የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት ቊ.፫/፳፻፭ ዳሠሣ

ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐለም መድረክ የምትታወቀው በጥንታዊነቷ ብቻ ሳይሆን አርቆ አሳቢና ጥበበኛ በሆኑ ሊቃውንት አባቶች አማካኝነት፣ ለዘመናት ተጠብቀው በቆዩ ቁሳዊና ቁሳዊ ባልሆኑ መንፈሳዊ ሀብታት ጭምር ነው፡፡ እነዚህ የቤተክርስቲያን አባቶች በየገዳማቱና አድባራቱ ጠብቀው ያቆዩት የእውቅት ሀብት በዚህ ዘመን ለጥናትና ምርምር ከፍተኛ ምንጭና ገና ያልተነካ የጥናት መዳራሻ ነው፡፡ እነዚህ አባቶች በየድርሳናቱ፣ በየጽሑፉ፤ በሥዕላት እና በቅርሶች ከትበው ያቆዩትን ዕውቀትና ጥበብ ለቤተ ክርስቲያን ልጆችና ለሣይንሱ ማኅበረሰብ ለማስተላለፍ የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት አሳትሞ ማሠራጨት ከጀመረ ሦስት ዐመታት አልፈዋል፡፡ በዚህ ዐላማ መሠረት ለሦስተኛ ጊዜ ያዘጋጀውን የጥናት መጽሔት በቅርብ ጊዜ አሳትሞ ለሥርጭት አብቅቷል፡፡ ይኽ ሦስተኛ ዕትም ሰባት ጥናታዊ ጽሑፎችን የያዘ ሲሆን ሦስቱ በዐማርኛ ቋንቋ፣ ዐራቱ ደግሞ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ጽሑፍ በሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን የተዘጋጀ ሲኾን ጸሐፊው በቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራዎች ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶችና ምርምሮች እርስ በርሳቸው ያላቸውን ተዛማጅነትና ልዩነት በጥንቃቄ በመቃኘትና በመረጃ ላይ በመመሥረት የሐሳብ ልዩነታቸውን ለማጥበብ የሞከሩበት ጥናት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥናቱ በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍትና ትምህርት የተንጸባረቁትን የቅዱስ ያሬድን ኹለንተናዊ አስተምህሮ ከነገረ መለኮት አንጻር ይተነትናል፡፡ ከጥናቱ ግኝቶች መካከል ለኢትዮጵያ ሊቃውንት የዕውቀታቸው፣ የብቃታቸውና የፍልስፍናቸው ልዩ መገለጫ የሆነው የግእዝ ቅኔ ከዜማ ድርሰት ጋር እንደ ተጀመረ በጥናቱ ታይቷል፡፡ በጥናቱ የታየው ዐዲስ ግኝት ደግሞ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት ለዐማረኛ የግጥም ምጣኔ /ልኬት/ መሠረት መኾኑን ነው፡፡

ቀጣዩ ጽሑፍ የቤተ ክርስቲያንን አሻራ በሸካቾ ብሔረሰብ ውስጥ የሚዳሥሥ ሲኾን የተጻፈውም በቀሲስ ወንድምስሻ አየለ ነው፡፡ ጸሐፊው በጥናታዊ ጽሑፋቸው በብሔረሰቡ የትበሀል፣ ሥርዐተ አምልኮ፣ የባዐላትና የክብረ ቅዱሳን ዕለታት አካባበር፣ የቦታና የቅዱሳን ስያሜ እንዲሁም የቀን አቆጣጠር አደረጃጀትና ስያሜ ላይ ቤተክርስቲያን ያላትን ጉልህ አሻራ በሰፊው ዳሥሥዋል፡፡ በማጠቃለያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ላይ ያላትን አሻራ ለማሳየት በሸካቾ ብሔረሰብ የታየው የቤተ ክርስቲያን አሻራ ጠንካራ ማሳያ ሊኾን እንደሚችል በመጠቆም ጽሑፋቸውን ይቋጫሉ፡፡

በዶ/ር ዐለማየሁ ዋሴ የተጻፈው ሥስተኛው ጽሑፍ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎችና እንስሳት እንዲሁም ለሰዎች መገለገያ የሆኑ የአረንጓደ ተፈጥሮ ቦታ መገኛ የሆኑ ተፈጥሯዊ ደኖችን በመጠበቅ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ረጅም ታሪክና ልዩ ድርሻ የሚዳሥሥ ነው፡፡ ጸሓፊው አብያተ ክርስቲያናት እግዚአብሔርን ማምለክና ሃይማኖታዊ ተግባር መፈጸም ተቀዳሚ ዐላማቸው /ተግባራቸው/ ቢሆንም በዋጋ ሊተመን የማይቻል ልዩ የኾኑና ጥብቅ ሥነ ሕይወታዊ ቦታዎች መገኛ ማእከል በመኾን እንደሚያገለግሉ ይገልጻሉ፡፡ አጥኝው የቤተ ክርስቲያን ደኖች የሀገር በቀለ ዝርያዎችን ያካተቱ ቀደምትና እየጠፉ ያሉ ዛፎች ቅሪት መኾናቸውን አንክሮ በመሥጠት ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ደኖች ክብር ያላቸው የሃይማኖት ቦታዎች ኾነው እንደሚቀጥሉ ሁሉ ተፈጥሯዊ ጥብቅ ደኖችን በመጠበቅም ቀዳሚ ትኩረት ሊያገኙ እንደሚገባ አበክረው ያስረዳሉ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎችን የጥናት ቦታቸው ወሰን በማድረግ የቤተ ክርስቲያኗ ደኖች ባጋጣሚ ተጠብቀው የቆዩ ሳይኾኑ የጥበቃ ጥረታቸውን ሥነ መለኮታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመክንዮ በሚሠጡ የቤተ ክርስቲያኗ ቁርጠኛ ምእመናን/ተከታዮች/ ጥብቅ ጥበቃና ጥረት መኾኑን ይተነትናሉ፡፡ በመጨረሻም አጥኝው በእነዚህ የቤተ ክርስቲያኗ ደኖች ላይ በዛ ያሉ ሥነ ምኅዳራዊና ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖዎች እየተጋረጡባቸው እንደኆነ በመግለጽ የመፍትሔ ሐሳብ አስቀምጠዋል፡፡

ይኽ ጥናት በቤተ ክርስቲያን ደኖች ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች የሚገልጽ ሲሆን ቀጣዩ የዶ/ር ጥጋብ በዜ ጥናት ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እየገጠማት ያለው ሌላኛውን የተግዳሮት ገጽ ያሳየናል፡፡ የመጀመሪያው ተግዳሮት ውስጣዊ፣ ሁለተኛው ደግሞ ዐለማቀፋዊ ይዘት ያለው ሲኾን የሁለቱም ተግዳሮቶች መነሻ ግን በክብካቤ እና የጥበቃ ጉድለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከክርስትና መጀመር ጀምሮ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ስለነበራት ይዞታ በመተንተን ዶ/ር ጥጋብ ብቸኛውንና ዋንኛውን የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ማለትም ዴር ሡልጣንን በተመለከተ ስላለው ያልተረጋጋ ሁኔታ በዎፍ በረር ያስቃኙናል፡፡ በጥናቱ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በቅድስት ሀገር የሚገኙ ይዞታዎቻቸውን እንዴት እንዳጡና ከ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይኽን ቅዱስ ሥፍራ ለማስጠበቅ ከግብጾች ጋር በምን ዐይነት የተንዛዛ ክርክር እንደተጠመዱ ይተርኩልናል፡፡

ወደ ቀጣዩ ጥናት ሥናልፍ ደግሞ በዝዋይ ሐይቅ በሚገኙ ገዳምና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ትኩረት አድርጎ የተሠራውን የአቶ ቡሩክ ወልደ ሰማያትን ጥናት እናገኛለን፡፡ ጥናቱ በዝዋይ ደሴያት ውስጥ በሚገኙ ቅዱሳት መካናት የሚገኙ በዋጋ ሊተመኑ ያማይቻሉ ቅዱሳት መጻሕፍትና ንዋያተ ቅዱሳት ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ የጥናቱ አዘጋጅ በቦታው የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን በዝርዝር በማስቀመጥና ቅርሶቹ በቊጥር ብዙ፣ በዐይነት ግን የማይተኩ መኾናቸውንና የአጠባበቅና የአያያዝ ሥርዐቱ በቂ ያለመኾኑን በመግለጽ ሊወሰዱ ይገባቸዋል የሚሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች በመጠቆም ጥናቱን ይቋጫሉ፡፡

