የዱባይ ሻርጃ አጅማን ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ተከበረ፡፡

 

መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

እርቅይሁን በላይነህ

በሊባኖስ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትና አካባቢው ክብረ በዓሉ የተካሄደው በዱባይ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ላይ በተጣለ ድንኳን ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ በበዓሉ ታድመዋል፡፡

dubai

ከ20 ዓመት በፊት የተመሠረተችው የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረቷ ምክንያት ከሆኑት ምእመናን በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ከአዲስ አበባ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተጋብዘው የሄዱ መምህራን ክብረ በዓሏን ለማድመቅ በቦታው ተገኝተዋል፡፡

ይህ 20ኛ የምሥረታ በዓል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ፣ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው መነባነብና ግጥሞች፣ የሕፃናት ዝማሬዎች፣ በትዳር ሕይወት ውስጥ ያሉ እኅት ወንድሞች መዝሙራት፣ የቤዛ ብዙሃን የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራንና የቤተ ክርስቲያኒቱ ዲያቆናት መዝሙራትን አካቶ በዓሉ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ 10 ዕድለኞችን አሸናፊ ያደረገ ዕጣ የወጣ ሲሆን የ1ኛ ደረጃ ባለዕጣ የመኪና ባለዕድል ሆኗል፡፡ በክብረ በዓሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መመሥረትና 20 ዓመታትን በገንዘብ በዕውቀትና በጉልበት እየረዱ ላሉ አገልጋዮች ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ አይከልና በትረ ሙሴ የተሸለሙትና ከተሸላሚዎች ቀዳሚው የሆኑት ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ መርሐ ግብሩን በጸሎት ከመዝጋታቸው በፊት ባደረጉት ንግግር “እናንተ የእኛ ሽልማቶች ጌጦቻችን ናችሁ” ብለዋል፡፡