ግብጻውያን ኦርቶዶክሳዊ የሕክምና ባለሙዎች በኢትዮጵያ ነጻ አገልግሎት ሰጡ::
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠያቂነትና በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መልካም ፈቃድ ግብጻውያን ኦርቶዶክሳዊ የሕክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ነጻ አገልግሎት ሰጡ፡፡
የሕክምና ቡድኑ አባላት ከ27/2/2004 ዓ.ም – 1/3/2004 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አገልግሎት እንደሰጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሃያ ሦስት አባላት ያሉት የሕክምና ቡድን አባላት መሪ የሆኑት ዶክተር ጆርጅ ታድሮስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ጥሪ በቤተ ክርስቲያናቸው በኩል እንደደረሳቸው ሁሉም የተመረጡት ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሙሉ ፈቃደኛ ነበሩ፡፡
የሕክምና ቡድኑ አባላት መቀመጫቸው ሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናቸው ለአገልግሎት በምትጠራቸው ወቅት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡በተለያዩ የዓለማዊ ሥራ ቦታ የተሰማሩ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በሙያቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ ሃይማኖት ሳይለዩ ለሕዝቦች ሁሉ ቀና ግልጋሎት ለመስጠት መትጋት እንደሚገባቸውም የቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መጠጊያ ነች ያሉት የቡድን መሪው በኢትዮጵያ የግብጽ ኦርቶዶክሳዊ ሐኪሞች የሰጡት የሕክምና እርዳታ ወደፊት ከማኅበረ ቅዱሳንና ከመሰል የቤተ ክርስቲያን አካላትና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡የልዑካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሕዝቡን ክርስቲያናዊ ፍቅር በነጻነት ሃይማኖቱን የመከተል እድልና እንግዳ ተቀባይነቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