ቡቱሽና ኪቲ /ለሕፃናት/
ጥር 15/2004 ዓ.ም.
ውድ ሕፃናት እንደምን ሰነበታችሁ ለዛሬ አንድ ተረት አስነብባችኋለሁ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቡቱሽና ኪቲ የሚባሉ ሁለት እኅትማማች እንቁራሪቶች በአንድ ወንዝ ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ኪቲ የእናቷን ምክር የምትሠማ ጎበዝ ልጅ ስትሆን ቡቱሽ ግን የእናቷን ምክር የማትሰማ የታዘዘችውን የማትፈጽም ልጅ ነበረች፡፡ እናቷ “ተይ ቡቱሽ ወደ ወንዙ መሐል አትግቢ አደጋ ይደርስብሻል፡፡” ስትላት አትሰማም ነበር ከጓደኞቿ ጋር ወደ ውኃው መሐል እየገባች ትጫወታለች ቡቱሽ ወደ ወንዙ መሐል እየገባች ስትጫወት ኪቲ ደግሞ እቤት ሆና እናቷን በሥራ ታግዛታለች ትምህርቷንም ታጠናለች፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በእነ ቡቱሽ ሰፈር እሳት ተነሣና የሰፈሩ ሰዎች በሙሉ ባልዲ፣ ጀሪካንና ሌሎችም የውኃ መቅጃ እቃዎችን ይዘው ወደ ወንዙ ሔዱ በዚህ ሰዓት ቡቱሽ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ወደ ወንዙ መሐከል ሔዳ እየተጫወተች ነበር፡፡ ሰዎቹም ከውኃው ጋር እፍስ አድርገው ይዘዋት ሔዱና እሳት ውስጥ ጨመሯት እሷም በእሳቱ ተቃጥላ ሞተች፡፡ ኪቲ ግን እቤት ሆና እያጠናች ስለነበር በእሳት ከመቃጠል ተረፈች፡፡
መቼም ልጆች ከዚህ ተረት ጥሩ ቁም ነገር እንደ ጨበጣችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አያችሁ ልጆች የታላላቆችን ምክር መስማት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ፡፡ ኬቲ የእናቷን ምክር በመስማቷ እና ከቤት ባለመውጣቷ በእሳት ከመቃጠል ስትድን ቡቱሽ ግን የእናቷን ምክር አልሰማም ብላ ወደ ወንዙ መሐከል ገብታ ስለተጫወተች በእሳት ተቃጥላለች፡፡ ስለዚህ ልጆች እናንተም የተለያዩ ችግሮች እንዳይገጥሙአችሁ የታላላቆቻችሁን ምክር በሚገባ ስሙ፡፡