ማቴዎስ ወንጌል

 ሐምሌ 9 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ አምስት

የተራራው ስብከት /አንቀጸ ብፁዓን/

ይህ ምዕራፍ ልዑለ ባሕርይ አምላክ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተራራ ወጥቶ ከፍ ካለ ቦታ ተቀምጦ ያስተማረው ትምህርት በመሆኑ የተራራው ስብከት በመባል ይታወቃል፡፡ ብፁዓን እያለ በማስተማሩም አንቀጸ ብፁዓን ይባላል፡፡ ጌታችን ከፍ ካለ ቦታ ተቀምጦ ያስተማረበት ምክንያት፣ መምህር ከፍ ካለ ቦታ ተማሪዎች ደግሞ ዝቅ ካለ ቦታ ተቀምጠው የሚማሩት ትምህርት ስለሚገባ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ትምህርቱ አንቀጸ ብፁዓንን እንደሚከተለው አስተምሯል፡፡

  1. “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡” ሀብትና ዕውቀት፣ ሥልጣንና ጉልበት እያላቸው የማይታበዩና የማይኮሩ፣ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው ብለው ለእግዚአብሔር አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎች ብፁዓን ይባላሉ፡፡ በመንፈስ ድሆች የሆኑ የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ጌዴዎን ኀያል ሲሆን እግዚአብሔርም እስራኤልን እንዲያድን በመረጠው ጊዜ በመንፈስ ድሃ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ “ጌታ ሆይ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሤ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፡፡ እኔ በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ፡፡” ሲል ነው ለተገለጠለት የእግዚአብሔር መልአክ የመለሰው፡፡ መሳ.6፡12-15፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል በሦስት መቶ ሰው ብቻ ምድያማውያንን ድል ካደረገ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተሰብስበው አንተ ልጅህም የልጅህም ደግሞ ግዙን ባሉት ጊዜ በመንፈስ ድሃ ሆኖ የተገኘው የጌድዮን መልስ “እኔ አልገዛችሁም፣ ልጄም አይገዛችሁም እግዚአብሔር ይገዛችኋል፡፡” የሚል ነበር፡፡ እንዲህም በማድረጉ እስከ እድሜው ፍጻሜ ድረስ ለአርባ ዘመናት ሰላምና በረከት ዘመንን አሳለፈ፡፡ መሳ.8፡22-28፡፡ አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሲሆን በመንፈስ ድሃ የሆነ ሰው በመሆኑ እኔ አፈርና አመድ ነኝ ብሏል፡፡ ዘፍ.18፡3፣ ዘፍ.18፡25፣ ያዕ.2፡23፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ሰባት ሀብታት ፍጹም ጸጋ የተሰጠው የእግዚአብሔር የልብ ሰው ሲሆን በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን ድሃ ያደረገ ሰው ነበር፡፡ ንጉሡ ሳኦል ልጁን ሊድርለት ባለ ጊዜ “ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማነኝ? ሰውነቴስ ምንድነው?” ሲል ለንጉሡ መልሶለታል፡፡1ኛ.ሳሙ.18፡18፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሲዘምርም “እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፤ ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ” ብሏል፡፡ መዝ.21፡6፡፡

  2. “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፡፡ መጽናናትን ያገኛሉና፡፡” ኃጢአታቸውን እያሰቡ እንደ አዳም፣ እንደ ዳዊትና እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ የባልንጀራቸውን ኃጢአት እያሰቡ ለንጉሥ ሳኦል እንዳለቀ ሰው እንደ ሳሙኤል /1ኛ ሳሙ.16፡1/ ሰማዕታትን አያሰቡ ለቅዱስ እስጢፋኖስ እንዳለቀሱት ደጋግ ሰዎች፣ መከራ መስቀልን እያሰበ ሰባ ዘመን እንዳለቀሰው እንደ ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ የሚያዝኑ ሰዎች ብፁዓን ይባላሉ፡፡

