የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን

ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

ክፍል አንድ፡-

በጎንደር ከተማ በርካታ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን አብያተ ክርስቲያናቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ደንብ ጠብቀው፣ እንዲሁም በዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያዊያን የሥልጣኔ ደረጃ ከፍተኛ መሆንን የሚያመለክቱ አሻራዎች አርፎውባቸዋል፡፡ ይህንንም አሻራዎቻቸውን ይዘው ዛሬ ድረስ ዓለምን እያስደመሙ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም አድባራትና ገዳማት በነገሥታት፤ በባላባቶችና በሀገሬው ሰው የተተከሉ ሲሆኑ፤ በነገሥታቱ ከተተከሉት አድባራት ውስጥ በ1703 ዓ.ም በንጉሡ በዐፄ ዮስጦስ የተመሠረተችው የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አንዷ ናት፡፡

ደጀ ሰላሙ በድንጋይ ጥርብ እንደተካበ ጥንታዊነቱን ጠብቆ ግርማ ሞገሱን ተላብሶ ይታያል፤ የቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ በድንጋይ ካብ እንደታጠረ ከቅጥሩ ጋር ተያይዞ ነገሥታቱ ፀሎት ያደርጉባቸው የነበሩ በእንቁላል ቅርጽ የታነጹት ማማዎች ቁልቁል gonder ledetaአካባቢውን ለመቃኘት ያስችላሉ፡፡ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ድርቡሽ ጥንታዊውን ቤተ ክርስቲያን ሲያፈርስ ለታሪክ ምሥክርነት የቀሩት የቤተ ክርስቲያኑ ዓምዶች አሁን ያለውን ቤተ ክርስቲያን ዙሪያውን ከበው ይታያሉ፡፡ በግቢውና ውጪ የሚታዩት እድሜ ጠገብ ዛፎች፤ ቤተልሔሙ፤ የዐፄ ዮስጦስ መቃብር . . . ለቤተ ክርስቲያኑ ጥንታዊነት ምሥክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

ግቢውን እየቃኘን በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ለመሥራት ላሰብነው ዘገባ መረጃ ሊሰጡን በቀጠሯቸው ተገኝተው እኛን በመጠበቅ ላይ ወደ ነበሩት አባቶችና ወንድሞች አመራን፡፡ ከቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ አባቶችና ወንድሞች ጋር ቤተ ክርስቲያኗን በሚመለከት ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡

አመሠራረት

ዐፄ ዮስጦስ ንግሥናቸው በእናታቸው ወገን በመሆኑ በርካታ ተቀናቃኞች ነበሯቸው፡፡ ተቀናቃኞቻቸውም “ንግሥና በአባት ወገን እንጂ፤ እንዴት በእናት ወገን ይሆናል?” እያሉ በርካታ ሴራዎችን በማሴር ንግሥናቸውን ለመቀማት ጥረት አድርገውባቸው ነበር፡፡ ንጉሡ ግን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነበራቸው ፍቅር እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ ተቀናቃኞቻቸውን በጦርነት ብቻ ሳይሆን በጾምና በጸሎት ድል ያደርጓቸው ነበር፡፡

በአንድ የጾመ ፍልሰታ ለማርያም ወቅት ሱባኤ ላይ እያሉ ከተቀናቃኞቻቸው መካከል አንዱ መንግሥታቸውን ለመቀማት ጦር አዘመተባቸው፡፡ ወታደሮቻቸው በሁኔታው በመደናገጥ “ከሱባኤዎ ይውጡ፤ የመጣውን የጠላት ጦር መክተን እንመልስ ዘንድ ይምሩን፤ በጠላት ከመያዛችን በፊት ድረሱልን” በማለት አስጨነቋቸው፡፡

ዐፄ ዮስጦስ ግን አሻፈረኝ በማለት ከያዙት ሱባኤ እንደማይወጡ ለወታደሮቻቸው ይናገራሉ፡፡ ወታደሮቻቸውም ጥያቄያቸውን በመቀጠል “በሚቀጥለው ዓመት ሱባኤ ይገባሉ፤ ራስዎን፣ እኛንም ለጠላት አሳልፈው አይስጡን፤ እባክዎ ከሱባኤ ወጥተው ጠላቶቻችንን ድል እናድርግ” በማለት ተማጸኗቸው፡፡

