በንባብ ባሕል ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ

ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የንባብ ባሕልን ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አዘጋጅነት ሰኔ 28 ቀን 2006 ዓ.ም ከ8፡00-11፡00 ሰዓት በማኅበሩ ሕንፃ ላይ እንደሚቀርቡ ማእከሉ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ሁለት ሲሆኑ፤ “ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል”፤ እንዲሁም “የንባብ ባሕልን ለማሳደግ የተለያዩ አካላት ሚና” በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያረጉ የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ አበበ ገልጸዋል፡፡

ትርጉም ያለው ንባብ ምንድን ነው? የንባብ ባሕልን ያሳደጉ አገራት ልምድ ምን ይመስላል? የንባብ ልምድ በሀገራችን እና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሚመስሉ በጥናቶቹ ይዳሰሳሉ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል በየዓመቱ በሀገራችን የንባብ ባሕልን ለማበረታታት ከሚያዘጋጀው የመርሐ ግብር አካል አንዱ ሲሆን፤ ጥናቶቹም የንባብ ባሕላችን ምን ላይ እንደሚገኝ የሚዳስሱና የሚያነብ ትውልድን ለመፍጠር ምን መደረግ እንዳለበት የሚያመላክቱ መሆናቸውን አቶ ሰይፈ ጠቁመዋል፡፡

ይህ የንባብ ጉባኤ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ በንባብ ባሕል ላይ የሚሠሩ አካላት፣ ምሁራን፤ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት፤ እንዲሁም ምእመናን ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