  3. የዋሆች ብፁዓን ናቸው ምድርን ይወርሳሉና፡፡” ቂም በቀል የማያውቁ፣ አንድም ሰውነታችንን መክረን አስተምረን ማኖር እንደምን ይቻለናል? ብለው በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን የሚኖሩ፣ በሞኝነት ሳይሆን አውቀው ስለ እግዚአብሔር ብለው የሚተው ኃዳግያነ በቀል የሆኑ ሰዎች ብፁዓን ናቸው፡፡ ዳዊት እግዚአብሔር በእጁ የጣለለትን ጠላቱን ሳኦልን መግደል ሲችል እራርቶ የተወው በሞኝነት ሳይሆን በየዋህነት ነው፡፡ 1ኛ.ሳሙ.24፡1-22፡፡ ጸሎቱም “አቤቱ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤” የሚል ነበር መዝ.131፡1፡፡ የዋሃን ይወርሷታል የተባለችው ምድር መንግሥተ ሰማያት ናት፡፡ ምድር መባሏም ምድር አልፋ እርሷ የምትተካ፣ በምድር በሚሰራ የጽድቅ ሥራ የምትወረስ፣ ምድራውያን ጻድቃንም የሚወርሷት ስለሆነች ነው፡፡ “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛየቱ ምድር አልፈዋልና” ራእ.21፡1፣ “ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም” ራእ.20፡11፣ “እነሆ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፡፡ የቀደሙትም አይታሰቡም፡፡” ኢሳ.65፡17፣ “ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይፈታል፡፡ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡”

  4. “ስለጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው ይጠግባሉና፡፡” ስለጽድቅ ብለው ረኃቡንና ጥሙን ታግሰው፣ የእግዚአብሔር መንግሥት በመብል በመጠጥ አትወረስም፣ አንድም ቢፈጽማት የእግዚአብሔርን መንግሥት የምታሰጥ አትወረስም፣ አንድም ቢፈጽሟት የእግዚአብሔርን መንግሥት የምታሰጥ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ የሆነ እምነትን ተስፋንና ፍቅርን እንጂ መብል መጠጥን አትሰብክም አንድም ልብላ ልጠጣ በምትል ሰውነት ወንጌል አትዋሐድም /ሮሜ.14፡19/ መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም ባንበላ ምንም አይጐድልብንም ብንበላም ምንም አናተርፍም /1ኛ.ቆሮ.8፡8/፡፡ መብል ለሆድ ነው፣ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል፡፡ ብለው የሚጾሙ ሰዎች ብፁዓን ይባላሉ፡፡ “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ” ሲልም እውነት በሕይወታቸው ነግሣባቸው የሚኖሩትን ያመለክታል፡፡ ጾመ ሙሴ ዘዳ.9፡9፣ ጾመ አስቴር 4፡16፣ 9፡31 ጾመ ዳንኤል፣ ዳን.10፡2 ጾመ ዳዊት፣ 2ኛ ሳሙ.12፡22 መዝ.108፡24፣ ጾመ ሐዋርያት የሐዋ.13፡2 ወዘተ ተመልከት፡፡

  5. “የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፡ ይማራሉና” የሚምሩ ሲል ምሕረት ሥጋዊ፣ ምሕረት መንፈሳዊና ምሕረት ነፍሳዊ የሚያደርጉትን ማለቱ ነው፡፡ ምሕረት ሥጋዊ ቀድዶ ማልበስ፣ ቆርሶ ማጉረስ፣ ቢበድሉ ማሩኝታ እና ቢበድሉ ይቅርታ ነው፡፡ ምሕረት መንፈሳዊ ክፉው ምግባር በጐ ምግባር መስሎት ይዞት የሚኖረውን ሰው መክሮ አስተምሮ ከክፋት ወደ በጐነት መመለስ ነው፡፡ ምሕረት ነፍሳዊ ደግሞ ክፉ ሃይማኖት በጐ ሃይማኖት መስሎት የሚኖረውን ሰው መክሮ አስተምሮ ወደ ቀናው ሃይማኖት መመለስ ነው፡፡

