የተሰጠህን አደራ ጠብቅ (፩ጢሞ. ፮:፳) (በእንተ ላ ሊበላ)
ብዙአየሁ ጀምበሬ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ያበረከተችው አስተዋጽኦ በብዙ ዐውድ የሚገለጽ እና መጠነ ሰፊ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል በቋንቋ፤ በባሕል፤ በአለባበስ፤በሥነ ጽሑፍ፤ በኪነ ጥበብ፤ በኪነ ሕንፃ እና በቅርጻ ቅርጽ ዘርፍ የተደረጉት አስተዋጽዖዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህች ስንዱ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮአዊ የሆኑ የዕፀዋት ዝርያዎችን በአግባቡ በመጠበቅ እና በመንከባከብ የሀገር ሕልውናን በማስጠበቅ እና ተፈጥሮ ዑደቱ ሳይዛባ እንዲቀጥል በማድረግም እጅግ የጎላ አገልግሎቷን በማስመዝገብ ላይ ናት፡፡ ዝርያቸው ሊጠፉ የተቃረቡ የዕፀዋት ዓይነቶችን ጠብቃ ያቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍም ቢሆን ሀገራችን የራሷ ፊደል እንዲኖራት እና ለሥልጣኔ ጉልህ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ መጻሕፍት ባለቤት እንድትሆን ረድታለች፡፡
የንባብ ባሕልን ከሥር መሠረቱ በማጎልበት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሳሌ ሊሆን የሚችል የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም አያሌ ምሁራን እንዲፈሩበት ጉልህ ሥራን ሠርታለች፡፡ በዜማውም ዘርፍ የዜማ ሥርዓትን ለዓለም በቀዳሚነት በማስተዋወቅ፣ ሰማያዊ ሥርዓት ያለውን ዜማ በሊቁ ቅዱስ ያሬድ አማካኝነት አበርክታለች፡፡ በኪነ ሕንፃ ዘርፍ ደግሞ በዓለማችን ታሪክ በየትኛውም ክፍላተ አህጉራት የማይገኙ እና ደግመው መሠራት ያልተቻሉ ልዩ ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበቦችን በውስጧ የያዘች፤ ያስተዋወቀች እና ጠብቃ ያቆየች ናት፡፡
ለምሳሌ ያህል የአክሱም ሐውልት፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የንጉሥ ፋሲለደስን ግንብ መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ቅርሶች ለሀገራችን እና ለመላው ዓለም ብታበረክትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለእነዚህ ቅርሶች ተገቢው ጥበቃ እና እንክብካቤ ባለመደረጉ የተነሳ ለከፍተኛ ጉዳት እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ እንዴት እንደተሠሩ መረዳት እንኳን ግራ እስኪገባን ድረስ አስተውለንና የአሠራር ጥበባቸውን አድንቀን ሳናበቃ በቂ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሳይደረግላቸው በመቅረቱ አብዛኞቹ ቅርሶች ለአደጋ እንዲጋለጡ እና ሥጋት ውስጥ እንዲገቡ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ከእነዚህ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ካሉት ቅርሶች መካከል በአሁኑ ሰዓት በከፋና እጅግ በአሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተፈለፈሉት በ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ላላሊበላ አማካኝነት ነው፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን በ፲፪ ኛውመቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ከእናቱ ኪርወርና እና ከአባቱ ከዛን ሥዩም በላስታ ሮሐ ቤተ መንግሥት ዋሻ እልፍኝ ውስጥ ተወልዷል፡፡ በተወለደ ጊዜም በንብ ስለተከበበ እናቱ ማር ይበላል “ላል ይበላል” ብላ ስም መጠሪያ ይሆነው ዘንድ አውጥታለታለች፡፡ ማር ከፍተኛ ደረጃ ያለው ተወዳጅ ምግብ ስለሆነ መልካም፤ ስመ ጥር፤ ታላቅ ንጉሥ ይሆናል ስትል ላልይበላ ብላዋለች፡፡
በሌላ መልኩም “ላልይበላ ብሂል ንህብ አእመረ ጸጋሁ ብሂል፣ ላልይበላ ማለት ንብ ጸጋውን (ገዢውን) ዐወቀ” ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ላልይበላ የብሉያትን እና የሐዲሳትን የትርጓሜ መጻሕፍት ጠንቅቆ የተማረ ነው፡፡ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን ከአንድ ወጥ ዓለት በመፈልፈል ያነጸው ንጉሡ ከዐሥራ አንዱ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ለ፵ ዓመታት ያህል ነግሦ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡(ምንጭ፡ ገድለ ቅዱስ ላልይበላ ሰኔ 2003 ዓ.ም ገጽ13)፡፡የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በቊጥር ዐሥራ አንድ ሲሆኑ፣እነርሱም፡- ቤተ-ማርያም፤ ቤተ-መድኃኔ ዓለም፤ቤተ-ደናግል፤ ቤተ-መስቀል፤ ቤተ-ደብረሲና፤ቤተ-ጎልጎታ፤ ቤተ-አማኑኤል፤ቤተ-አባሊባኖስ፤ቤተ-መርቆሬዎስ፤ ቤተ-ገብርኤል ወሩፋኤል፤ ቤተ-ጊዮርጊስ የተሰኙ ናቸው፡፡
