመጣውን የጥፋት ኃይል እንዳያሸንፍ ያደረገች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህ ድርጊቷ ያበሳጫቸው ምዕራባውያን በዘመናዊ ትምህርት ሰበብ በየሴሚናሪዎቻቸውና ኮሌጆቻቸው አስተምረው የላኳቸው ወገኖቻችን ነባሩን የኢትዮጵያ ሃይማኖትና፣ የክርስቲያኖች ተጋድሎ የሚያናንቅ፣ መልኩ የእኛ ቢሆንም የነጭ ጉዳይ አስፈጻሚ ሀገሪቱን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት የባለቤትነት ስሜት የሚያድርበት እንዳይሆን አእምሮውን ለውጠው ሲልኩት ኖረዋል፡፡ በመመረቂያ ጽሑፍ ሰበብ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ስሟ ስም፣ ያለ ግብሯ ግብር እየሰጡ የዘመናችን ተመራማሪ ነን ባዮች የግብር አባት ሆኑ፡፡ በዚህ ተግባራቸውም ትውልዱ በሰላም ውሎ እንዳይገባ እንቅልፍ ላጡ ወገኖች መንገድ መሪ የጥፋት ተባባሪ ሆነው አልፈዋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሠየሙ አካላት በተለያዩ የኅትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያወርዱትን የስድብ ዶፍ መመልከት ይቻላል፡፡ በአካል መግዛት ያልተቻላቸውን ኢትዮጵያውያንን በአእምሮ ለመግዛት መሰሎቻችንንና በሥጋ የሚዛመዱንን አእምሮ እየለወጡ የሚልኩልንንና እነሱም አልፎ ሒያጅ መንገደኞችና ለቤተ ክርስቲያን ጥላቻ ያደረባቸውን ወገኖች እየጠየቁ የጻፉትን አሉባልታ በትክክለኛ ማስረጃ በመሞገት፣ የዕውቀታቸውን ግልብነት፣ የመረጃቸውን ተራነት፣ የትነታኔያቸውን አመክንዮ አልባነት ማሳየት ይኖርብናል፡፡ አጥፊዎች ታጥቀው ሲዘምቱብን ዝም ብሎ ማየት እሳት መቃጠሉን የሰማ የዋህ እኔስ ሣር ውስጥ ተደብቄያለሁ በማለት የመለሰውን የሚያስታውስ ይሆናል፡፡
ቱሪስቶች ሊጐበኙ የሚመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ገዳማት፣ አድባራት፣ ሥዕላት፣ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት እንዲሁም ክርስቲያን ነገሥታት የገነቧቸውን አብያተ ክርስቲያናት፣ ሐውልቶችና አብያተ መንግሥታት ለመጎብኘት ነው፡፡ ይህን አስተዋጽኦ ያደረገችልን ቤተ ክርስቲያን መደገፍና መጠበቅ ሲገባ ስትጠቃ ዝም ብሎ ማየት ማሯን እንጂ ንቧን አልፈልግም እንደ ማለት ይቈጠራል፡፡ ለጥፋት የተሰለፉ ወገኖች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ አደጋ ሲያደርሱ የግለሰቦች ጉዳይ እየመሰለ ይቀርባል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ይነገራል፡፡ በሌሎች እምነቶች ላይ የሚፈጸመው ወይም ራሳቸው ፈጽመው ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል የተባለውን ለሚፈጽሙት ግን ከመገናኛ ብዙኃን ጀምሮ የሚሰጠው ሽፋን የሚገርም ነው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች ሲገደሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ መረጃው በቶሎ እንዳይነገር ከተቻለም ተዳፍኖ እንዲቀር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን እንድንጠረጥር የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ በቡኖ በደሌ የተፈጸመውን ሰቆቃ በሥልጣን ላይ የተቀመጡ አካላት ወንጀሉን የፈጸሙት አካላት በእምነት ስለሚመስሏቸው ለማዳፈን ሞክረዋል፡፡ በሰሜን ሸዋና በኬሚሴ በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው ጥፋት በመገናኛ ብዙኃን የተነገረው ጥፋቱ ከተፈጸመ ከአራት ቀናት በኋላ መሆኑን ኢትዮጲስ ጋዜጣ በሚያዝያ ፮ ዕትሙ አስነብቧል፡፡ በበሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አካባቢው አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለውና ምእመናን ተገድለው አጥፊዎችን መያዝ ሲገባ መረጃው ያላቸውን ክርስቲያኖች ለመያዝ ይደረግ የነበረው ወከባ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ይቆየን!
ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከግንቦት ፲፮-፴ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም