በዓለ ሥላሴ
ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
ወበዛቲ ዕለት ቦኡ ሥሉስ ቅዱስ ውስተ ቤተ አብርሃም ወተሴሰዩ ዘአቅረቦ ሎሙ፡፡ በከመ መጽሐፍ ውስተ ኦሪት ወአብሠርዎ ልደቶ ለይስሐቅ ወባረክዎ፡፡ በዚችም ቀን ልዩ የሆኑ ሦስቱ አካላት /ቅድስት ሥላሴ/ በኦሪት መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ወደ አብርሃም ቤት ገቡ ያቀረበላቸውንም ተመገቡ፡፡ የይስሐቅንም ልደት አበሠሩት ባረኩት አከበሩትም፡፡
መጽሐፈ ስንክሳር ዘሐምሌ ሰባት
ሥላሴ ማለት በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት አንድ አምላክ በሦስት አካላት እንዳለ ለአበው ለነቢያትና ለሐዋርያት መገለጡን አምነን የምንማረው ትምህርት ነው፡፡ሥላሴ ማለት የግእዝ ቃል ሲሆን ሦስት፤ ሦስትነት ማለት ነው፡፡
የአንድ አምላክ በሦስትነት መገለጥን ለመረዳት በኦሪት ዘፍጥረት 1፡26 ላይ በተገለጠው መሠረት “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌችን እንፍጠር” ይላል ይህ አገላለጽ “እግዚአብሔርም አለ” ሲል አንድነትን (አንድነታቸውን) “እንፍጠር” ሲል ከአንድ በላይ (ሦስትነትን) መሆንን ያስረዳል፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት 3፡22 ላይ “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው አገላለጽ ከአንድ በላይ መሆንን የሚያስረዳ ነው፡፡በኦሪት ዘፍጥረት 11፡5-7 የተጠቀሰው “ኑ እንውረድ ቋንቋቸውን እንደባልቅ”በማለት ሥላሴ የተናገሩት ከአንድ በላይ (ሦስትነት) መሆንን የሚያመለክት ነው፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት18 ላይ ሥላሴ ለአብርሃም እንደተገጹለት የሚያስረዳ ሀሳብ የያዘ አገላለጽ ሲሆን ሥላሴ ለአብርሃም በመገለጻቸው አብርሃም ሥላሴን በእንግድነት አሰተናግዷል፡፡የሥላሴ ባለሟል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በእርግናው ጊዜ ልጅ እንደሚያገን ተበስሮለታል፡፡ ዘሩ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ እንደሚበዛ በሥላሴ ቃል ተገብቶለታል፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚጠመቅበት ጊዜም የሥላሴ ምስጢር ተገልጧል፡፡ “እግዚአብሔር አብ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል እግዚአብሔር ወልድ ሲመጠቅ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ተገልጧል፡፡ ማቴ.3፡13 አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ሂዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀመዛሙርቴ አድርጉ” ማቴ. 14፡28 ሲል ሦስትነት የሚገልጽ መልእክት አስተላልፏል፡፡ እንግዲህ ሥላሴ ስንል በስም በአካል፣ በግብር የተለዩ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ይኸውም፡-
የአካል ሦስትነት፡-
-
-
አብ የራሱ መልክ፣ ገጽ፣ አካል አለው፡፡
-
ወልድ የራሱ መልክ፣ ገጽ፣ አካል አለው፡፡
-
መንፈስ ቅዱስ፡- የራሱ መልክ፣ ገጽ አካል አለው፡፡
-
የስም ሦስትነት ስንል፡- የአንዱ ስም ለአንዱ የማይሆን አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በመባል ይጠራሉ፡፡
የግብር ሦስትነት ስንል፡- አብ ወላዲ፣ አስራጺ ሲሆን ወልድ ተወላዲ ነው የተወለደውም ከአብ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ ነው፡፡ የሰረጸውም ከአብ ነው፡፡
የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ለመረዳት በሥላሴ ፈቃድ መጻሕፍት እንዳስተማሩ ሊቃውንት እንደተረጉሙልን እንጂ ማንም በገዛ ፈቃዱ ተመራምሮ አይደርስበትም፡፡
በዓለ ሥላሴ
በዓላት የሰው ልጅ በእግዚአብሔር የተደረገለትን የቸርነት ሥራ በማሰብ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ያደረጉትን ተጋድሎና ተአምራት በመስማትና በማሰማት የተደረገውን ድንቅ ነገር በመዘከር በደስታ የሚከበሩ ዕለታት ናቸው፡፡ “በቃለ አሜን ወበትፍስሕት ድምፁ እለ ይገብሩ በዓለ፡- በዓለ የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አለው” እንዳለ ቅዱስ ዳዊት መዝ.41፡5 የበዓል መከበርን ያሳወቁት ሥላሴ ሲሆኑ፤ ሥላሴ ፍጥረታትን ስድስት ቀናት ፈጥረው ሰባተኛውን ቀን ቀዳሚትን አርፈውበታል፡፡ “በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ፡፡ እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባርከውም ቀድሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፏልና” ዘፍ.1፡1-3 እንዲል
በዚህ መሠረትነት በዓል እንዲከበር የመደቡት ሥላሴ ሲሆኑ የመጀመሪያው የሥላሴ መታሰቢያና የበዓል አከባበር መጀመሪያ የሆነችው ቀዳሚት ናት፡፡
የዛሬው ሐምሌ 7 ቀንም ሥላሴ በአብርሃም ቤት ገብተው ቸርነታቸውና ፍቅራቸውን የገለጹበት፣ አብርሃምን የባረኩትና ልጅ እንደሚወልድ፣ መጻዒው ሕይወቱን የነገሩት ዕለት ስለሆነ በዓሉን ስናዘክር ሥላሴን እናመሰግናለን፡፡ ቸርነታቸው፣ ፍቅራቸው፣ ትድግናቸው እንዳይለየን እንማጸናለን፡፡ የቅድስት ሥላሴ ቸርነት አይለየን፡፡