የገዳማውያኑ ጸሎትና አንድምታው /በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/!!
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ሲመጣ ለሁሉም እንደሥራው ያስረክባል” /ማቴ.16፡27/ ብሎ ሲናገር እኔም ንግግሩን ስሰማ የድል አክሊልን ከሚቀዳጁ ቅዱሳን ወገን ስላልሆንኩኝ ተብረከረክኩ፡፡ ይህን ፍርሐቴንና ጭንቀቴን ሌሎች ሰዎችም እንደሚጋሩኝ አስባለሁ፡፡ ይህን ሁሉ በልቡ እያሰበ የማይደነግጥ ማን ነው? የማይንቀጠቀጠውስ ማን ነው? ከነነዌ ሰዎች በላይ ማቅን የማይለብስና አብዝቶ የማይጾምስ ማን ነው? ምክንያቱም ይኸን ሁሉ የምናደርገው ስለ አንዲት ከተማ መገለባበጥ ተጨንቀን ሳይሆን ዘለዓለማዊውን ቅጣትና ትሉ የማያንቀላፋ እሳቱም የማይጠፋውን ነበልባል ለማለፍ ነው፡፡
በየበረሀውና በየገዳማቱ የሚኖሩት አበው ወእማት ይኸንን ቃል ከሌላው ሰው በበለጠ አኳኋን ስለ ገባቸው እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለሁ፤ አደንቃቸውማለሁ፡፡ ምክንያቱም እራታቸውን ከቀማመሱ በኋላ፣ እንደውም እራታቸውን ሳይሆን ምሳቸውን ከተመገቡ በኋላ (ምክንያቱም አብዝተው የሚጾሙና የሚያዝኑ ስለሆነ እራት የሚባል ነገር አያውቁም በዜማ አምላካቸውን ያመሰግኑና መዝሙር ይዘምራሉ፡፡ እናንተም መዝሙሩን መስማት ከፈለጋችሁ ላስታውሳችሁ እና ደጋግማችሁ ዘምሩት፡፡ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን፣ ሥጋ ለባሽን ሁሉ የምትመግብ ቡሩክ እግዚአብሔር ሆይ! መልካሙ ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን፡፡ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ይገባኻል! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህም የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተመላን አድርገን፡፡”
ይህ ዝማሬ በተለይም የመጨረሻው ስንኝ አንክሮ የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም መብል በባሕርይው የድካምና የመወፈር ስሜትን የሚያመጣ ቢሆንም በመነኰሳቱ ዘንድ ግን በነፍስ ላይ ሲያበራና ነገረ ምጽአትን ሲያሳስብ እንመለከተዋለን፡፡ እነዚህ ሰዎች እስራኤል ሰማያዊው መና ከተመገቡ በኋላ ምን እንዳገኛቸው ተምረዋል፡፡ እንዲህ እንደተባለ፡- “የተወደደውን ጥጋብ አቀናጣው፤ ሰባ፤ ወፈረ፤ ሰፋ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ” /ዘዳ.32፡15/፡፡ ዳግመኛም ሙሴ፡- “በበላህና በጠገብህም ጊዜ… እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ” እንዲል /ዘዳ.6፡11-12/፡፡
እስኤላውያን የተወደደውን ምግብ ከበሉ በኋላ አሳፋሪ ነገርን ለማድረግ ጀመሩ፡፡
እናንተስ ይኼን የመሰለ ነገር በእናንተ ዘንድ እንዳይሆን ትገነዘባላችሁን? ምንም እንኳን ለድንጋይ፣ ወይም ለወርቅ ምስል በግ ወይም ከብት ባትሠዉም የራሳችሁን ነፍስ ስለሠዋችሁ መዳናችሁን እንዴት እንደምታጥዋት እና እንዴት ያለ ቁጣ እንደሚደርስባችሁ ተመልከቱ፡፡ እነዚህን መነኰሳት ስንመለከት ይኼን የመሰለ ውድቀት በእነርሱ እንዳይደርስ በመፍራት ምግባቸውን ከተመገቡ በኋላና በጊዜ ጾማቸው መካከል ሁሉ ስለዚያች አስፈሪ ቀን እና ስለ አስጨናቂው የፍርድ ወንበር ያስባሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ መነኰሳት እንኳን በጾም ሌሊቱን ሁሉ በመሬት ላይ ተኝተው እንቅልፍን በማጣት በንቃትና ማቅን በመልበስ እልፍ ጊዜ እየደጋገሙ ስለዚያች ቀን በማሰብ የሚተጉ ከሆነ የምግብ ክምር በጠረጴዛችን ላይ ከምረን ስንጀምርም ስንጨርስም የማንጸልይ ትሩፋተ ሥጋ ትሩፋተ ነፍስ የሌለን እኛስ ይኼን የምናደርገው መቼ ይሆን?