ቤተ-ደብረሲና በመባል የሚጠራው ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ቤተ-ሚካኤል በመባልም ጭምር ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከልም በቅድሚያ የታነጸው ቤተ-ማርያም የተሰኘው ሲሆን በወርኃ ታኅሣሥ በ፳፱ኛው ቀን የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እና የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል “ቤዛ ኲሉ” የሚዘመርበት ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ከእነዚህ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት መካከል በመጠን ከሁሉም የሚልቀው እና ግዙፍ የሆነው ቤተ-መድኃኔዓለም ሲሆን በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ”አፍሮ አይገባ” በመባል የሚታወቀው የመስቀል ይገኛል፡፡
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሲነሱ በሁላችን አእምሮ የሚታወስና ትዝ የሚለን ከላይ ሲታይ በመስቀል ቅርጽ የታነጸው እና ከሌሎች በተለየ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የተወቀረው ቤተ-ጊዮርጊስ ነው፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ተሠርተው ለመጠናቀቅ ፳፫ ዓመታትን ፈጅተዋል፡፡ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ በዓለም ላይ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተገለጡት አስደናቂ የኪነ ሕንፃ ጥበቦች መካከል ወደር እና አቻ የማይገኝላቸው ናቸው፡፡
የአብያተ ክርስቲያናቱ የኪነ ሕንፃ ንድፍ (Design) እና ሥነ ውበት (Aesthetics) በአስደናቂ ሁኔታ ተጣምሮ የተዋሐደበት ልዩ የመንፈሳዊ ምሕንድስና አሻራም የታየበት ነው፡፡እስካሁን ባለው የኪነ ሕንፃ እና የምሕንድስና ታሪክ ውስጥ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዓይነት የረቀቀ ጥበብ የታየበት ሥራ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ እንዳልተሠራ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ፡፡ የአሠራሩ መንገድ ከታች ከመሠረት ሳይሆን ከላይ ከጣራ መጀመሩ በዋነኛነት ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዓለት መፈልፈላቸው እና በሥራቸው የውኃ ማጠራቀሚያ ቋት መያዛቸውም በራሱ ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ ንጉሥ ላሊበላ ይህንን አስደናቂ የኪነ ሕንፃ ሥራ ሲሠራ ከፈጣሪው ከልዑል እግዚአብሔር ባገኘው መንፈሳዊ ጥበብ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይገልጣሉ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለመረጣቸው እና አካሄዳቸውን ከእርሱ ጋር ላደረጉ መልካም ሰዎች ጥበብን ያድላል፤ ለዚህም የባስልኤል እና የኤልያብን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስታወስ ያሻል፡፡ “ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ባስልኤልና ኤልያብ በልባቸው ጥበበኛዎችም ሆኑ፣ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ነገር ሁሉ አደረጉ፡፡ ሙሴም ባስልኤልና ኤልያብን እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው፡፡ (ዘጸ.፴፮፡፩-፩) እንዲል፡፡
የውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ መሠረታዊ የጂኦሜትሪያዊ ልኬት(Geometric proportion) የንድፍ ሥርዓትን የጠበቁ ናቸው፡፡ በሥጋዊ ምርምር ሊደረስባቸው አይችልም፡፡ለዚህም ነው ልዩ የከበረና ዘመን የማይሽረው የኪነ ሕንፃ ቅርስ መሆን የቻለው፡፡ ለዚህም ነው የዓለም ዜጎች ያከበሩት እና በየጊዜው ለመጎብኘት ወደ ሀገራችን የሚመጡት፡፡ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አስደናቂነት እና ዘመን የማይሽራቸው የታሪክ አካላት እንደሆኑ በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ምሁራን ዘንድ ጥናት ተደርጓል፤ በግልጽም ተመስክሯል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹን እናንሳ ከ፲፭፻፲፪ ዓ.ም እስከ ፲፭፻፲፰ ዓ.ም ድረስ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አብያተ ክርስቲያናቱን የጎበኘው የፖርቹጋሉ ተወላጅ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ስለ ላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት ድንቅ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ይህ ሰው የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ዜጋ ሲሆን ጎብኝቶ ካጠናቀቀ በኋላም ስለ አብያተ ክርስቲያናቱ አስደናቂነት እጅግ ብዙ ጽፏል፡፡