  6. “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፡፡ እግዚአብሔርን ያዩታልና፡፡” በንስሐ ከኃጢአት እንዲሁም ከቂምና ከበቀል ንጹሓን የሆኑ ከንጽሐ ልቡና የደረሱ ሰዎች ብፁዓን ይባላሉ፡፡ “ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም፡፡ ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፡፡ ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፡፡” መዝ.15፡8፡፡ እነቅዱስ እስጢፋኖስ ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ የደረሱት ልበ ንጹሐን በመሆናቸው ነው የሐዋ.7፡56፡፡

  7. “የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና፡፡” ሰውን ከሰው፣ ሰውን ከእግዚአብሔር የሚያስታርቁ ሰዎች ብፁዓን ይባላሉ፡፡ መልከጼዴቅ የተጣሉትን ሲያስታርቅ ይውል ነበር፡፡

  8. “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡” ለመማር፣ ለማስተማር፣ ለምናኔ እንዲሁም በሃይማኖት ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ሰዎች ብፁዓን ይባላሉ፡፡ “ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፡፡ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ፡፡” ዕብ.11፡37፡፡ ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገራቸው ስለ ጽድቅ ብለው የተሰደዱትን ነው፡፡ አብርሃም ከከለዳውያን ዑር ከሀገሩ ወጥቶ በባዕድ ሀገር ሲንከራተት የኖረው ተጠብቆ የሚቆየው ተስፋ ጸንቶ ነበር፡፡ የተስፋውም ባለቤት እግዚአብሔር የተስፋውን ዋጋ እንዲያገኝ አደረገው፡፡ ያዕ.2፡23፣ ዘፍ.15፡6፣ ኢሳ.41፡8፡፡

  9. “ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔ ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲህ አሳደዋቸዋልና፡፡” በመነቀፍ፣ በመሰደድ፣ በአሉባልታ የሚፈተኑትን ፈተና በትዕግስት ማሸነፍ እና ስለ እውነት መከራን መቀበል የማያልፍና የማይለወጥ ፈጹም ሀብትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሰጣል፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፡፡” ሲል ያስተማረው፡፡

ክርስቲያን የምድር ጨው ሆኖ በምግባሩ አልጫ ሕይወት ያላቸውን ሰዎች ሕይወት ማጣፈጥ እንደሚገባውም ያስተማረው በዚሁ ክፍል ነው፡፡ ነገር ግን ጨውነቱን ትቶ አልጫ ሆኖ ቢገኝ እንኳን ሌላውን ሊያጣፍጥ ለራሱም ወደውጭ ተወርውሮ እንደሚረገጥ ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ እንደሚቀር ለምንም እንደማይጠቅም አስገንዝቧል፡፡

 

በመቀጠልም እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ እንዳትሰወር ተራራው ይገልጣታል፡፡ መብራትን ከእንቅብ በታች ሣይሆን በቤቱ ላሉ ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ያኖሩታል፡፡ መቅርዙም ከፍታ ፋናውን ይገልጸዋል ሲል ተናግሯል፡፡

 

ፍሬ ነገሩም ያለው በተራራ ላይ ያለች ከተማ እና በመቅረዝ ላይ ያለ መብራት አይሰወሩም፤ የተራራውና የመቅረዙ ከፍታ ይገልጣቸዋል የሚለው ላይ ነው፡፡ ምሥጢሩም፡-

  • እናንተ ሥራውን አብዝታችሁ ሥሩ ግድ በተአምራት ይገልጻችኋል፣

  • ከሥጋ ጋር የተዋሐደች ነፍስ ሥራ ሠርታ ልትገለጽ ነው እንጂ ተሰውራ ልትቀር አይደለም፣

  • ከሥጋ ጋር የተዋሐደ መለኮት አስተምሮ ተአምራት አድርጐ አምላክነቱን ሊገልጽ ነው እንጂ ተሰውሮ ሊቀር አይደለም፡፡

  • የተሰቀለ ጌታ ሞቶ ተነሥቶ አምላክነቱን ሊገልጽ ነው እንጂ ሞቶ ሊቀር አይደለም፡፡

  • ወንጌል በአደባባይ ተገልጻ ልትነገር ነው እንጂ ተሰውራ በልባችሁ ልትቀር አይደለም፡፡ ማለት ነው፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡” በማለትም እግዚአብሔር የሚከበርበትንና የሚመሰገንበትን ሥራ እንዲሠሩ ተናግሯል፡፡

 “ሕግንና ነቢያትን ለመሻር ነው የመጣው” የሚለውን የአይሁድ አሉባልታ ለማጥፋት ሕገ ኦሪትንና ትንቢተ ነቢያትን ለመሻር ሳይሆን ለመፈጸም የመጣ መሆኑን ያስረዳውም በዚሁ ክፍል ነው፡፡ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የውጣ አንዲት ነጥብ እንደማታልፍ አረጋግጧል፡፡ አትግደልን በአትቆጣ /ማቴ.5፡22/፣ አታመንዝርን “ወደሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ አመንዝሯል” /ማቴ.5፡28/ በሚለው ላጸናቸው መጥቻለሁ ማለቱ ነው፡፡ ከዚህ የወጣ ግን ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ እንደሚቀር አስገንዝቧል፡፡ ይህም ሕገ ኦሪትን ሽሯል ለሚሉ ለዘመናችንም ተረፈ አይሁድ ታላቅ መልስ ነው፡፡ ስለመሰናክል ሲያስተምርም ዓይንህ ብታሰናክልህ አውልቀህ ጣላት፡፡ እጅና እግርህም ቢያሰናክሉህ ቆርጠህ ጣላቸው ብሏል፡፡ 

 

ዓይን የተባለች ሚስት ናት እጅ የተባለ ልጆች፣ እግር የተባሉ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ምሥጢሩም ሚስትህ ያልሆነ ሥራ ላሰራህ ብትለህ ፈቃዷን አፍርስባት፡፡ ዛሬ በዚህ ዓለም የሚስትህን ፈቃድ ፈጽመህ ኖረህ ኋላ ገሃነም ከምትገባ በዚህ ዓለም የሚስትህን ፈቃድ አፍርሰህ ኖረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና፡፡ ወድቀው ይነሱ በእጅ ዘግይተው ይከብሩ በልጅ እንዲሉ ልጆችህ ያልሆነ ሥራ እናሰራህ ቢሉ ፈቃዳቸውን አፍርስባቸው፡፡ በዚህ ዓለም የልጆችህን ፈቃድ ፈጽመህ ኖረህ ኋላ ገሃነም ከምትወርድ በዚህ ዓለም የልጆችህን ፈቃድ አፍርሰህ ኖረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና፡፡ እግር የተባሉ ቤተሰቦችህ ምክንያተ ስሕተት ሆነው ያልሆነ ሥራ እናሠራህ ቢሉህ ፈቃዳቸውን አፍርስባቸው፤ በዚህ ዓለም የእነሱን ፈቃድ ፈጽመህ ኖረህ ኋላ ገሃነም ከምትገባ ፈቃዳቸውን አፍርሰህ ኖረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና አንድም እንደ ዓይንህ፣ እንደ እጅህ እና እንደ እግርህ ማለትም እንደራስህ የምትወደው ባልንጀራህ ያልሆነ ሥራ አሠራሃለሁ ቢልህ ፈቃዱን አፍርስበት ማለት ነው፡፡

 

በመጨረሻም ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ፤ ጥርስ የሰበረም ጥርስ ይሰበር የሚለው፣ ጠላትህ ቢራብ አብላው ቢጠማም አጠጣው” በሚል ሕገ ትሩፋት ወንጀል መተካት እንደሚገባውና በቀልም የክርስቲያኖች ገንዘብ አለመሆኑን አስተምሯል፡፡

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ቁጥር 2 ኅዳር 1989 ዓ.ም.