በአባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላሙ ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ
የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራርና የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤያት መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ በአስተዳደርና በተወሰኑ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም ልዩነት ምክንያት ለሁለት አሠርት ዓመታት ተለያይተው በቆዩ አባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት እስከ መጨረሻው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ “የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ በአገር ውስጥና በውጪ አገር በሚገኙ አባቶች መካከል የተጀመረው ውይይት ከሁሉም ጉዳዮች በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሠራና እንዲፈጸም የማኅበሩ ፍላጎት መሆኑን ለማስታወቅና እንደ ጥያቄም ለማቅረብ ነው፡፡” በማለት መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ስለተካሄደው ስብሰባ መግለጫ የሰጡት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም ናቸው፡፡
ዋና ጸሐፊው ለመካነ ድራችን በሰጡት መግለጫ “የማኅበሩ አባላትም ሆኑ ሌሎቹም ምእመናን የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ተግተው መጸለይ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የሰላሙንና የዕርቁን ሁኔታ ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጉዳዮችን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም አንድነቷ ተመልሶ የምትሠራበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ማኅበሩ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመፈጸም ዝግጁ ነው፡፡ ስለሆነም የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መምህራን ጭምር የማኅበሩን አቋም የማስታወቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡” ብለዋል፡፡
እርቁ እንዴት ይሁን? እንዴት ይፈጸም የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጣቸው በሁለቱም ቦታዎች በሚገኙ አባቶችና በአስታሪቂ ሽማግሌዎች መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት መተው እንደሚገባ ያስታወቁት ዲ/ን ሙሉጌታ የተጀመረው እርቅ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግና እግዚአብሔርንም በጸሎት እንዲማጸን አሳስበዋል፡፡
ዋና ጸሐፊው በማጠቃለያ መልእክታቸው፡- “ፍቅር ሰላምና አንድነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ስምረት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ ለፍቅር ለመግባባትና አብሮ ለመሥራት በሰላም ለመኖር ሁሉም መጣር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ የሚያደናቅፍ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ አንድነትን የሚጠላ ፍቅርን የሚጠላ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ለዚህ ጉዳይ መትጋት ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