በስልታዊ ዕቅድ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ

ታኅሣሥ 22 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ


ማኅበረ ቅዱሳን ከ2005 ዓ.ም – 2008 ዓ.ም ድረስ የሚተገበረውን የ4 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ ዙሪያ በ6 ማእከላት ማስተባበሪያ አማካኝነት ለሁሉም ማእከላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክክር መሰጠቱ ተገለጸ፡፡

ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል የሀገር ውስጥ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ሓላፊና ምክትል ዋና ጸሐፊ እንደተናገሩት መቀመጫቸው ባሕር ዳር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሓዋሳ፣ ድሬደዋና አዲስ አበባ ላይ በሆኑ 6 የማእከላት ማስተባበሪያ ቢሮዎች አማካኝነት ለሁለት ቀናት በስልታዊ ዕቅድ ወሳኝ ጉዳዮች፣ ዓላማ፣ ግቦችና ስልቶች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተሰጠ ሲሆን በሀገር ውስጥ ባሉ 44 ማእከላት የማእከላቱ ድርሻ ላይ ምክክር ተደርጓል ብለዋል፡፡

 

የስልታዊ ዕቅድ የግንዛቤ ማስጨበጫውን ተከትሎም የአባላት አሳብ መስጫ፣ ቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሥርዓትና የግንዛቤ ምክክርና የግቢ ጉባኤያት የገንዘብና የንብረት አጠቃቀም መመሪያ ላይ ውይይት ተደርጓልም በማለት ተናግረዋል፡፡

 

ለሁለት ቀናት በተደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ላይ 44 ማእከላት የ6ቱ የማእከላት ማስተባበሪያ አማካኝነት ሁለት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን ከጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲሱ ስልታዊ ዕቅድ አገልግሎቱን እንደሚጀምር ዲ/ን አንዱአምላክ አስረድተዋል፡፡