ለቅኔ ትምህርት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ
ዓውደ ርእዩ ኅብረተሰቡ ስለአብነት ትምህርት ቤቶች ግንዛቤ እንዲኖረው ረድቷል
«ቅኔ የአብነት ትምህርቱ ፍልስፍና መሠርተ» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበራዊ አገልገሎት ልማት ዋና ክፍል የተዘጋጀው የግማሸ ቀን ዐውደ ጥናት በስ ድስት ኪሎ ስብሰባ አዳራሽ ተካሄደ፡፡ ዐውደ ጥናቱን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እንደገለጹት፤ ዐውደ ጥናቱ በቅኔ ትምህርት አገልግሎቱና ፍልስፍናው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
የቅኔ ትምህርት የቤተክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት፣ የሀገራችን ታሪክ እና የቀደምት አባቶችና የዛሬዎች ሊቃውንት ፍልስፍና ጥበብ እንዲሁም ማኅበራዊ ሒስ የተላለፈበት የዕውቀት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቅኔ በሀገሪቱ ሕዝቦች የአኗኗር ሥርዓትና ባሕል ውስጥ የራሱ አሻራ ያስቀመጠ ትምህርት ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ የውጭ ሙሁራን በትምህርቱ ላይ ምርምር እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በአንጻሩ በሀገሪቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ትምህርቱን ለማሳደግ የሁሉም ርብርብ የሚያስፈልገው እንደሆነና ዐውደ ጥናቱም የጠለቀ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ ምሁራንን መነሻ የሚያመላክትና የሚያነሳሳ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
«ቅኔ የግእዝ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ» በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር እና ተመራማሪ ዶ/ር ሥርግው ገላው በበኩላቸው፤ የቤተ ክርስቲያንና የሀገሪቱ ሊቃውንት የአብነት ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ የቅኔን ትምህርት ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የቅኔን ትምህርት በማሳደግ የነገይቱን ቤተክርስቲያንና ሀገርን ወደተፈለገው እድገትና ለውጥ ለማድረስ የሚችሉትን የአብነት ትምህርት ቤት ሊቃውንት በተገቢው መንገድ ማዘጋጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የቅኔ ትምህርት እንዲስፋፋ ለማድረግ የቅኔ ትምህርት ቤቶችን ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ደረጃ በማሳደግና ሥርዓተ ትምህርት ሊቀረጽላቸው እንደሚገባም ዶ/ር ሥርግው አስተያየ ታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዐውደ ጥናት ላይ «ቅኔ በቤተክርስቲያን አገልግሎት» ና «ቅኔ ለመጽሐፍት ትርጓሜ» በሚል ርዕስ ሌሎች ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች የማኅበረ ቅዱሳን ጥናት እና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ በመምህር ደሴ ቀለብና በስዋሰው ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ የቀረበ ሲሆን፤ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ከተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የቅኔን ትምህርት ለማሳደግና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ቤተክርስቲያን ሰፊ ድርሻ እንዳላትና ትኩረት ልትሰጠው እንደሚገባ የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ክቡር አምባሳደር ሙሀሙድ ድሪር እንደገለፁት፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖች ለአብነት ትምህርት ቤቶች የሰጡት ትኩረት እጅጉን እንደሚደነቅ ጠቁመው፡፡
ያብነት ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ የቅኔን ትምህርት ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት ጥረታቸው ከዳር ይደርስ ዘንድ የባህልና የቱሪዝም ሚኒስቴር ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
በሲምፖዝየሙ በተለያዩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔ የተዘረፈ ሲሆን «ቅኔ ያብነቱ ፍልስፍና» የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም ተመርቆ ለእይታ በቅቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ዋና ክፍል «በጌጠኛ ቤትህ ልማት ይሁን» በሚል መሪ ቃል ለ10 ቀናት የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ተጠናቀቀ፡፡
ከሐምሌ 18 እስከ 26 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ በዓይነቱም በይዘቱም የተለየ እንደነበረ የገለጹት የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ዋና ክፍል የቅስቀሳና ገቢ አሰባሳቢ ክፍል ሓላፊ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት፤ ዐውደ ርእይው በፎቶ ግራፍና በተለያዩ ገላጭ መረጃዎች የተደራጀ በመሆኑ ለመእመኑ ስለ አብነት ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤን እነደፈጠረ ተናግረዋል፡፡
በዐውደ ርእዩ ላይ ዋና ክፍሉ በ2002 እና 2003 ዓ.ም ገዳማትና አድባራት ላይ የሚያከናውናቸው 12 ፕሮጀክቶች ለዐውደ ርእዩ ተመልካቾች ማስተዋወቁንም ጠቁመዋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር