፲ቱ ማዕረጋት
ሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
መምህር ደጉ ዓለም
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ
የሐዲስ ኪዳን መምህር
- “ኩኑ ቅዱሳን እስመ ቅዱስ አነ” ዘሌ.19፡2
ቅዱሳን ማለት የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐንየሆኑ፣ የጠሩ….. ወዘተ ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን በዚህ ስም የሚጠሩበት ከሰው ወይም ከምድራዊ ባለሥልጣን የተቸሩት አይደለም፡፡
በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ጐልምሰው የሥጋ ምኞታቸውን ጥለው አፍርሰው ሲገኙ የቅድስና ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር እነሱን /ቅዱሳንን/ መሣሪያ አድርጐ ኃይሉንና ሥልጣኑን ቢገልጽባቸው ማኅደረ እግዚአብሔር መሆናቸው ይገለጻል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ እሱ እግዚአብሐር ቅዱስ ተብሏልና የጌትነቱ መገለጫ የሆኑ ሁሉ ቅዱሳን ይባላሉ ጻድቃን እንደመ ላእክት ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ /ኢዮ.1፡6/፣ ሮሜ.8፡14/ ቅዱሳን ጻድቃን በግብር መላእክትን መስለው ሆነው የፈጣሪአቸውን ፈቃድ ፈጽመው በመገኘታቸው ከዚህ ዓለም በመለየታቸው ቅዱሳን ሲባሉ የፈጣሪአቸውን ሕያው መንግሥት ወራሾች ናቸውና ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ በሌላም ቃል ውሉደ ብርሃን ይባላሉ፡፡ /ሉቃ.16፡8/ በዓለማቸው ይራቀቃሉና ይህን ዓለም ይጠሉታል፡፡ ውሉደ ሕይወት ይባላሉ ሞትንና የሞት ከተማ ይህን ዓለም ይንቃሉና በክብር ተነሥተው ዳግመኛ ሲሞቱ የማይገባቸው ስለሆነ /ሉቃ.10፡30/ ውሉደ ጥምቀት ተብለዋል ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን ተጐናጽፈዋልና፡፡ ውሉደ መንግሥትም ተብለዋል የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናቸውና፡፡ በጸጋ እግዚአብሔር የበለጸጉ በመሆናቸው የእግዚአብሔር አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለዋል /መዝ.33፡15/
የፈጣሪአቸው ፈቃድ በተግባራቸው ስለሚታይ የእግዚአብሔር አዝነ ፈቃድ ወደ ጻድቃን ነው፡፡ ልመናቸው ጾማቸው እንዲሁም ምጽዋታቸው ሁሉ የተወደደ መሥዋዕት ነው፡፡ ቅዱሳን በዓላማቸው ጾምን ግብዣ /ድግስ/፣ ለቅሶን ዘፈን፣ ደስታን ሐዘን አድርገው በመኖራቸው ይህ ተለዋዋጭ ዓለም በየጊዜው የሚአቀርብላቸው መርዶ በእነሱ ዘንድ ዋጋ የለውም ወይም ዋጋ አይሰጡትም፡፡ ዓለምም ለእነሱ የሚያቀርበው ዓለማዊ የምኞት ስጦታ እንደ ኢምንት የተቆጠረ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱ ወደ ዓለማውያን ሰነፎች እንደሆነ ገጸ ምሕረቱ ወደ ቅዱሳን ነው፡፡ ስለዚህ አማላጅነታቸው ጸሎታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ “አፍቅርዎ ለእግዚአብሔር ኲልክሙ ጻድቃኑ” ቅዱሳን እውነትን ይዛችሁ ትሕትናን ተላብሳችሁ እግዚአብሔርን ውደዱት “እስመ ጻድቅ የሐስስ እግዚአብሔር” እግዚአብሔር እውነትን ትሕትናን ይወዳልና፡፡ /መዝ.30፡23/ የቅዱሳን ፍሬ ትሕትና ነው፡፡ በዓይነ ሕሊናቸው ፈጣሪአቸውን በዓይነ ሥጋቸው የእነሱን ምንነት እንዲሁም የዓለምን ከንቱነት ይመለከታሉ፡፡