ስለዚህ ምግበ ሥጋ ብቻ በምግብ ጠረጴዛች እንዳንከምር ይኼን የመሰለ ጣዕመ ዝማሬ እና ትርጕሙን እንናገር፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቅሙን እየተመለከትን በማዕዳችን ዙርያ እንድናመሰግን እና ለሆድ ብቻ ብለን የምናደርገውን ሩጫ በማስወገድ የመላእክትን ሥርዓት ወደ ቤታችን እናስገባ፡፡ ከመብላታችሁ በኋላ መልካም እንዲሆንላችሁ ይኸን ታደርጉ ዘንድ ይገባችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ብያንስ እንኳን ለምነግራችሁ ቃል ፈቃደኞች ስላልሆናችሁ ይኸንን ጣዕመ ዝማሬ አድምጡና ከዛሬ ጀምራችሁ ከማዕዳችሁ በፊትም ይሁን በኋላ ምስጋናን ተለማመዱ፡፡
“ብሩክ እግዚአብሔር ሆይ!” ነው ያሉት፡፡ እነዚህ መነኰሳት የሐዋርያትን ትእዛዝ ሲፈጽሙ እንመለከታቸዋለን፡፡ ሐዋርያት እንዲህ ብለው ነበርና፡- “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” /ቈላ.3፡17/፡፡
ሲቀጥሉ ደግሞ የእግዚአብሔር መግቦት ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለሁል ጊዜ እንደሆነ ሲናገሩ፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን” ነው ያሉት፡፡ ይኼን ትእዛዝ ደግሞ፡- “እግዚአብሔር ምግባችሁን ይሰጣችኋልና አትጨነቁ” ማለት ነው፡፡ እናንተ ከአንድ ንጉሥ ጋር እየኖራችሁ ንጉሡ ምግባችሁን ሁሉ ከግምጃ ቤት እያወጣ የሚሰጣችሁ ከሆነ በጭራሽ ስለምትበሉት ነገር አታስቡም፤ ምግብ እንደሚሰጣችሁ ተስፋችሁን ሁሉ በንጉሡ ላይ ጥላችሁታልና፡፡ እንግዲያስ ከዝናብም በላይ በእናንተ ላይ እነዚህን ነገሮች ሊያዘንም የሚችለውን እግዚአብሔር በበለጠ አኳኋን ተስፋ እያደረጋችሁ ስለ አንዳች ነገር ልትጨናነቁ አይገባችሁም፡፡ አዎ! እነዚህ መነኰሳት ራሳቸውንና በእግራቸው ለሚተኩት ደቀመዛሙርቶቻቸው ያስተምሩ ዘንድ ይኼን መዝሙር ደጋግመው ይዘምራሉ፡፡
ከዚህ በኋላ እነዚህ መነኰሳት ለራሳቸው ብቻ ያመሰግናሉ እንዳይባል፡- “ሥጋ ለባሽንም ሁሉ የምትመግብ” ይላሉ፡፡ ስለዚህ በዓለም ሕዝብ ፈንታ እነርሱ ያመሰግናሉ፤ እንደ ዓለም ሁሉ አባቶች እግዚአብሔርን ይባርካሉ፤ ጽኑ ፍቅረ ቢጽን /የወንድም ፍቅርን/ ይለማመዳሉ፡፡ ወንድሞቻቸውን እግዚአብሔር ስለመገበላቸው ያመሰግናሉ እንጂ አይጠሉም፡፡
እንግዲህ በቀደሙትና በእነዚህ የምስጋናቸው ቃል እንዴት አመስጋኝነትን፣ እንደገለጹና ዓለማዊ ምቾትን እንዳራቁ ተመለከታችሁን? እግዚአብሔር ሥጋ ለባሹን ሁሉ የሚመግብ አምላክ ከሆነ የሚያመሰግኑትን ደግሞ የበለጠ ይመግባቸዋል፤ በዓለም ኑሮ ለተወጠሩት እንኳን የሚመግብ ከሆነ ከዓለማዊ ምኞት ራሳቸውን ላራቁ ደግሞ ይበልጥ ይመግባቸዋል፡፡
ይኼን ግልጽ ያደርግ ዘንድ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ከብዙ ድንቢጦች እናንተ አትበልጡምን?” /ሉቃ.12፡7/፡፡ በዚህም እምነታችንን በሀብትና በምድር ፍሬ እንዳንጥል አስጠንቅቆናል፡፡ ምክንያቱም ምግባችንን የሚሰጡን እነዚህ ሳይሆኑ እግዚአብሔር ነውና /ዘዳ.8፡3፣ ማቴ.4፡4/፡፡…
ተሐራምያኑ ልመናቸውን ይቀጥሉና አምላካቸውን፡- “ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን” ይሉታል፡፡ ይህን ማለታቸውስ ምን ማለት ነው? በዚህ ዓለም ደስታ ይሆን? በፍጹም! ይኸን የለመኑ ቢሆን ኖሮ ራሳቸውን በየፍርኩታው፣ በየገደሉ፣ በየበረኻው ማቅ ለብሰው ባልተመላለሱ ነበር፡፡ ስለዚህ እየለመኑት ያለው ደስታና ሐሴት ከዚህች ዓለም ደስታ ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት የሌለው ይልቁንም የመላእክትን ሐሴት የሆነውና ሰማያዊውን ደስታ ነው፡፡