በአቶ ሒንጋቡ ሖርዶፋ የተዘጋጀው ስድስተኛው የጥናት ወረቀት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ውስጥ በሚገኙ የዕፅዋት ዐይነቶች፣ አጠቃላይ መዋቅርና ብዝኀ ሕይወት ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ የጽሑፉ ዋና ዐላማም በገዳሙ ውስጥና በአካባቢው ያሉ የዕፅዋት ዘሮችንና አትክልቶችን ዐይነት፣ ስብጥርና መዋቅር መዳሠሥ ነው፡፡ ጥናቱ በገዳሙ ደን ውስጥ ያለው የዕፅዋት ዐይነትና ስብጥር በመንግሥትና በግል ከተያዙት የደን ልማቶች በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም በገዳሙ ደን ውስጥ ያሉት የዕፅዋት ዝርያ ልዩ መኾንና ተፈጥሮዊ ስብጥር (መስተጋብር) ጉላ ያለ መኾኑን አሳይቷል፡፡ በመጨረሻም የገዳሙ ደን ከዚህ በተሻለ ትኩረት ቢጠበቅ በውስጡ ያለው ብዝኀ ሕይወት የተፈጥሮን ሚዛን ለመጠበቅና እንደገና ሞተው ሊነሡ የማይችሉ ውድ የዛፍ ዐይነቶች እንዳይጠፉ በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት በመጠቆም ጥናቱን አጠቃልሏል፡፡

በአቶ ዮሐንስ አድገህ የቀረበው የመጨረሻውና ሰባተኛው የጥናት ወረቀት ደግሞ ኦሮምኛ ቋንቋን ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርትና ሃይማኖታዊ አገለግሎት በመጠቀም ረገድ ያሉ ተግዳሮቶችንና ምቹ ኹኔታዎችን ይተነትናል፡፡ ጥናቱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ እንደ ተቋም በአጠቃላይ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት፣ በተለይም በኦሮምኛ ቋንቋ ጠቀሜታ ላይ ያላትን በጎ (አዎንታዊ) አመለካከት አሳይቷል፡፡ ሆኖም ግን የሃይማኖቱን ጽንሰ ሐሳብ የሚሸከሙ አቻ ሙያዊ ቃላት እጥረት፣ የገንዘብና የሰው ሀብት እጥረት፣ ቤተ ክርስቲያን ግልጽ የኾነ የቋንቋ መመርያ የሌላት መኾኑ፣ የተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ላይ ያላቸው የግዛቤ እጥረት፣ የቋንቋ መብዛት ለሀገር አንድነት እንቅፋት ይኾናል የሚል ፍርሃትና የመሳሰሉት የኦሮምኛ ቋንቋ በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አግልግሎት ላይ በሚጠበቅበት ደራጃ እንዳያገለግል ተግዳሮቶች መኾናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጥናቱ፣ የኦሮምኛ ቋንቋ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ጥቅም ላይ መዋሉ እየጎለበተ መምጣቱንና በተለይም ማኅበረ ቅዱሳን የኦሮምኛ ቋንቋን በመጠቀም በኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን የቋንቋውን ተናጋሪዎች ለመድረሥ እየተጋ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም በአፍ መፍቻ ቋንቋ መጠቀም ያለውን ሥነ ትምህርታዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ሥነ ማኅበራዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ፣ ቤተ ክርስቲያን ኦሮምኛንም ኾነ ለሌሎችንም የሀገሪቱን ቋንቋዎች በመጠቀም ብዙኃኑን ምእመን ማስተማር እንዳለባት በማሳሰብ ጥናቱን ቋጭቷል፡፡

እንግዲህ ለመነሻ ይህን ያህል ካልን ሙሉውን ጽሑፍ ከጥናት መጽሔቱ እንዲያንቡ መልእክታችን ነው፡፡ ጥናት መጽሔቱን ለማግኘትና ጥያቄ ካልዎት በ mkidusantmaekel@yahoo.com ወይንም በ +251-11-155-99-34 ሊያገኙን ይችላሉ፡፡