የዘወረደ ወንጌል (ዮሐ.3÷10-24)
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን አንዴት ይህን አታውቅም?” አለው፡፡
እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም፡፡ በምድር ያለውን ስነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁን ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ አንጂ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፡፡ ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም አንዲፈርድ እግዚአአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም አልላከውምና፡፡ በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል፤ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አላመነምና፡፡ ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጥቶአልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደብርሃን አይመጣም፡፡ አውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ አብሮአቸው ተቀመጠ፡፡ ዮሐንስም በዮርዳኖስ ማዶ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ያጠምቅ ነበር፤ በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ እየመጡ ያጠምቃቸው ነበር፡፡ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልገባም ነበርና፡፡