አጠያየቃቸውን እንኳን ተመልክተን ከሆነ ቀለል ባለ አገላለጽ “ስጠን” ሳይሆን “ሙላልን”፤ “እኛን” ሳይሆን “ልባችንን” ነው የሚሉት፡፡ የልብ ሐሴት ማለት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆኑት ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም የመሳሰሉ ናቸውና /ገላ.5፡22/፡፡
ስለዚህ ኀጢአት ሐዘንን ስለምታመጣ ያለዚህም ደስታ ስለማይገኝ በዚሁ ደስታ አማካኝነት ጽድቅን እየለመኑ ነው ማለት ነው፡፡
ሐዋርያው፡- “እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጐ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” ይላል /2ቆሮ.9፡8/፡፡ እነዚህ መነኰሳት በዚህች አጭር ምስጋናቸው “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” የሚለውን የወንጌሉን ቃል እንደ ተገበሩትና እነዚህን ሁሉ ለመንፈስ ፍሬ እንዴት እንደ ፈለጓቸው ተመልከቱ፡፡ ምክንያቱም፡- “በጐው ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ ልብ በሉ! “ሥራችንን እንፈጽም ዘንድ፣ በጐ ምግባርን እንሠራ ዘንድ” ብቻ ሳይሆን “ይበዛልን ዘንድ” ነው እያሉ ያሉት፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ዘንድ ትንሽዋን ፈቃድ ሲፈልግብን እነዚህ መነኰሳት ግን ከዚህም በላይ የሆነ መታዘዝን ነው ያሳያት፡፡ ይህ አባባል የመልካም ባሮች እና ራሳቸውን የሚገዙ የጠንቃቃ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡
በመቀጠል ይኸን መልካም ሥራ የሚሠሩት በራሳቸው አቅም እንዳልሆነ እና ደካማነታቸውን ለመግለጽ፡- “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ገር ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን” ይላሉ፡፡ በምስጋና የጀመሩት ልመናቸው በምስጋና ያሳርጉታል፡፡
ከዚህ በኋላ አዲስ ምስጋና የጀመሩ ቢመስሉም ያንኑ ምስጋናቸውን ተከትሎ የሚመጣ ተጨማሪ ሐሳብ ይቀጥላሉ፡፡ ይኼም ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶቹን ሲጀምር፡- “እንደ አባታችንና እንደ አምላካችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፡፡ ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን አሜን” ገላ.4፥5 ብሎ በምስጋና ጀምሮ ተመልሶ ወደ መጀመርያው ሐሳብ እንደሚመለስ የመሰለ ነው፡፡ በሌላ ቦታም ቅዱስ ጳውሎስ ፡- “በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው አሜን” ሲል ቃሉን ፈሞ ሳይሆን እንደገና እንደጀመረ /ሮሜ.1፡25/፡፡
እንግዲያስ እኛም እነዚህን መነኰሳት ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደገና ጀመሩ ብለን የምንወቅሳቸው አይደለንም፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያቱ በምስጋና ጀምረው በምስጋና ጨርሰው ዳግመኛ መልእክታቸውን እንደሚቀጥሉ ሁሉ እነዚህ መነኰሳትም ይኼን በመሰለ መንገድ ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡
