ST. Gebreale

እኛ የምናመልከው አምላክ ኪሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፡፡ ት.ዳን.3፥17

ታኅሣሥ 18 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኀይለ ኢየሱስ ቢያ

 

ST. Gebrealeንጉሡ ናቡከደነጾር በዱራ ሜዳ ላቆምኩት የወርቅ ምስል ካልሰገዳችሁ ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ በኀይልና በዛቻ በጠየቃቸው ጊዜ ሠለስቱ ደቂቅ በልበ ሙሉነት፥ በፍጹም እምነት፥ መልስ የሰጡበት ኀይለ ቃል ነው፡፡ ከኀይለ ቃሉ ቅዱስ ዳዊት አመንኩ በዘነበብኩ /በተናገርሁት አመንሁ፤ እንዳለ መዝ.115፥1 ፍጹም እምነታቸውንና ታማኝነታቸውን፣ ጽናታቸውን እንረዳለን፡፡ ዛሬ የምናከብረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከባቢሎን እሳት ያዳነበት ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው በብሉይ ኪዳን ዘመን ከ605-562 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነገሠው በናቡከደነጾር ዘመን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከጣዖት አምላኪና አስመላኪ ኀያላን ነገሥታት መካከል አንዱ ናቡከደነጾር ነበር፡፡ ምስሉ የቆመው በ587 ቅ/ል/ክ እንደሆነ መተርጎማን ያስረዳሉ፡፡ ዳን.3፥1 ናቡከደነጾር እስራኤላውያንን በማረከበት ዘመን ዳንኤልንና ሦስቱን ሕፃናት በልዩ ሁኔታ አክብሯቸው ነበር፡፡

 
 
      • ዳንኤልን ብርጣሶር አለው አሰበ በል አምኃ ቤል ሲል ነው
      • አናንያንም ሲድራቅ አለው ወልደ ሰቃየ አትክልት /አትክልተኛ/ ማለት ነው
      • ሚሳኤልንም ሚሳቅ አለው ፀሐቂ ተጋሂ ፍንው ለግብር መልእክት  /ትጉህ ፈጣን መልእክተኛ/ ማለት ነው፡፡
      • አዛርያንም አብደናጎም አለው ገብረ ዳጎን /የጣዖት አገልጋይ/ ማለት ነው፡፡ የቀድሞ ስማቸው ትርጉም ግን
      • ዳንኤል ማለት ፍትሕ እግዚአብሔር ዳኛ እግዚአብሔር
      • አናንያ ማለት ደመና
      • ሚሳኤል ማለት ሰምዓኒ እግዚአብሔር /እግዚአብሔር ስማኝ/
      • አዛርያ ማለት ረድኤት ማለት ነበር፡፡ ት.ዳን.1፥7

      ንጉሡ እነዚህን ሕፃናት ለሦስት ዓመት በቤተ መንግሠት ጥሩ ምግብ እየተመገቡ የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ያጠኑ ዘንድ አዝዞ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ትምህርቱን እየተማሩ በንጉሡ ቤት የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ሳይመገቡ ጥራጥሬና ውኃ እየተመገቡ በፈተና ያለፉ ነበሩ፡፡ ዳን.1፥8-21

      ጠቢባንና አስተዋዮች በመሆናቸው በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ተሾሙ፡፡ ዳን.2፥46-49 የሠለስቱ ደቂቅ በንጉሡ ዘንድ መወደድና መሾም ያስቀናቸው ባቢሎናውያን ለናቡከደነጾር “በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሸምካቸው ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ አምላክህን ያላመለኩ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉ” ብለው ከሰሷቸው ያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጣና እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ እነርሱም አንሰግድም አሉ፡፡ “ያን ጊዜም …… ዳን.3፥13-19”

      ናቡከደነጾር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሞ ለምስሉ ለማሰገድ ጥረት አድርጓል