በጽሑፉ ማጠናቀቂያ ላይም እንዲህ ብሏል “ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራዎች ብዙ ብጽፍም የሚያምነኝ ሰው መኖሩ በጣም ያስጨንቀኛል፤ ያሳስበኛልም እስካሁን ያልኩትም እንኳ ቢሆን ውሸት ነው የሚሉኝ፡፡ ነገር ግን የጻፍኩት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም ስሜ በቀጣፊነት እንዳይነሳ እሰጋለሁ … ይህን የሚመስል በዓለም እንደማይገኝ እገልጻለሁ፡፡” በማለት ድንቅ ምስክርነቱን በዚያን ዘመን ገልጿል፡፡ (ምንጭ፡ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ሰኔ 2003 ዓ.ም ገጽ 15)፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አንድርዜይ በርትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል ኒየችኮ የተባሉት የታሪክ ጸሐፍት የኢትዮጵያ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ “ንጉሡ በስሙ በሚጠራው በላሊበላ ከተማ እስከ ዛሬም ድረስ ዝናቸው ያልደበዘዘውን ከዓለት ተፈልፍለው የታነጹ አብያተ ክርስቲያናት መሥራቱ ታላቅ የታሪክ ባለውለታ አድርጎታል” በማለት ገልጸውታል፡፡ (ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ታሪክ አንድርዜይ በርትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል ኒየችኮ ትርጉም አለማየሁ አበበ ገጽ 32፤2003 ዓ.ም እትም)፡፡
ዓለም የተደነቀባቸው እና በእጅጉ ያወደሳቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ፲፱፸፻፱ ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፤ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (UNSCO) አማካኝነት በዓለም ቅርስነት ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ለሀገራችን ኢትዮጵያም ባለውለታ ናቸው፡፡ ይህም ሲባል ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ቅርሶቹን ለመጎብኘት ከሚመጡ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች አማካኝነት በየዓመቱ ከፍተኛ ገቢ በቱሪዝም ዘርፍ ለመንግሥት እንዲገባ ማስቻሉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ የሀገራችን አባቶች ዓለምን የሚያስደንቅ ረቂቅ የኪነ ሕንፃ አሻራ አስቀምጠውልን ማለፋቸው አስተዋይ ትውልዶች ከሆን የእነርሱን ፈለግ በመከተል በሥልጣኔ እድገት ከፍተኛ ማማ ላይ እንደምንቀመጥ አመላካች ነው፡፡
ለሀገር ውለታ የዋሉ እነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ከፍተኛ የሆነ አደጋ ተጋርጦባቸው ይገኛል፡፡ ይኸውም በዕድሜ መግፋት እና ለቅርሶቹ ጥበቃ ተብለው በተሠሩት የብረት ጣሪያዎች(Shade structures) ምክንያት አብያተ ክርስቲያናቱ ላይ በግርግዳቸው በኩል የመሰንጠቅ አደጋ እየተስተዋለባቸው ይገኛል፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ እና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ጉዳቱ አመዛኝ ሆኖ የቅርሶቹ ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ለእኛ ለዚህ ትውልድ ሰዎች ደግሞ ከአባቶች በአደራ የተላለፉትን ዘመን የማይሽራቸውን ውድ ቅርሶች በአግባቡ ባለመጠበቅ የታሪክ ተወቃሽ ለመሆን እንበቃለን፡፡
ለመሆኑ ንጉሥ ላሊበላ ምን ይለን ይሆን? አባቶቻችንስ እንዴት ይታዘቡን ይሆን? እነዚያን የመሰሉ አይደለም ደግመን ለመሥራት ቀርቶ እንዴትስ እንኳን እንደተሠሩ ተመራምረን መድረስ ያልቻልንባቸውን ድንቅ የታሪክ አሻራዎች ሠርተው አስረክበውን እኛ እንዴት በኃላፊነት መጠበቅ እና በአግባቡ መንከባከብ ያቅተን? በሀገራችን የሚገኙ በኪነ ሕንፃውም በምሕንድስናውም ዘርፍ አንጋፋ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው የቤተ ክርስቲያን ብሎም የሀገሪቱ ምሁራንስ በዚህ ጉዳይ ለምን በአስቸኳይ መፍትሔ መስጠት አልቻሉም?
