በዲታ ወረዳ የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን የቃጠሎ አደጋ ደረሰበት
ጥር 5/2004 ዓ.ም
በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት፣ በዲታ ወረዳ፣ ጋና ደሬ ቀበሌ፣ የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሌሊቱ በስድስት ሰዓት አካባቢ በእሳት ቃጠሎ አደጋ ደረሰበት፡፡
የቦታው አቀማመጥና አደጋው የደረሰበት ሰዓት ሌሊት በመሆኑ በቦታው ምንም ዓይነት ነዋያተ ቅድሳት ማትረፍ እንዳልተቻለ በቦታው የሚገኙት የደብሩ አገልጋይ ገልጸዋል፡፡ የአደጋውን መከሰት ሰምተው የመጡት የአካባቢው ምዕመናን ከሌሊት ጀምሮ ጥልቅ ሀዘናቸውን በለቅሶ ሲገልጹ እንደነበር በቦታው የተገኙት የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ዘግበዋል፡፡
የአካባቢው ምዕመናን በወቅቱ አደጋውን ሰምተው ለመጡት ለብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱሰ ሲኖዶስ አባል፣ ለሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ የደብር አለቆች፣ ለአርባ ምንጭ ማእከል የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ ከመንግሥት በኩል ለጋሞ ጎፋ ዞን ፕሬዝዳንት ለአቶ ጥላሁን ከበደ፣ ለተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለፌደራል ፖሊስ ጸጥታ አስከባሪዎች እንደተናገሩትና በተደረገው ገለፃ የአደጋው መንስኤ ታኅሣሥ 28 ቀን በወረዳው ከተማ ዛዳ በሚገኘው የአካባቢው አብያተ ክርስቲያናትም ለጥምቀተ ባሕር የሚገለገሉበትን ቦታ ላይ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የገና በዓልን ለማክበር በመውጣታቸው ግጭት እንደነበርና ይህ በሆነ ማግስት ቤተ ክርስቲያኑ መቃጠሉን ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱሰ ሲኖዶስ አባል፣ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ የደብር አለቆች፣ የአርባ ምንጭ ማእከል የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፌደራል ፖሊስ ጸጥታ አስከባሪዎች በቦታው ተገኝተው ምዕመናንን ለማረጋጋትና ለማጽናናት ችለዋል፡፡ ከዚህ በተያያዘ በወረዳው የሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ምዕመናን ወደ ወረዳው ከተማና ቤተ ክርስቲያኑ ወደ ተቃጠለበት ቀበሌ በመድረስ ህዝቡን አጽናንተው የአብሮነት ስሜታቸውንም ሲገልጹ እንደነበር ተስተውለዋል፡፡
በዕለቱ በቃጠሎ አደጋ ለደረሰበት ቤተክርስቲያን የዕርዳታ ማሰባሰብ ሥራ የተጀመረ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በማኅበረ ቅዱሳን የአርባ ምንጭ ማእከልና ምዕመናን በዕለቱ ማድረግ የሚችሉትን ቃል ገብተዋል፡፡ የአካባቢው ምዕመናንም ሥራውን በፍጥነት ለማስጀመር በዕለቱ እንጨት በማምጣት የተሠማሩ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ በፍጥነት እንዲሠራላቸው ያላቸውን ጥልቅ ጉጉት ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