ለአብነት መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ
የካቲት 12 ቀን 2006 ዓ.ም.
ህሊና ሲሳይ ከሐዋሳ
በማኅበረ ቅዱሳን ሐዋሳ ማዕከል የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ለግቢ ጉባኤያት የአብነት መምህራን ከጥር 21-23 2006 ዓ.ም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
በሐዋሳ ማዕከል መሰብሰቢያ አዳራሽ ሥልጠናው የተሰጣቸው የአብነት መምህራን ከሲዳማ፣ጌዲኦ፣አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከበንሳ፣ ዲላ፣ ይርጋጨፌ፣ ወንዶገነት፣ አርቤ ጎና፣ ሀገረ ሰላም፣ አማሮ፣ አለታ ወንዶ፣ እና ሐዋሳ ወረዳ ቤተ ክህነት የተመረጡ 13 የአብነት መምህራን ሲሆኑ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው ትምህርተ ኖሎት፣የአብነት ትምህርትን የማስተማር ዘዴ፣የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እና የባለ ድርሻ አካላት ሚና በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች በውይይት፣ በገለጻ፣ እና በልምድ ልውውጥ መልክ በአሠልጣኝነት የተጋበዙት የአብነት መምህራንና የዩኒቨርስቲ መምህራን ሥልጠናው ሰጥተዋል፡፡
በሥልጠናው ወቅት የአብነት መምህራኑ በሀገረ ስብከቱ በካህናት እጥረት የተነሳ የገጠረ አብያተ ክርስቲያናት እየተዘጉና አብዛኛዎቹ የተሟላ አገልግሎት እንደማይሰጥባቸው ገልጸው በሀገረ ስብከቱ አዳዲስ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱና ያሉትን ጥቂት ትምህርት ቤቶች ማጠናከር የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የአብነት ትምህርት መምህራኑ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ገልጸዋል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ ዋና ዋና ፈተናዎች ናቸው ተብለው ከተነሱት መካከል፡-
-
የተማሪዎች ቤተሰብ ተጽእኖ፣
-
በገጠር አብያተ ክርስትያናት ብቁ እና በቂ መምህራን አለመኖር፣
-
በተለያየ ምክንያት መምህራን ለማስተማር ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆን፣
-
የአብነት መምህራን ከከተማ ወደ ገጠር እየተመላለሱ ማስተማር፣
-
የተማሪዎች የግንዛቤ ችግር እና ፍላጎት ማነስ እንዲሁም ርዕይ አለመኖር፣
-
የሰበካ ጉባኤ ለአብነት ትምህርት ትኩረት አለመስጠት፣
-
ለሚያስተምሩ መምህራን ከሀገረ ስብከቱ ምንም አይነት ማበረታታት አለመኖር፣
-
ለአብነት መምህራን በቂ ክፍያና ትኩረት አለመኖር
-
የአብነት መምህራን ከገጠር ወደ ከተማ መፍለስ የሚሉና ሌሎችም ምክንያቶች ተጠቅሷል፣
የአብነት መምህራኑ አክለው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የአብነት ትምህርት ባለድርሻ አካላት ማለትም ሀገረ ስብከቱ፣ወረዳው ቤተ ክህነት፣ ሰበካ ጉባኤ፣ማኅበረ ቅዱሳን፣ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች እንዲሁም መላ ህዝበ ክርስቲያን ይህንን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት መረባረብ እንደሚገባ የተነሳ ሲሆን ይህ ሳይሆን ቢቀር ግብ ችግሩ የከፋ ደረጃ እንደሚደርስ የአብነት መምህራኑ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም እንደዚህ አይነት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተጠናክሮ ቀጥሎ ሌሎች የአብነት መምህራንም እንዲሳተፍ ማድረግ እንደሚገባና መቋረጥ እንደሌለበት የአብነት መምህራኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