ፍሬ የያዘ ተክል ሁሉ ቁልቁል የተደፋ ነው፤ ትሕትናን ያስተምራል፣ የጻድቃን ምሳሌ ነው፡፡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ልቡ የተሰበረ እሱነቱን /ምንነቱን/ የመረመረ ሰው በዓይነ ሕሊናው የፈጣሪውን ቸርነት በዓይነ ሥጋው የራሱን ውድቀት ይመለከታል፡፡ ይህ አመለካከት ለጸጋ እግዚአብሔርና ለፍሬ ክብር ያደርሱታል፡፡ በመቅረዝ ላይ ያለች መብራት መሰወር እንዳይቻላት የመቅረዙ ከፍታ የግድ እንደሚገልጻት በተራራ ላይ ያለች ቤትም በእይታ እንደማትሰወር የተራራው ከፍታ እንደሚገልጻት በጥበበ እግዚአብሔር ከብረው በጸጋ እግዚአብሔር ተውበው የሚኖሩ ቅዱሳን ጻድቃንም ደረጃ በደረጃ ማዕረጋትን አልፈው ከመለኮት ባሕርይ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ይሆናሉ፡፡ “መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኑ” /መዝ.67፡35/ “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ በወዳጆቹ አድሮ የሚሠራው ሥራ ድንቅ ነውን፡፡ /2ኛጴጥ.1፡3/ ቅዱሳን የጸጋ ተዋሕዶ ተዋሕደው ሲገኙ ሙት ሲሆኑ ሙታንን ማስነሳት እውር ሲሆነ እውርን ማብራት፣ በዓለም ላይ ድንቅ ሥራቸው ይሆናል፡፡ የጸጋና የክብር ተሸላሚዎች ሆነዋልና በዓለም ላይ ሳሉ የሚመጣባቸውን ፈተና ሁሉ ከምንም ባለመቁጠር ተቋቁመው የጸጋ መቅረዝ ተቋሞች ይሆናሉ፡፡ በዚህም በአላሰለሰው ሕይወታቸው የአንበሳ አፍ ዘጉ /ዳን.7፡1-28/ ውኃውን ወደ ኋላው መለሱ /ዘጸ.14፡22/ ሰማይን አዘዙ /1ኛ ነገ.17፡1፣ ያዕ.5፡17/ ነበለባለ እዥሰት አበረዱ /ዳን.3፡1-13/ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ወዳጅ እግዚአብሔር ከዘመድ ባዕድ ከሀገር የሚኖሩትን በረድኤት ይቀበላል፣ ሥጋዊ ሀገረ ተድላን ጥለው ሓላፊ ጠፊ ምድራዊ ምቾታቸውን ንቀው ጸጋውን የሚጠባበቁትን ሁሉ አብሮአቸው ይኖራል፡፡ ትዕግስትን የጥዋት ቁርስ የቀን ምሳ የማታ እራት አድርገው የሚመገቡትን ሁሉ ቤተ መቅደስ አድርጓቸው ይገኛል፡፡
ቅዱሳን በዚህ ዓለም ይጠበቡበታል፣ ወጥተው ወርደው እነሱነታቸውን ከስስት ኃጢአት ጠብቀው ለወዲያኛው ዓለም ደግሞ በትዕግሥት ደጅ ይጠኑበታል፡፡ “አሪሃ እግዚአብሔር ትፍስህተ ልብ ውእቱ ወይሁብ ሐሴተ ወያስተፌስህ ወያነውሀ መዋዕለ ሕይወት፤ እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፡፡ ፍጹም የሥጋና የነፍስን ደስታ ይሰጣል በሕይወትም ያኖራል፡፡” “ለፈሪሃ እግዚአብሔር ይሴኒ ድሐሪቱ ወይትባረክ አመ እለተ ሞቱ እግዚአብሐርን የሢፈራ ሰው ፍጻሜው ያምርለታል እንደ ኢዮብ ከደዌው ተፈውሶ ልጅ ልጅ አይቶ ይሞታል /ኢዮብ.31፡16/ ይህ ሁሉ በረከት የቅዱሳን የሁልጊዜ ፍሬ ነው፡፡
ቅዱሳን ሁል ጊዜ የሚሠሩት ሰማያዊ ድርብ ድርብርብ /እንደ ሐመረ ኖኅ/ በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ወደ 10ሩ መእረጋት ይወጣሉ፡፡ በያዙት ቀን መንገድም ኢዮባዊ ትዕግስት አብርሃማዊ ሂሩት ይስሐቃዊ ፈቃደኛነት ያዕቆባዊ ቅን አገልግሎት ጠሴፋዊ ሀዳጌ በቀልነት ሙሴአዊ ለወገን ተቆርቋሪነት እየጨመሩ በመኖራቸው ሳያውቁት የፈጣሪአቸውን ኃይል የጌትነቱ የመለኮትነቱን ድንቅ ሥራ መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡
ማዕረጋቸውን ከዚህ ይናገሩታል፡-
የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት 3 ናቸ ው እነሱም፡-
-
ጽማዌ
-
ልባዌ
-
ጣዕመ ዝማሬ ይባላሉ፡፡
የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት 4 ናቸው
-
አንብዕ
-
ኲነኔ
-
ፍቅር
-