ስለዚህ፡- “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እገዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና” ይላሉ፡፡
ምስጋናን ማቅረብ ያለብን ስለ ትልልቅ ጉዳዮቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ጥቃቅኑም ጭምር መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መነኰሳት የተባሕትዎን ኑሮ የሚንቁትን ሁሉ ያሳፍሩ ዘንድ ስለ ጥቃቅኑም ጭምር ያመሰግናሉ፡፡ እነዚህ መነኰሳት መናፍቃን እንደሚያወሩት ማለትም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ከመጥላት ወይም ጋብቻን ከማንቋሸሽ አንጻር ሳይሆን ቁጥብነትን፣ ራስን መግዛት ይለማመዱ ዘንድ ይኼን ያደርጋሉ፡፡
ምስጋናቸው ደግሞ እግዚአብሔር ከዚህ አስቀድሞ በሰጣቸው ሁሉ የተገደበ ሳይሆን ፡- “በመንፈስ ቅዱስ ሙላን” እያሉ ወደ ሰማያዊ መሻት እንደሚወጡና ያንን ሕይወት እንደሚናፍቁ ልብ በሉ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔር ካልረዳው በስተቀር ማንም ሰው ታላለቅ ሥራዎችን መሥራት አይችልም፤ ቢሠራ እንኳን ታላላቅ መሆን ያለባቸውን ያህል ታላላቅ አይሆኑም፡፡
ስለዚህ፡-“ በጐ ሥራችን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” እንዳሉ ሁሉ አሁንም “በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በቅዱስ መንፈስህ ሙላን” ይላሉ፡፡
እንግዲህ ስለአሁኑ ዓለም ኑሮዋቸው ጸሎት ሳይሆን ምስጋናን ብቻ እንዳቀረቡና ከመንፈስ ቅዱስ ለሚሆነው ነገር ግን ጸሎትም ምስጋናም እንዳቀረቡ ተገነዘባችሁን? ጌታም ያስተማረው ይኼንኑ ነበር፡- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” እንዲል /ማቴ.6፡33/፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ መነኰሳት ዘንድ ያለውን ከፍተኛ መልካምነት ልብ በሉ፡፡ ምክንያቱም ሲጸልዩ፡- “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ እንዲህ ማለታቸውም ነበር፡- “በብዙዎች ዘንድ የሚደርስብን ማንኛውም የሚያሳፍር ነገር አያስጨንቀንም፤ ሰዎች በእኛ ላይ የወደዱትን ሁሉ ቢናገሩ፣ ቢስቁብን፣ ቢታበይቡን ለእኛ ቁብም አይሰጠንም፡፡ የእኛ ጭንቀትና ናፍቆት በፊትህ የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ ብቻ ነው፡፡” በዚሁ ጸሎታቸውም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ደግሞም መንግሥቱን ለሚያወርሳቸው ያዘጋጀውን መልካሙን ሁሉ እና የእሳቱን ባሕር በሚገባ አስቀምጠውታል፡፡
ሲጸልዩም፡- “እንዳንቀጣ” ሳይሆን “በአንተ ፊት የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ” ነው ያሉት፡፡ ይኸውም እኛ ሁላችን ከገሃነም አስፈሪነት ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት መቆምን እንድንፈራ ሲያስተምሩን ነው፡፡
