dscn6308

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሰማዕታቱን ቤተሰቦችንና ምእመናንን አጽናኑ

ሚያዝያ15 ቀን 2007ዓ .ም.

dscn6308ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በደብረ ፍሥሓ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ አካባቢ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሰማዕታቱን ኢያሱ ይኵኖ አምላክና ባልቻ በለጠ ቤተሰቦችንና ምእመናንን ሊያጽናኑ፤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘካናዳ፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ኖክና ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሄደዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

ልጆቻችን የምንኮራባቸው መጻሕፍቶቻችን ናቸው፡፡ ልጆቻችን ሰማዕታቶቻችን ናቸው፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የውድ ልጆቻችን የሰማዕታቱ፣ የታማኝ ልጆቻችን፣ የጀግኖች ልጆቻችን፣ በኢትዮጵያዊ ባህላቸው፣ በኢትዮጵያዊ ትውፊታቸው፣ በእምነታቸው፣ በሥርዐታቸው፣ በወጋቸው ጸንተው፣ ለማንም ሳይበገሩ እና ለማንም ሳይደለሉ፣ ለሌላ እጃቸውን ሳይሰጡ፣ ሳይቀለበሱ ጀግንነትን ያስተማሩ ልጆቻችን፣ መጻሕፍት የኆኑ ልጆቻችን ወላጆች እና እዚኅየተሰበሰባችሁ ውድ ወገኖቼ፡-

ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰባት መቶ ዓመታት ቀድሞ የነበረው ነቢዩ ኤርያስ፣ በዚያን ጊዜዋ ባቢሎን በዛሬዋ ኢራቅ፤ በዚያን ጊዜዋ ፋርስ በዛሬዋ ኢራን እየዘዋወረ ባስተማረበት ዘመን ስለ ኢትዮጵያውን አድናቆት፣ ክብር፣ ጀግንነት፣ አይበገሬነት በትንቢቱ ምዕራፍ 13 ቁጥር 23 ላይ እንዲኽ ብሏል፡-ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን?

dscn6309ኢትዮጵያዊ ባህሉን፣ ኢትዮጵያዊ እምነቱን፣ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ጀግንነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ትውፊቱን በሌላ ሊቀይር ይችላልን? አይቀየርም፡፡ ነቢዩ ቆቃው ኤያስ በተባለ መጽሐፉም ይህን በስፋት እየገለጸ ይናገራል፡፡

ውድ ወገኖቼ፤ ልጆቻችን እኮ ጀግኖች ናቸው፤ ልጆቻችን እኮ እጃቸውን አልሰጡም፤ ልጆቻችን እኮ አልተንበረከኩም፤ ልጆቻችን እኮ መጻሕፍቶቻችን ናቸው፤ ልጆቻችን እኮ አርበኞቻችን ናቸው፤ አልተማረኩም፤ የጀግና እናት አታለቅስም እንደተባለው ሁሉ፣ እናንተም የጀግኖች እናቶች ናችሁ፤ ልትኮሩ ይገባችኋል፤ ስማቸውን ለውጠው፣ ሃይማኖታቸውን ለውጠው፣ ሥርዐታቸውን ለውጠው፣ ተማርከው ቢሆን ኖሮ ነበር ማልቀስ የሚገባን፡፡

ውድ ወገኖቼ፤ የጀግኖች ወላጆች ናችኹና ልትኮሩ፣ ልትጽናኑ ይገባችኋል፡፡ እሰይ ልጄ፤ ተባረክ ልጄ፤ ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃኽ ብላችሁ ልትመርቁ፣ ልትጸልዩ፣ ልትጽናኑ ይገባል፡፡ የመጽናኛ ዕለት ነው፤ ልጆቻችን አስተምረውናል፤ ልጆቻችን አኩርተውናል፤ ልጆቻችን አስከብረውናል፤ አስወድደውናል፤ በዓለም ደረጃ አገራችንን አስተዋውቀዋል፡፡

ውድ ወገኖቼ፤ እንዲኽ ላሉት ነው እንዴ የሚለቀሰው? አገር አጥፍቶ ለሔደ፣ በሙስና ተዘፍቆ ለሔደ፣ ሰክሮ ለሔደ፣ አመንዝሮ ለሔደ፣ ቀምቶ ለሔደ በምድር ኑሮው ተበላሽቶ፣ በሰማይ እንዴት ይኾን ከቶ ተብሎ የሚለቀስለት ለዚኽ ነው፡፡ ብዙ ልጆቻችን በየመልኩ ኸሉም አርበኛ ነው፡፡ አካሉን፣ ሕይወቱን፣ ወላጁን፣ ልጁን፣ ዘመኑን፣ ንብረቱን የሰጠ ስንት አለ? ውድ ወገኖቼ፤ እንዴ፣ እነዚኽማ ልጆቻችን የምንኮራባቸው መጻሕፍቶቻችን ናቸው!! የምንማርባቸው ዩኒቨርስቲዎቻችን ናቸው ልጆቻችን!! ብርሃናችን ናቸው ልጆቻችን!! ማዕተቤን አልበጥስም፤ ወደ ሌላ አንለወጥም፤ አንበገርም አሉ፤ ይኼ ነው ወይ የሚያስለቅሰው? የሚለቀስበትን ነገር እንወቅ እንጂ!

