ራሔል እንዘ ትበኪ በእንተ ውሉዳ፥ ራሔል ስለልጆችዋ አለቀሰች

ኅዳር 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኀይለ ኢየሱስ ቢያ

“ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ በራማ ተሰማ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች፤ ልጆችዋ የሉምና” ማቴ.2፥18

 

ይህ የግፍ ልቅሶ 3 ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ይኸውም፡-

1ኛ. በንጉሥ ፈርዖን ዘመን እስራኤላውያን በግብፅ እያሉ ራሔል የተባለች የሮቤል/ ስምዖን ሚስት ነፍሰጡር ሆና ጭቃ ስትረግጥ የወለደቻቸውን መንታ ልጆች ከጭቃ ጋር እንድትረግጥ ተገዳ በመርገጧ “ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል” በማለት እንባዋን ወደ ሰማይ ረጭታለች ዘዳ.1፥15፡፡ እግዚአብሔርም ልመናዋን ሰምቶ፥ ሊቀ ነቢያት ሙሴን አስነሥቶ ከግብፅ ነፃ አወጣቸው (ዘፀ. 3፥7 ተመልከቱ)

 

2ኛ. በንጉሥ ናቡከደነጾር ዘመን እስራኤላውያን በባቢሎን ተማርከው 70 ዘመን ግፍ ተፈጽሞባቸው እንደ ራሔል መሪር እንባን አልቅሰዋል፡፡ ከ70 ዘመንም በኋላ በዘሩባቤል አማካይነት ነፃ ወጥተዋል ኤር.31፥15፣ መዝ.79፥3 ተመልከቱ

 

3ኛ. ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን የመወለዱን ዜና ከሰብአ ሰገል የሰማው ሄሮድስ ፥በቅንአት ሥጋዊና በፍርሃት ተውጦ፥ ጌታችንን እንዲያገኝ 144.000 ሕፃናትን ፈጅቷል፡፡ ራዕ.14፥1 በዚህም በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ ያሉ እናቶች መሪር እንባን አሰምተው ስለነበር፥ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ የመከራውን ጽናት ከራሔል መከራ ጋራ አነጻጽሮ ተናገረ፡፡ ማቴ.2፥16-18 ተመልከቱ

 

ራሔል ያዕቆብን አግብታ ዮሴፍንና ብንያምን ወልዳለች፡፡ በዚህ ምክንያት የ12ቱ ነገደ እስራኤል እናት ትባላለች፡፡ በዚህ ምክንያትም፡- የእስራኤል እናቶች ተወካይ ሆና ተጠቅሳለች፡፡ ዘፍ.28፥31 ልጆች በእስራኤላውያን ዘንድ ተወዳጅ ናቸው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ዳዊት “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” በማለት ተናገረ፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ በክብር ይያዘልና፡፡ መዝ.126፥3

 

ልጅ በመወለዱ – ከድካም ያሳርፋል

  • ስም ያስጠራል
  • ዘር ይተካል
  • ወራሽ ይሆናል

 

ነቢዩ ኤርምያስ የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች” ያለውን /ኤር.31፥15

 

ራሔል ማን ናት? ቢሉ

1.    ራሔል ወላጅ እናታችንን ትመስላለች፡፡ ራሔል የወለደቻቸውን ልጆች በሞት እንዳጣቻቸው፤ የእኛም ወላጆች/እናቶቻችን/ ወልደውን፣ አሳድገውን፣ እናቴ አባቴ ብለን ምክራቸውን አንቀበልም ይልቁኑ እናቃልላለን፤ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አንረዳም/መርዳት እየተቻለን የአቅማችንን እንወጣም፤ የእናትነት /የወላጅነት ክብር ነስተናቸዋል፡፡ ስለዚህ ሳንሞት በቁማችን አዝነውብናል፡፡ በዚህ ምክንያት ራሔል እያለቀሰች /እያዘነች/ ነው፡፡ የልጅ ጠባይ፣ የአናትነት ክብር ስለጠፋ “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኀይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።” 2ኛ ጢሞ.3፥1-6

2.   ራሔል ሀገራችን ትመስላለች

ለምን ቢሉ የሀገር ፍቅር ስለጠፋ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መግቢያ ላይ ስለ ሀገር ምንነት ሲገልጹ አገር ከነድንበሩ ከነፍቅሩ ስም ከነምልክቱ ከነትርጉም መረከባችንን ገልጸዋል፡፡

 

ነቢዩ ኤርምያስም “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” በማለት ይጠይቃል፣ መልሱ አይችልም ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ብዙዎቻችን ስለ ሀገር ምንነት ያለን አመለካከት እየተዛባ ነው፡፡ ማለትም ሁሉም ሀገሬ ነው፡፡ አገር አገር አትበሉ ማለት እየተበራከተ ነው፡፡

 

ቅዱስ ዳዊት “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ፥ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ” ብሏል መዝ.136፥5-6 ስለዚህ ስለሀገራችን ታሪክና ወግ፣ ባህል የማንነታችን መለያ ስለሆኑ ነገሮች ሁሉ ሊገደን ይገባል፡፡

 

3.   በሌላ በኩል ራሔል ቤተ ክርስቲያናችን እያዘነች /እያለቀሰች/ ነው፡፡ በ40 እና በ80 ቀን ከማየ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የወለደቻቸው ልጆቿ ስለጠፉ፣ የበጎ  ሃይማኖት ልጅ ስለጠፋ፣ የበጎ ሥነ ምግባር ልጅ ስለጠፋ፣ ቤተ ክርስቲያን እያዘነች ነው፡፡

 

ሁሉም እንደ ዔሳው ብኩርናውን /ልጅነቱን / ክርስትናውን ለምስር ወጥ /ለዚህ ከንቱ ዓለም/ እየሸጠ/ እየለወጠ ስለሆነ ነው፡፡ ዕብ.12፥16፣ ራዕ.3፥11፣ ምሳ.9፥1፣ ማቴ.22፥1 ይህ ሁሉ ጥሪና ግብዣ የእኛ ሆኖ ሳለ እኛ ግን የራሳችን ምኞትና ፍላጎት አሸንፎን ችላ አልነው ተውነው፡፡ በኋላ ግን ቅጣቱ የከፋ ነው፡፡

 

ስለዚህ ለሃይማኖትችን ለቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት፣ ለታሪካችን ለቅርሳችን ትኩረት በመስጠት የሚጠበቅብንን አደራ ልንወጣ ይገባል፡፡ “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።” ይሁዳ 1፥3፡፡ ለዚህ ያብቃን፡፡

 

4.   ራሔል እመቤታችን ናት

እመቤታችን በራሔል የተመሰለችው፡- የሥጋ እናት ወልዳ፣ መግባ በማሳደጓ ትወደዳለች፡፡ የሃይማኖት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን አባሕርያቆስ እንደ ነገረን የምንወዳት፣ እናታችን የምንላት እውነተኛ መጠጥ፣ እውነተኛ መብል ወልዳ ስለመገበችን ነው፡፡ “ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዕብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን” (ቅዳሴ ማርያም)፡፡ ታዲያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለምን አዘነች ቢሉ ሰአሊ ለነ ብሎ የሚለምን /የሚጸልይ ከፈጣሪው ጋር ስለ ኀጢአቱ ይቅርታን የሚጠቅስ ስለጠፋ ነው፡፡ እርሷ ራሷ “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” ሉቃ.1፥48 ብላለች ዳዊት “የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትሽ ይማልላሉ” ይላል ይለምናሉ ማለቷ ነው፡፡ መዝ.47፥12 እንኳን እመቤታችን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን/ እንማልዳለን” ብሏል፡፡ 2ኛ ቆሮ.5፥20

 

ነቢዩ ኤርምያስ ራሔል ስለልጆችዋ አለቀሰች መጽናናትንም እንቢ አለች ልጆችዋ የሉምና እንዳለ፡-

ዛሬም – ወላጅ እናታችን የልጅ ጠባይ ስለጠፋ አዝናለች

  • ሀገራችን የሀገር ፍቅር ከልባችን ስለጠፋ አዝናለች

  • ቤተ ክርስቲያችን የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ስለጠፋ አዝናለች

  • እመቤታችን የእናትነት ፍቅሯ ስለጠፋብን አዝናለች

  • መንግሥተ ሰማያት የሚወርሷት ሲጠፋ ታዝናለች፡፡

በአጠቃላይ የበጎ ሃይማኖትና ሥነ ምግባር ልጅ “ሄሮድስ” በተባለ በዚህ ከንቱ ዓለም አሳብ ጠፍተዋልና አለቀሰች አለ፡፡

 

የራሔል ልጆች ለመሆን የወጣቶች ኦርቶዶክሳዊ ግዴታ፡-

  1. በኦርቶዶክሳዊ እምነትና ምግባር፣ በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ፍቅር በኢትዮጵያ ጨዋነትና ቁም ነገረኝነት በሰው አክባሪነትና በመንፈሳዊ ጀግንነት የአባቶችና የእናቶች አምሳያ ልጅ ሆኖ መገኘት፡፡

  2. ሲነግሩትና ሲመክሩት የሚሰማ ሲመሩት የሚከተል ክፉና ደግን ከስሕተት ሳይሆን ከአበው ምክርና ከቃለ እግዚአብሔር የሚማር ተው ሲሉት በቀላሉ የሚመለስ ሰው አክባሪና እግዚአብሔርን ፈሪ ሆኖ መገኘት፡፡

  3. ሃይማኖቱንና የቤተ ክርስቲያን አባልነቱን እየቀያየረ እንደ ዔሣው ብኩርናውን /ክብሩን/ ለምስር ወጥ የሚሸጥ አሳፋሪ ልጅ አለመሆን፡፡

  4. ከጋብቻና ከድንግልና ሕይወት ውጭ የሆነ ሌላ የክርስትና ሕይወት ስለ ሌለ የሁሉም ዓይነት ችግር መገለጫ የሆነውን 3ኛውን ዓይነት ኑሮ ላለመኖር መጠንቀቅ ወይም ከዚያ ኑሮ ፈጥኖ መውጣት፡፡

  5. የአባቶችንና የእናቶችን ኦርቶዶክሳዊ እምነትና አምልኮ በልማድ ሳይሆን በትምህርታዊ ዕውቀት በመውረስ መፈፀም፡፡

  6. በኦርቶዶክሳዊ ቋንቋ በመጸለይና በኦርቶዶክሳዊ ዜማ በመዘመር ቅዱስ መጽሐፍን በኦርቶዶክሳዊ ቋንቋ በማንበብና በመተርጐም በመማርና በማስተማር ወዘተ…. አምልኮተ እግዚአብሔርን ከልጅነት ጀምሮ መፈጸም፡፡  ማለት በዚህ ዓይነት ኦርቶዶክሳዊ እምነትና ምግባር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በጥበብና በሞገስ ማደግ መጎልመስ “የወይፈን በሬ” መሆን ማለት እንደ ሕፃን ሳይሆን እንደ ባለ አዕምሮ የሚያስብ “የልጅ ሽማግሌ” መሆን፡፡

  7. በዚህ ዓይነት ሕይወት ሥጋዊና ዓለማዊ የሆነውን የወጣትነት ሰውነት መንፈሳዊና ሰማያዊ ማድረግ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ወጣቶች የሚጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ ነው፡፡

(ፈለገ ጥበብ 2ኛ ዓመት ቁ2 መስከረም 1992)


የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱሳን አማላጅነት ሁላችንንም ከዚህ ክፉ ዓለም ጠብቆን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሽ ለመሆን ያብቃን፡፡