ታድያ እነዚህ መጻተኞች፣ ስደተኞች፣ የበረሀው ከዚያም በላይ ደግሞ የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች የሆኑት እነዚህ መነኰሳት ምን ያህል እንደጠቀሙን ተመለከታችሁን? እኛ በዚህ ምድር ሐሳብ ስንፏቀቅ እነርሱ ግን በተቃራኒው ከዚህ ዓለም ተቃራኒ በመቆም የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች ሆነዋል፡፡
ዝማሬአቸውን ከጨረሱ በኋላ ስለ ኃጢአታቸው በማዘንና በማያቋርጥ የእንባ ጅረት ካለቀሱ በኋላ ለቀጣዩ ቀን ራሳቸውን እንደ አዲስ ይዘጋጁ ዘንድ ትንሽ ዕረፍት ይወስዳሉ፡፡ እንደገና ተነሥተውም ሲያመሰግኑ ደግሞም መዝሙረ ዳዊታቸውን እየደገሙ ሌሊትን ቀን ያደርጉታል፡፡
የሚደንቀው ነገር ደግሞ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ የተፈጥሮ ደካማነታቸውን በትጋት በማሸነፍ ይኼን ራስን የመካድ ኑሮ የሚፈጽሙት ሴት መነኰሳየያትም ናቸው፡፡
እንግዲያስ እኛም ወንዶች ስንሆን የእነዚህን ሴት መነኰሳይያትን ትጋት እየተመለከትን በራሳችን የምናፍር እንሁን፡፡ እንደ ጥላ ከሚያልፉት፣ እንደ ሕልም ከሚረሱትና እንደ ጢስ ከሚተጉት ከዚህኛው ዓለም ጉዳዮች ጋር እንታሠር፡፡ ብዙዎቻችን በዚሁ ድንዛዜ ተይዘን ዕድሜአችን ያልቃልና፡፡
የአብዛኞቻችን የዕድሜአችን የመጀመርያው አጋማሽ በዚሁ ስንፍና የተሞሉ ናቸው፡፡ ወደ ሁለተኛው የዕድሜአችን አጋማሽ ከገባን በኋላም ትንሽ ደስታን አጣጥመን መልሰን በርኩሰት፣ በድካምና በሌሎች የማይረቡ ነገሮችን እንታነቃለን፡፡
ስለዚህ ሌባ የማይሰርቃቸውንና ዘላለማውያን የሆኑትን /የማያልፉትን/ ሀብታት እንዲሁም ማርጀት (ሽምግልና) የሌለበትን ሕይወት ትሹ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡
አንድ ሰው በከተማ ውስጥ ሆኖም እንደ እነዚህ መነኰሳት ራስን መግዛት መለማመድ ይችላል፡፡ አዎ! ሚስት አግብቶ፣ በቤትና በኑሮ ጉዳዮች የተጠመደ ሰው እንኳን መጸለይ፣ መጾምና ስለ ኃጢአቱ ማልቀስ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ከሐዋርያት የተማሩትም ምንም እንኳ በከተማ ቢኖሩ በበረሃ የሚኖሩትን ሰዎች ንጽሕናና ቅድስና ይዘው ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ብዙ ሠራተኞች የነበሯቸውም እንዲሁ አድርገዋል፡፡
ነቢያቱም እንዲሁ ሚስትና ቤት ነበራቸው እንደ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤልና ሊቀ ነቢያት ሙሴ፡፡ እነርሱ ከበጎ ምግባርና ትሩፋት የተነሣ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡
እንግዲያስ እኛም እነዚህን ሁሉ እየመሰልናቸው እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ እናመስግን፤ በጊዜውም ያለጊዜውም በመዝሙር እንቀኝለት፤ ትዕግሥትንና መልካም ምግባርን ሁሉ ገንዘብ እናድርግ፡፡ በገዳማውያኑ የተለመደውን ራስን የመግዛት የሕይወት ልምምድ ወደ ምንኖርበት የከተማ ሕይወት በማምጣት በእግዚአብሔር ፊት የተገባን ሆነን እንገኝ፡፡ ብርሃናችንም በሰው ፊት ይብራ፡፡ ሊመጣ ያለውን በጎ ስጦታ ሁሉ እንውረስ፡፡
ይህንን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ያድለን፡፡ ምስጋና ክብርና ለእርሱ በእርሱ ለአብ ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!