ውድ ወገኖቼ፤ ስለዚህ ልጆቻችንን በሰማዕትነታቸው፣ በጀግንነታቸው ልናከብራቸው፣ ልንማርባቸው፣ ምሳሌአቸውን ልንወስድ፣ ልናወድሳቸው ይገባል፡፡ ስለዚኽ ይኼ የመረጋጋት፣ የሰላም የፍቅር ቦታ ነው፡፡ ልጆቻችን የአገር ፍቅር፣ የአገር ሰላም፣ የአገር አንድነት አስተምረውናል፡፡ በልጆቻችን ተምረናል፤ ጠግበናል፤ ረክተናል፤ ኮርተናል፡፡

የልጆቻችንን ነፍስ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያሳርፍልን፤ ይማርልን፤ ወላጆቻቸውን ይጠብቅልን፤ ከክፉ ነገር ይሰውረን፤ መልካሙን ነገር ያምጣልን፤ ልጆቻችንና ወገኖቻችንን በሰላም ወደ ቤታቸው ይመልስልን፡፡ ሁላችንም ተጽናንተን የሚያኮራ ሥራ እንድንሠራ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ ነፍሰ ገብሩ ኃይለ ኢየሱስ፣ ኃይለ ሚካኤል ሀገረ ሕይወትን መንግሥተ ሰማያትን ያውርስልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የሐዘን ዳርቻ ያድርግልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የቤተሰቡን ሕይወት፣ የቤተሰቡን ሐዘን በመልካም ነገር፣ በፍቅር ነገር ይለውጥልን፡፡ ቤተሰቡን ያለምልምልን፡፡ ቤተሰቡን ያጽናልን፡፡ ደግ ያልኾኑ ሰዎችን ወደ ደግነት፣ ወደ ምሕረት፣ ወደ ቸርነት ይመልስልን፡፡ ለዓለሙ ኹሉ ሰላም መረጋጋትን ያድልልን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያን በክብር በረድኤት ይጠብቅልን፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ

dscn6312ያለንበት አካባቢ ቤተ መቅደሱ ቂርቆስ ነው፡፡ እንደምታውቁት ቂርቆስ ሕፃን ነው፡፡ በምን መልክ እንደ ዐረፈ ታውቃላችሁ፡፡ ሕፃኑ ቂርቆስ፣ ዓላውያን ነገሥታት በእኛ እምነት እመን፤ እኛ የምናዝዝህን ፈጽም ባሉት ሰዓት አልተቀበላቸውም፡፡ እሳት ነደደ፤ በበርሜል ውስጥ ውኃ ፈላ፡፡ በዚህ ሰዓት እናቱ ደንግጣ ወደ ፈላው ውኃ ለመግባት ስትፈራ ሕፃኑ ቂርቆስ፣ እናቴ ጨክኚ፤ ዛሬ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ቀን ነው፡፡ አባቶቻችን በሰጡን፣ ባወረሱን፣ ባስተማሩን እምነት ጸንተን ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ነውና ከዓላዊው ንጉሥ አትፍሪ ብሎ እናቱን ወደ እሳት የጋበዘ ነው፡፡ እስከ መጨረሻው እስከ ዘላለሙ ሰማዕቱ ቂርቆስ ሲባል ይኖራል፤ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል፤ ታሪክ አይደመሰስም፡፡

አሁንም እነዚህ ወንድሞቻችን፣ ወገኖቻችን ሰማዕታት የታሪክ ባለቤቶች ስለኾኑ፣ ታሪክ አትርፈው ስለሔዱ ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት ኹሉ ለዘላለም ስማቸው፣ ሥራቸው ሲወሳ ይኖራል፡፡ ሐዘን ሁልጊዜ ሲያነሡት ልብ ይሠቀጥጣል፡፡ ይኼን እያነሡ መናገር በጣም ይከብዳል፡፡ ጭንቅላት ሊሸከመው አይችልም፡፡ እናም እዚህ ያሉትን እያጽናናችኹ፣ እዚያ የቀሩት ደግሞ በሰላም እንዲወጡ ምህላ እያደረግን ልንጸልይ ይገባል፡፡ እኛ እዚኽ ፀሐይ እየሞቅን፣ እየተነጋገርን እናዝለን፤ እዚያ እነርሱ ከወጡበት ሰውነታቸው አልቆ ነፍሳቸው የምትጨነቅ አለችና በሰላም እንዲያወጣቸው ላለፉት ብቻ ሳይኾን ለቀሩትም ጸሎት እያደረጋችኹ በዚኽ እንድትጽናኑ ነው አደራ የምንለው፡፡

ወላጆች ወለዱ እንጂ የሁላችን ልጆች ናቸው፤ ሐዘኑ የኢትዮጵያ ነው፤ እግዚአብሔር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናቱን ይስጥልን፡፡ እዚያ የቀሩትንም በሰላም ያውጣልን፡፡