ቤተ ክርስቲያንን ከጠላት ስውር ደባ ለመጠበቅ ጾምና ጸሎት ያስፈልጋል!

           

በሕይወት ሳልለው

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የድህነታችን መገኛና መገለጫ ናት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጫቻችኋለሁና” (፪ቆሮ ፲፩፥፪) ሲል በቆሮንቶስ መልእክቱ ገልጿል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በጠላት ስትታደን እንደኖረች ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ልጆቿም እንደሷ ብዙ መከራን እንዳዩ፤ ያለበደላቸው መከራን እንደታገሱና ለእምነታቸው ብዙ መሥዋዕትነት እንደከፈሉም አንብበን ተረድተናል፡፡ ለምሳሌ “ዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን ያሳለፈችበት ዘመን ነበር፡፡ ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ስናይ ዕለተ ዐርብን እናስባለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት፤ካህናት፤ ቀሳውስትና አገልጋዮች የሥራ ድርሻቸውን የሚያካሂዱባት የተቀደሰች ስፍራ ቤተ ክርስቲያን ናት” በማለት መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግሥቱ ማርያም፤ በአዲስ አበባ ሀገር ስብከት የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ቤተ ክርቲስያን የስብከተ ወንጌል ሐላፊ አስረድተዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ህልውናዋ ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየክፍለ ሀገራቱ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ መሆኑ በይፋ እየተነገረ ነው፡፡ ከጅማው ክስተት በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ ችግር ደርሷል፡፡ ለዚህ የሀገር ጉዳይ መፍትሔ ለማግኘት የሃይማኖት አባቶች፤ አገልጋዮችና የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ያቃጠሉ ሰዎች ሲያልፉ በዘመነ ሰማዕታት ውስጥ ያለፈች ቤተ ክርስቲያን ግን ዛሬም ነገም ምእመኖቿን አስተምራ፤ሥጋ ወደሙን እያቀበለች ትኖራለች፡፡

“የምእመናን ድርሻ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መከራ እንዲቆም ጾምና ጸሎት ያስፈልጋል፤ያለበለዚያ ግን እሳትን ሰማዕትነት ነው ብለን አናስበውም፤መከራ ነው እንጂ፡፡  ሰማዕታት የሃይማኖት ፍሬ እንዳያመልጣቸውና አክሊልም እንዳያልፈን በማለት ይሯሯጡ ነበር፡፡ በመጀመሪያ፤ እንኳን መንፈሳዊ ሥራ ሥጋዊ  ሥራም ያለ የእግዚአብሔር ፍቃድ አይሳካም” ሲሉም መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግሥቱ ማርያም ጨምረው አብራርተዋል፡፡

ይህ የጠላት ሴራና ክፋት በተለያየ መንገድ ምእመናንንና ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚደረግ በመሆኑ ከሥር መሠረት ልንመረምረው ይገባል፡፡ “የአማኞችን መብት ጠብቀው የአምልኮት ሥርዓታቸውን በሀገራቸው በነፃነት እንዲፈጽሙ የሃይማኖት መሪዎች ጥብቅና ሊቆሙላቸው ይገባል፡፡ ሲሰደዱ፤ ሲገደሉና ለተለያየ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ዝም ብለን ማየት የለብንም፡፡ ይህ የአገልጋዮች ምግባር እየቀዘቀዘ በመሄዱ፤ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ አይነት ተፅዕኖ ተዳርጋለች፡፡ አንዳንድ ሰዎች በኃይል ወይም በነውጥ የሚያደርጉት አግባብ የሌለው ተግባር ሊወገዝ ይገባል” ሲሉ የቅዱስ ጳውሎስ የሐዲስ ኪዳን መምህር መጋቤ ሐዲስ አእምሮ ደምሴ ገልጸዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንድትደክም፤ ምእመናን ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር እንዲሁም የትክክለኛዋ ሃይማኖት ተከታይና ክርስቲያናዊ ምግባር እንዳይኖር በስውር ተመሳስለውና በስመ ሰባኪ የጠላትን ምኞት ለማሳካት ደፋ ቀና የሚሉ ተኵላዎችም በዝተዋል፡፡ “የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው”፤(ማቴ ፯፥፲፭) ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡

ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የራቁ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና፤ ሥርዓትና ትውፊት ውጪ በመሆን ከራሳቸውም አልፎ ሌሎችን ያስታሉ፡፡ ጠላታችን ዲያብሎስ ከጥንት ጀምሮ ምእመናንን ተስፋ ማስቆረጥ፤ ከእምነታቸውና ሃይማኖታቸው ማስወጣት ተግባሩ ነውና  ልንጸና ይገባል፡፡ ይህም የሚሆነው አምነን፤ተጠምቀን በበጎ ምግባር ታንጸን በሕገ እግዚአብሔር መኖር ስንችል ነው፡፡ በመጽሐፍ እንደተጻፋው እነዚህ ጸንተው ይኖራሉ የሚላቸው ሦስት ነገሮች እምነት፤ተስፋና ፍቅር  ናቸው፤ (፩ቆሮ ፲፫፥፲፫)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ እንደገለጸው “ደስ የሚላችሁን እንድታደርጉ እንረዳችኋለን እንጂ እንድታምኑ ግድ የምንላችሁ አይደለም”፤ (፪ቆሮ ፩፥፳፬) ፡፡

እንዲህ እምነት በጠፋበት፤ የመናፍቅ ቅሰጣ በበዛበት፤ ዓለም በኃጢአት ማዕበል በምትናወጥበት ወቅት ከሐሰተኞች ትንቢት መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ጌታችንም እንደተናገረው “የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ብዙዎችንም ያስታሉ፤ጦርነትን፥ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው”፤(ማቴ ፳፬፥፬-፮)፡፡

ከጠላት ስውር ደባ ለማምለጥ የእግዚአብሔር ቸርነት ከእኛ ጋር ሊሆን  ያስፈልጋል፡፡ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ያለንን ኅብረት ማጠንክር ስንችልም ፈጣሪያችን ያድነናል፡፡ እያንዳንዳችን ቤተ ክርስቲያን መሔድ፤ ክርስቲያናዊ ምግባርን ማዘውተር፤ ዘወትር መጸለይ፤ ንስሓ መግባትና መጾምም  ይጠበቅብናል፡፡