ሁለት ናቸው፡፡
የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት ናቸው እነሱም
-
ንጻሬ መላእክት
-
ተሰጥሞ
-
ከዊነ እሳት ናቸው፡፡
የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት
-
ማዕረገ ጽማዌ፡- ይህ ማዕረግ የመጀመሪያው ነውና ማስተዋል ውስጣዊ ትዕግስትን ውስጣዊ ትህትና ውስጣዊ የራስ ሚዛንን ይዞ ማሰላሰል…… ወዘተ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ እግዚአብሔርን ብቻ መዘከር ይችሉ ዘንድ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላሉ፡፡ በዚህ ማዕረግ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያያሉ፡፡ ነገር ግን ለምን እንደሚወጡና እንደሚወርዱ አያውቁም፡፡ ዮሐንስ ሐጺር የሰፋውን ስፌት ገበያ ላይ ለመሸጥ ተቀምጦ እያለ እርሱ ግን በተመስጦ እነ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን እንዲሁም ሌሎችን መላእክት በየማዕረጋቸው እያየ ሲያደንቅ ስፌቱን የሚገዛ ሰው ቁሞ እንቅቡ ዋጋው ስንት ነው ብሎ ሲጠይቀው እርሱ የሚያየውን የሚያይ መስሎት “ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ አኮ ገብርኤል ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል” ብሎ በአንክሮ ጠየቀው፡፡ ይህን ሲለው ሰውየው ይሄስ እብድ ነው ብሎ ትቶት ሄዷል፡፡
-
ማዕረገ ልባዌ፡– ደግሞ ማስተዋል ልብ ማድረግ አሰሙኝ እንጂ ስሙኝ አለማለት ልማር እንጂ ላስተምር አለማለት የተነገረው ትንቢትና ተግጻጽ ምዕዳን ሁሉ የራሱ እንደሆኑ መገመት መመርመር ዓይነ ሥጋን ከመጽሐፍ ከስነ ፍጥረት ዓይነ ነፍስን ከምስጢር….. ወዘተ ማዋል ነው፡፡ ወይም የእግዚአብሔርን ቸርነት ማድነቅ ስለሰው ያደረገውን ውለታ ማሰላሰል ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከሰው መወለዱን በገዳም መጾሙን መገረፉን ሥጋውን መቁረሱን ደሙን ማፍሰሱን መሰቀሉን መሞቱን መቀበር መነሳቱን እያሰቡ ልብን በፍቅረ እግዚአበሔር መሰበር አንደበትን በመንፈሳዊ ሕይወት መስበር ዓላማን በገጸ መስቀል/ትዕግሥት/ ማስተካከል የመሳሰሉት ናቸው፡፡
-
ማዕረገ ጣዕመ ዝማሬ፡- ከዚህ ደረጃ ሲደርስ አንደበትን ከንባብ ልቡናን ከምስጢር ማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ አንደበታቸው ምንም ዝም ቢል በልባቸው ውስጥ ዝም አይሉም፡፡ ከአፍ እስትንፋስ ከአፋፍ ላይ ነፋስ እንደማይለይ ሁሉ ከአንደበታቸው ትዕግስት ከእጃዋው ምጽዋት ከልቡናቸው ትሕትና ከሰውነታቸው ንጽሕና አይለይም፡፡
-
የሚጸልዩትና የሚይነቡት ምስጢሩ እየገባቸው ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ ከዚህ ማዕረግ የደረሰ አንደ ባሕታዊ ለብዙ ዘመናት አቡነ ዘበሰማያት /አባታችን ሆይ/ እያለ ብቻ ሲኖር መልአክ መጥቶ ይትቀደስ ስምከ በል እንጁ ቢለው ኧረ ጌታዬ እኔስ አቡነ የሚለው ኃይለ ቃል ምስጢሩና ጣዕሙ በአፌ እንደ ጨሙ እየሟሟ አልጠገበኝ ብሏል እንዴት አድርጌ ወደፊት ልሂድ ብሎታል፡፡
የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት
-