የወታደሮቻቸው ጉትጎታ አላሳርፍ ያላቸው ንጉሡ “ጠላትን ድል አድርጌ በሰላም ከተመለስኩ በዚህ ቦታ ላይ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን እሠራለሁ” ሲሉ ስዕለት ተስለው ወታደሮቻቸውን እየመሩ ወደ ጦርነቱ ዘመቱ፡፡ በጦርነቱም ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ድል አድርገው ተመለሱ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባደረገችላቸው መልካም ነገር በመደሰት ቃላቸውን ጠብቀው የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሱባኤ ይዘውበት በነበረበት ቦታ ላይ በ1703 ዓ.ም. ተከሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በንጉሥ ዐፄ ዮስጦስ ስትመሠረት የነገሥታት ትክል በመሆኗ ብዙ ሰው በአጥቢያዋ አልነበረም፡፡ የምትተዳደረውም ሪም በሚባል ሥርዓት ነበር፡፡ /የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከአለቃው ጀምሮ እስከ ዲያቆናትና ዐቃቢት ድረስ በተዋረድ እንደ አገልግሎታቸው ከቤተ ክርስቲያኗ ጉልት እየተከፈለ መሬት ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ለአገልጋዮቹ የሚሰጣቸው መሬት ሪም በመባል ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮችም ከተሰጣቸው ሪም ላይ ከሚኖሩ ዜጎች ዓመታዊ ምርት /እህል ብቻ/ ሢሶውን ለመተዳደሪያቸው ይቀበላሉ፡፡/ በጊዜው ቤተ ክርስቲያኗን ለሚያገለግሉ ከ150 በላይ ለሆኑ ሊቃውንት ደምቢያ ከሚባል አገር እህል ይጫንላቸው ነበር፡፡

አድርሺኝ

ከጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን መተከል ጋር በተያያዘ በጎንደር ከተማ ውስጥ የሚካሔድ አንድ ሥርዓት አለ፡፡ ይህም ሥርዓት አድርሺኝ በመባል ይጠራል፡፡ ሥርዓቱ የሚከናወነው በፍልሰታ ጾም ወቅት ነው፡፡

ስለ ሥርዓቱ አጀማመር አባቶች ሲናገሩ፣ ዐፄ ዮስጦስ ወደ ጦርነት ሲዘምቱ “ጦርነቱን በልደታ ለማርያም ምልጃ ተደግፌ አሸንፌ ከተመለስኩ በፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ ማታ ማታ ካህናቱን፤ መኳንንቱንና ምእመናንን ሰብስቤ ግብዣ አደርጋለሁ” በማለት ብፅዐት ይገባሉ፡፡ እርሳቸውም ድል አድርገው ተመለሱ፤ በቃላቸውም መሠረት ግብዣ አደረጉ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም እርሳቸውን ተከትሎ በጾመ ፍልሰታ ወቅት ይህን ሥርዓት ይተገብሩት ጀመር፤ ስያሜውም “አድርሺኝ” ተባለ፡፡

አድርሺኝ በመላው ጎንደር እስከ ዛሬ ድረስ በየቤተ ክርስቲያኑና በየአካባቢው በፍልሰታ ጾም ወቅት ይከናወናል፡፡ ምእመናን ከቅዳሴ መልስ ሱባኤው እስኪያልቅ በመረጡት አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ቆሎና ጠላ ተዘጋጅቶ በእመቤታችን ስም ጽዋ ይጠጣሉ። በተለይ መነኮሳያት እናቶች በሚታደሙበት ጽዋ ላይ “ኦ! ማርያም” የሚለውን የተማጽኖ መዝሙር ይዘምራሉ። ይህ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ እመቤታችን ፊት ለፊት ስለምትቆም በፍፁም ተመስጦና መንበርከክ ያከናውኑታል።