እንደ ሀገር የቤተ ክርስቲያን የሆኑትን ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የሚገኙ ማንኛውም ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ላይ አደጋ ሲጋረጥ “የእከሌ ኃላፊነት ነው፣ እኔን አይመለከተኝም” በማለት ራስን ገለልተኛ ከማድረግ ይልቅ በመወያየት እና አግባብነት ያላቸውን ምክክሮች በማድረግ መፍትሔ ማምጣት ግድ ይለናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን “እነርሱም አልሠሩትም፤ እነርሱም አልጠበቁትም” ተብለን የታሪክ ተወቃሽ ሆነን እናልፋለን፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ የሀገሪቱ የባሕል እና ቱሪዝም ኃላፊዎች፤ የኪነ ሕንፃ እና ምሕንድስና ምሁራን፤ በየሥልጣን ተዋረዱ የሚገኙ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ብሎም እያንዳንዱ ምእመን ችግሩ ይመለከተኛል በማለት አስቸኳይ እና ቀጠሮ የማይሰጠው መፍትሔ ማምጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ምእመን ፈጣሪ ሀገራችንን፤ ሕዝቦቿን እና ቅርሶቻችንን እንዲጠብቅልን ዘወትር በጸሎት መጠየቅም ይጠበቅበታል፡፡
ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግር በቅርሶቻችን ላይ እንዳያጋጥም እና ቢያጋጥም እንኳን ተገቢውን መፍትሔ ለመስጠት ያስችለን ዘንድ በኪነ ሕንፃ እና በምሕንድስና ላይ የተሰማሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማስተባበር ሥርዓትን እና ሥነ መዋቅርን የተከተለ የቤተ ክርስቲያን ቴክኒካዊ ክፍል መዘርጋት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የሲቪል መሀንዲሶች(Civil and Structural Engineers )፣ የኪነ ሕንፃ እና የከተማ ልማት ባለሙያዎች(Architects Urban planners and Architectural Historians)፤ የኮንስትራክሽን ግንባታ ባለሙያዎች (Construction TechnologyManagement)፤ የመካኒካል መሐንዲሶች(Mechanical Engineers)፤ የአፈር እና የድንጋይ ምርምር ባለሞያዎች(Geologists and Geo Tech Engineers)፤የቅርስን እና አካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች(Culture and Heritage professionals)፤ የሥነ ሰብእ ተመራማሪዎች(Anthropologists)፤ የታሪክ ምሁራን (Historian) እና የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ያሰባሰበ ቡድን በማቋቋም ችግሩ የተከሰተበትን ምክንያት በማጥናት እና በምን መልኩ ጥገና እና ዕድሳት ይደረግለት የሚለውን ታሳቢ በማድረግ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ይህ የሞያተኞች ቡድን ወደፊትም ተመሳሳይ ችግር በቤተ ክርስቲያን እና በሀገር ቅርሶች ላይ ሲጋረጥ መፍትሔ ለማምጣት የሚሠራ የቤተ ክርስቲያን የአስተዳድር ወይም የቴክኒክ አካል ተደርጎ ሊመሠረት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ባለመሥራታችን ተመሳሳይ ችግሮች በተከሰቱ ቊጥር የመፍትሔ ያለህ እያልን መጮህ እና የቅርሶቹን የእንግልት እና የአደጋ ሥጋት ጊዜ ማስፋት እና እስከወዲያኛውም ድረስ ላናገኛቸው እና ላይተኩ ሆነው እንዲጠፉ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ በጣሊያን አማካኝነት ተወስዶ የነበረውን የአክሱም ሐውልት ለማስመለስ የተደረገውን ጥረት ለአብነት እንደ ጥሩ ተሞክሮ አድርጎ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ በጊዜው በሁሉም ባለድርሻ አካላት የተደረገውን ዓይነት ርብርብ አሁን ላይም በመድገም ቅርሶቻችንን መታደግ ያስፈልጋል፡፡
በሌሎች ሀገሮች የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ የሚያደርጉ ከዲዛይን፤ ምሕንድስና እና ግንባታ ዘርፎች የተወጣጡ አባላትን ያካተቱ የቴክኒክ ክፍሎችን በማዋቀር የቅርስ ጥበቃ እና እድሳት (Conservation and Restoration) እንደ አስፈላጊነቱ ያደርጋሉ፡፡ የእኛም ሀገር የሃይማኖት ተቋማት ከነዚህ ሀገራት አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች እምነት ተቋማት ተሞክሮ በመውሰድ በቅርሶቻችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ መቀነስ ብሎም ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡ አባቶቻችን የሠሩልንን እና ያስረከቡንን የታሪክ ቅርሶች በአግባቡ ተቀብለን እና ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ እና ቅብብሎሹ እንዲቀጥል ማድረጉ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የአስተዳድር ሥነ መዋቅርም ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ ከመንግሥት ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ማምጣት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፤ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁ7 ኀዳር2011 ዓ.ም