ማዕረገ አንብዕ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ቅዱሳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ፍቅር እስከ ሞትና መቃብር የተጓዘውን የመከራ ጉዞ እያሰቡ በአንጻሩም ምረረ ገሃነመ እሳትን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እያሰላሰሉ ውሉደ አዳም ይህን ሁሉ መከራ ባለ መገንዘብ ወደ ሰፊው የፈቃደ ሥጋ ሲጓዝ በማየታቸው ሲአለቅሱ ይታያል፡፡ ያለምንም መሰቀቅ ሲአለቅሱ እንባቸው እንደ ምንጭ ይፈሳል፡፡ እንደ ሰን ውኃ ይወርዳል ይኸውም ለዚህ ዓለም ብለው የሚአለቅሱት ልቅሶ ፊትን ያንጣጣል ዓይንን ይመልጣል የቅዱሳን ልቅሶ ግን ፊትን ያበራል ኃጢአትን ያስወግዳል እርጥብ እንጨት ከእሳት ጋር በተያያዘ ጊዜ እንጨቱ ከነበልባለ እሳት ሲዋሐድ እንጨቱ እርጥብነቱን ትቶ ውኃውን በአረፋ መልክ እያስወገደ ይነዳል፡፡ ቅዱሳንም በግብር/በሥራ/ ከመለኮት ጋር ሲዋሐዱ የዚህ ዓለም ምስቅልቅል ሥራ በሰማያዊ የረጋ ሕይወት ተለውጦ አሠራራቸው አካሄዳቸው ፍጹም ሕይወታቸው መልአካዊ ይሆናል፡፡
-
ማዕረገ ኲነኔ፡- ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ሁሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል ነፍስ በሥጋ ባሕርያት ላይ ትሰለጥናለች ምድራዊ /ሥጋዊ/ ምኞት ሁሉ ይጠፋና መንፈሳዊ /ነፍሳዊ/ ተግባር ሁሉ ቦታውን ይወርሳል ያለምንም ማወላወል መንፈሳዊ ተግባር ሁሉ ይከናወናል፡፡
-
ማዕረገ ፍቅር፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ውሉደ እግዚአብሔር ቅዱሳን እንደ ፈጣሪአቸው ሁሉን አስተካክለው በመውደድ ይመሳሰላሉ አማኒ መናፍቅ ኃጥእ ጻድቅ ዘመድ ባእድ ታላቅ ታናሽ መሃይም መምህር ሳይሉ አስተካክለው በመውደድ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
-
ማዕረገ ሁለት፡- ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ባሉበት ሆነው ሁሉን ማየት መረዳት ይችላሉ፡፡ ጠፈር ደፈር ሳይከለክላቸው ርቀት ሳያግዳቸው ሁሉን በሁሉ ይመለከታሉ፡፡
የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት
-
ንጻሬ መላእክት
-
ተሰጥሞ
-
ከዊነ እሳት ናቸው፡፡
-
ማዕረገ ንጻሬ መላእክት፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ የመላእክት መውጣት መውረድ ማየት ተልእኮአቸውን ያለምንም አስተርጓሚ መረዳት ማነጋገርና ማማከር የመሳሰሉትን መፈጸም፤ ለምሳሌ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ መልአኩን 10 ዓመት ማቆም ነው፡፡
-
ማዕረገ ተሰጥሞ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደረስ በባህረ ብርሃን መዋኘት ባሉበት ሆኖ ወደ ላይም ወደታችም መመልከት መቻል….. ወዘተ ናቸው፡፡
-
ማዕረገ ከዊነ እሳት /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/፡- የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ሆኖ ጸጋ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር ሆኖ ረቆ ማመስገን ያሉበትን ሥጋ በብቻው ማየት በአካለ ነፍስ ሰማየ ሰማያትን መጐብኘት ገነት ውስጥ መግባት ናቸው፡፡
እነዚህም የቅዱሳን ማዕረጋት 10 ናቸው፡፡ /2ኛ ጴጥ.1፡4-10፣ ዮሐ.1፡40/ የአስሩ ማዕረጋት ምሳሌዎች የአስሩ ቃላት፡፡ /ዘጸ.20፡3-12፣ ዮሐ.13፡17/
በመጨረሻም ቅዱሳን የቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው ኑሮአቸውም ቅዱስ ነው፡፡
የቅዱሳን በረከታቸው አይለየን፡፡ አሜን፡፡
- ምንጭ፡- ዝክረ ቅዱሳን ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.