በዋነኛነት የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ይህንን የተቀደሰ ተግባር በማስተባበርና በማስፈጸም እንዲሁም ትውፊቱ እንደጠበቀ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ዐፄ ዮስጦስ

gonder ledeta 2 ዐፄ ዮስጦስ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነበራቸው ፍቅር እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ በርካታ ታሪኮች እንዳሏቸው ይነገራል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጥምቀትን በዓል ለማክበር ዐፄ ዮስጦስ ከካህናቱ፤ ከመኳንንቱና ከምእመናን ጋር በመሆን ታቦቱን አጅበው ቀሃ ዳር ወደሚገኘው ጥምቀተ ባሕር በመውረድ ላይ ሳሉ አንዲት ሴት ከታቦቱ አጠገብ ስትጓዝ ይመለከታሉ፡፡ “ከታቦቱ አጠገብ የምትጓዘውን ሴት ከሥፍራው አርቋት፤ ከታቦት አጠገብ እንዴት ብትዳፈር ነው የምትጓዘው?” በማለት ለወታደሮቻቸው ትእዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ ወታደሮቻቸው ግን ንጉሡ ያሏትን ሴት ማግኘት አልቻሉም፡፡ እሳቸውም ሠይፋቸውን መዝዘው ቢሔዱም ከታቦቱ አጠገብ ተሰወረችባቸው፡፡

“ይህ ምሥጢር ሳይገለጽልኝ ወደ ንግሥናዬና ወደ ቤተ መንግሥቴ አልመለስም” በማለት እዚያው ድንኳን አስተክለው ሱባኤ ይገባሉ፡፡ በሦስተኛው ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻ “ከታቦቱ አጠገብ ያየኸኝ እኔ ድንግል ማርያም ነኝ” በማለት ተናገረቻቸው፡፡ ጊዜ እረፍታቸውንም መች እንደሚሆን አስታውቃና ባርካ፤ በየዓመቱ ኅዳር 21 በአክሱም ጽዮን ማርያም፤ ለአስተርእዮ ማኅደረ ማርያም እንደምገኝ ሁሉ በጥምቀት በጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም እገኛለሁ በማለት ቃል ኪዳን ገብታላቸዋለች፡፡

ምእመናን በቤተ ክርስቲያኗ የጥምቀት ዕለት ገንዘብ አዋጥተው ዝክር መዘከር የጀመሩት ከዚህ ቃል ኪዳን ጋር በተገናኘ መሆኑን አረጋውያን ያስረዳሉ።

ለውኃ ለውኃ ምን አለኝ ቀሃ

የቀሃ ወንዝ በጎንደር ውስጥ የጎንደርን ከተማ ለሁለት ከፍሎ ይልፋል፡፡ ቀሃ በጎንደር ውስጥ ታዋቂ ከመሆኑ የተነሣም “ለውኃ ለውኃ ምን አለኝ ቀሃ” እየተባለም ይነገራል፡፡ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ወቅት የልደታ ለማርያም ታቦት በዚሁ አካባቢ ታርፋለች፡፡

gonder ledeta 3 አረጋዊ መንፈሳዊ ስለ እንጦንስ የትውልድ አካባቢ ሲናገር ቀሃ ወንዝን እንደምልክትነት ይጠቀመዋል፡፡ ወንዝ ዳር፤ ወንዝ አካባቢ እንደሆነ ይነግረንና ምን ትመስላለች የሚለውን ሲገልጽ “ቀሃ ዳር ልደታ ማርያም እንዳለች ሁሉ . . . ” እያለ ያብራራል፡፡
የልደታ ውኃበጎንደር ከተማው ውስጥ በዛ ያሉ የጸበል ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ የጸበል ቦታዎች አንዱ በመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ የጸበል ቦታውም የልደታ ውኃ በመባል እየተባለ ይጠራል፡፡ በጸበሉ በርካታ ድውያን የሚፈወሱበት ሲሆን እንደ ግሸ አባይ ከምእራብ ወደ ምሥራቅ ይፈሳል፡፡

የልደታ ውኃ በተለያዩ የትርጓሜ መጻሕፍት ውስጥ ትገኛለች፡፡ መምህር ኤስድሮስ ውዳሴ ማርያምን ሲተረጉሙ “ዳዊት ዘነግሠ ለእሥራኤል አመ ይትነሥኡ ላዕሌሁ ዕልዋን ፈተወ ይስተይ ማየ እም ዓዘቅተ ቤተልሔም. . .፤ የሕይወት ውኃነት እንዳላት ከምእራብ ወደ ምሥራቅ እንደምትፈሰው እንደ ልደታ ውኃ” ይላል፡፡

በጸበሏ ዛሬም ድረስ በርካታ ሕሙማን እየተፈወሱ ይገኛሉ፡፡

ይቆየን