      1. በመጀመሪያ ዐዋጅ በማወጅ ነው ይህ ዐወጅ ከተራው እስከ ባለሥልጣናቱ ያሉትን የሚመለከት ነበር፡፡ በተለይም ባለሥልጣናቱ ቀድመው በመስገድ አርአያ እንዲሆኑ ተጋብዘዋል፡፡
      2. ሁለተኛው የሕዝቡን ልብ በሙዚቃ እንዲደሰቱ በደስታው ተውጠው ሳያስቡት እንዲሰግዱ ማድረግ
      3. የመጨረሻው በማስፈራራት /ወደ እሳት ትጣላላችሁ እያለ/ እንዲሰግዱ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢያባብልና ቢጥር ሠለስቱን ደቂቅ ለማሰገድ ያደረገው ሙከራ  አልተሳካለትም፡፡

      ሠለስቱ ደቂቅ ጣዖት አናመልክም ካሉ ለምን ወደ ጣዖቱ መጡ? ቢሉ

      1. ለምስክርነት፡- የአምልኮ ጣዖትን ከንቱነትና የእግዚአብሔርን ክብር ለመመስከር
      2. ለአርአያነት፡- በምርኮ ያሉት እስራኤላውያን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ አርአያ ለመሆን ነው፡፡

      ሠለስቱ ደቂቅ ለንጉሡ የትእዛዝ ለመቀበል ምክንያት አላቸው፡፡ ግን ተቃወሙት

      1. ወጣቶችና ምርኮኞች ናቸው
      2. በንጉሡ ሥልጣን ሥር ናቸው፡፡
      3. አንዴ ብቻ ስገዱ ተባሉ እንጂ እግዚአብሔርን ተው አልተባሉም ስለዚህም፡- “ለዛሬ  ተመሳስለን እንለፍ” ማለት ይችላሉ፡፡
      4. “የንጉሡ ውለታ ይዞን ነው” ማለት ይችላሉ
      5. “በባዕድ ሀገር ስለሆንን ነው፡፡”
      6. እንኳስ እኛ በባዕድ ምድር በሰው እጅ ያለነው ቀደመቶቻችን በራሳቸው ፈቃድ ጣዖት አምልከዋል፡፡
      7. “ከሰው ጋር ሲኖሩ ሞኝ ሆኖ አህያ ሲጭኑ ሦስት ሆኖ ነው” በማለት ምክንያት መፍጠር ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ምክንያት አልሰጡም፡፡

      ከሠለስቱ ደቂቅ ሦስት ነገር እንማራለን

      ማመን፣ መቁረጥ እና ማድረግን፡፡ ሃይማኖት እነዚህን 3 ነገሮች ይፈልጋል፡፡ ሦስቱ ሕፃናት በእግዚአብሔር ፍጹም አመኑ፣ ይህንንም እምነታቸውን ሲገልጡ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል” በማለት ተናግረዋል፡፡ የመጣባቸውን ሁሉ ለመቀበል ወሰኑ ቆረጡ “አምላካችን እኛን ማዳን ይችላል ነገር ግን ፈቃዱ ከዚህ እሳት ገብተን ሠማዕትነትን እንድንቀበል ቢሆን ከእሳት እንገባለን” በማለት አንድ ልብ፣ አንድ ቃል ሆነው አቋማቸውን ገለጡ፡፡ የቆረጡትን ነገር አደረጉት፤ ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ሦስቱም ነገሮች ስለተፈጸሙ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እሳቱን አብርዶ አዳናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” በማለት የተናገረው ቃልም ተፈጽሞላቸዋል፡፡ /መዝ.33፥7/ ጠባቂ መልአካቸው ቅዱስ ገብርኤል በእሳት ውስጥ ገብቶ ከመከራ ሥጋ አድኖአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና መልአኩል ልኮ የፈጸመውን ትድግና ያየው ናቡከደነጾር “ናቡከደነፆርም መልሶ፡- መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብድናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ያደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡” ዳን.3፥28-30

      ናቡከደነጾር ሦስት ነገሮችን አስተውሏል

      1. ሠለስቱ ደቂቅ ፈጣሪያቸውን በመዝሙር ሲያመሰግኑ ሰምቷል፡፡
      2. እሳቱ በወጣቶች ላይ ምንም ጉዳት እንዳላደረሰባቸው አስተውሏል
      3. ሰው ያልሆነ ፍጡር አብሯቸው መኖሩን አውቋል ከዚህ የተነሣ አማኞችንም ፈጣሪያቸውንም አመስግኗል፡፡ “መልአኩን የላከ…. የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይመስገን” ብሏል፡፡ ዳን.3፥28

      የእግዚአብሔርን ጥበቃ ስናነሣ ጥበቃው በብዙ ዓይነት /መንገድ ነው፡፡

      1. የእግዚአብሔር ጥበቃ፡- እግዚአብሔር በመግቦቱ ዓለምን ይጠብቃል ይመራል፡፡ መዝ.22፥1፣ ማቴ.5፥45፣ ማቴ.6፥25፣ 1ኛ ጴጥ.5፥7
      2. የቅዱሳን መላእክት ጥበቃ፡- ቅዱሳን መላእክት በተልእኮ ይጠብቃሉ ይራዳሉ ያማልዳሉ፡፡ መዝ.33፥7 “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል፡፡” ይላል
      3. የካህናት ጥበቃ በማስተማርና በምክር በጸሎት ይጠበቃሉ ዮሐ.21፥15፣ 1ኛ ጴጥ.5፥2፣ ዕብ.13፥17 “ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ… ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና”
      4. የሕግ ጥበቃ ሕግ ሲያከብሩት ሰውን ይጠበቃል ይመራል፡፡ መዝ.118፥105 “ሕግህ ለእግሬ ብሥራት ለመንገዴም ብርሃን ነው”

      ከዚህም ውስጥ የቅዱሳን መላእክትን ጥበቃ ብንመለከት

      ቅዱሳን መላእክት ምንድን ናቸው? አገልግሎታቸው ምንድ ነው ብንል

      • የቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮ እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ እሑድ እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ/ካለመኖር ወደመኖር አምጥቶ የፈጠራቸው ንጹሐን ቅዱሳን ረቂቃን ፍጥረታት ናቸው፡፡ ኩፋ.2፥5-9፣ መዝ.103፥4፣ ቈላ.1፥16-17
      • ቅዱሳን መላእክት በነገድ መቶ ናቸው ማቴ.18፥11-14 ሳጥናኤል በመሳቱ 99 ነገደ መላእክት ሲሆኑ 100ኛ ነገድ አዳም ሆኗል፡፡
      • ቅዱሳን መላአክት ቁጥራቸው አይታወቅም ት.ኤር.33፥22
      • ቅዱሳን መልእክት ሕያዋን ናቸው ሞት የለባቸውም ማቴ.22፥30

      የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት በሁለት ይከፈላል

      1ኛ. እግዚአብሔርን ያለ ዕረፍት ማመስገን

      ራዕ.4፥6-11፣ ራዕ. 5፥6-14፣ ኢሳ.6፥1፣ መዝ.102፥20፣ ሄኖክ 11፥16 “ለእነርሱ ዕረፈታቸው ምስጋናቸው ነውና ያመሰግናሉ ያከብራሉም አያርፉም”

      2ኛ. ሰውን ያለ ዕረፍት ማገልገል /መጠበቅ/ ነው ማቴ.18፥10፣ ዕብ.1፥14፣ ዘፀ.13፥21፣ ዳን.6፥22 /”አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ”/፣ ዳን.12፥1

      • ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን እንዲወርሱ ያግዛሉ ይራዳሉ፡፡ ዕብ.1፥14
      • ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ወደ ፍጥረታት ለምሕረትም ለመዓትመ ይላካሉ፡፡

      ለምሕረት ሲላኩ

      ት.ዘካ.1፥12 “የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ “አቤቱ ሁሉን የምትችል ሆይ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” እያሉ እግዚአብሔርን ይለምናሉ፡፡ ሮሜ.9፥23፣ ዘፍ.19፥12-23 “….ራስህን አድን” አሉት

      ለመዓት ሲላኩ

      2ኛ ነገ.19፥35 “በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ መጣ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ ማለዳም በተነሡ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ” 2ኛ ሳሙ.24፥16

      • ቅዱሳን መላእክት ከሰው ወደ እግዚአብሔር ልመናን ምልጃን ያቀርባሉ /የምዕመናንን ጸሎት ያሳርጋሉ/ ራዕ.5፥8፣ ራዕ.8፥2-5፣ ማቴ.18፥10፣ ዮሐ.1፥52
      • ቅዱሳን መላእክት ከክፉ ነገር ሁሉ ይመልሳሉ /ወደ በጎ ይመራሉ/ ዘኁ.22፥32 የእግዚአብሔር መልአክ “መንገድህ በፊቴ ቀና አልነበረምና አቋቁምህ ዘንድ መጥቼአለሁ አለው፤ ለክፋት ተነሥቶ የነበረውን ለበጎ አደረገው፡፡
      • ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ያጽናናሉ ያበረታታሉ፡፡ 1ኛ ነገ.19፥5፣ ዳን.10፥13-21፣ ሉቃ.22፥43 “የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው” ማቴ.4፥11 “እነሆም መላእክት ሊያገለግሉት መጡ” እኛንም በችግራችን ጊዜ ሊያገለግሉን ይመጣሉ፡፡
      • ቅዱሳን መላእክት ከሰይጣን ተንኮልና ስሕተት ይጠበቃሉ ይታደጋሉ ዘፀ.23፥20-23፣ መዝ.90/91፥11-12
      • ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ለሚገዳደሩና ለሚጠረጠሩ ይቀስፋሉ  መዝ.34፥5-6

      በአጠቃላይ ስለ ቅዱሳን ምልጃ ስናነሣ 3 ነገሮች መኖራቸውን ማወቅ መረዳት ይገባናል፡፡

      1. የሚለመነው የሚማለደው እግዚአብሔር ይቅር ባይ መኖሩን ዘፀ.32፥11-15
      2. የሚለምን/ የሚማልድ አስታራቂ መልአክ/ጻድቅ መኖሩን ት.ዘካ.1፥12
      3. የሚለመንለት ሰው/ ተነሣሂ ይቅርታ ጠያቂ/ መሆን አለበት ሉቃ.18፥13፣ ዘፍ.20፥7
      • የሚለመንለት ሰው አማኝ ተነሣሂ መሆን አለበት ት.ሕዝ.14፥14፣ መዝ.33፥7
      • ለማስታረቅ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ፣ ብቃት መመረጥ መወደድ ያስፈልጋል የሐዋ.19፥11-20፣ ዘኁ12፥1
      • ለማስታረቅ በሰው ፊትም ቢሆን መወደድ መከበር ተሰሚነት ያስፈልጋል፡፡
      • በአጠቃላይ ሠለስቱ ደቂቅ በእምነታቸው ጽናት የእግዚአብሔርን ቸርነት የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ጠባቂነት በግልጽ አሳየተው አስረድተዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ነው ንጉሡ “መልአኩን የላከ.. የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ፣ የአብደናጎም አምላክ ይመስገን” ያለው፡፡
      • እኛም በክርስትናችን ጸንተን በሥነ ምግባራችን ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ከዚህ ክፉ ዓለም በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱሳን ጸሎትና ተራዳኢነት በወላዲተ አምላክ አማላጅነት ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን የስሙ ቀዳሽ የመንግሠቱ ወራሽ ለመሆን ያብቃን፡፡

      የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አይለየን

      ወስብሐት ለእግዚአብሔር

      አሜን

      ምንጭ፡- ድርሳነ ቅዱስ ገብርኤል

      • ስንክሳር ግንቦት 10 ቀን
      • መዝገበ ታሪክ
      • ትንቢተ ዳንኤል ከዘመነ ባቢሎን እስከ ዓለም ፍጻሜ፡፡