የ6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሥርዓተ ሢመት ፈጸሙ

የካቲት 27 ቀን 2005ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

ሪፖርታዥ

1-bealesimet“የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አከብራለሁ አስከብራለሁ” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደተፈጸመላቸው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ለማገልገል ቃለ መሐላ የፈጸሙ ሲሆን ከሰሜን አሜሪካ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚካሄደው የእርቀ ሰላም ሂደት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

 

በሥርዓተ ሢመቱ ላይ የመንግሥት ባለስልጣናት፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ልዑካን ምእመናን በተገኙበት በፈጸሙት ቃለ መሐላ “. . . የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፤ የሁሉም አባት ሆኜ በእኩልነት፤ በግልጽነትና በታማኝነት በፍቅርና በትሕትና አገለግላለሁ፡፡ በምሥጢረ ሥላሴና በምስጢረ ሥጋዌ ትምህርትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት አምኜ አስተምራለሁ፡፡ . . . የእግዚአብሔር ቸርነት፤ የድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የቅዱሳን መላእክት፤ የቅዱሳን ነብያት፤ የቅዱሳን ሐዋርያት፤ የቅዱሳን ጻድቃን ሰማእታት ተራዳኢነትን በማመን ሁሉንም ለመባረክ፤ ለመቀደስና ለማገልገል ቃል እገባለሁ፡፡ በኒቅያ በ325 ዓ.ም. በ318ቱ ሊቃውንት፤ በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም. በ150 ሊቃውንት፤ በኤፌሶን በ431ዓ.ም. በ200 ሊቃውንት የተወሰነውን ትምህርተ ሃይማኖት፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አከብራለሁ፤ አስከብራሉ፡፡ ለዚህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቃል እገባለሁ” ብለዋል፡፡

 

በዐውደ ምሕረት ላይ በተካሄደው መርሐ ግብር የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በዓሉን በማስመልከት2-bealesimet ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም  በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተባበሪነት ከየቤተ ክርስቲያኑ የተውጣጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቆሜ አጫበር ወረብ፤ እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የመዝሙር ክፍል አባላት ለበዓሉ ያዘጋጁትን ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃማኖት መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ ባስተላለፉት መልእክት “ታሪካዊት፤ ጥንታዊት፤ ብሔራዊትና አለማቀፋዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በየጊዜው ከውስጥም ከውጪም የሚደርስባትን መከራና ፈተና ሁሉ በጸሎቷ፤ በትዕግስቷ ተቋቁማ በደሙ በዋጃትትና በመሠረታት በሚጠብቃትም በዓለም ቤዛ በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኀይል አሁን ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ ጥንታዊትና የሁሉም በኩር የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ኋላ ቀር እንዳትሆንና ቀዳሚነቷንም እንደያዘች ትጓዝ ዘንድ ብዙ መሥራትና ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ማጠናከር ይጠበቅባታል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የጀመሯቸውን የልማት ሥራዎችና  ከዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንድትቀጥል 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በበዓለ ሲመቱ ላይ ከተገኙት የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ልዑካን መካከል ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ባርቶማ ጳውሎስ 2ኛ ዘመንበረ ቶማስ የማንካራ ሜትሮ ፖሊታን ባስተላለፉት መልእክትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሢመት ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በሁለቱ አኀት ቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

 

3-bealesimetየግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል በበዓለ ሢመቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ “በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ በጣም ብዙ ችግሮችና ፈተናዎች ይታያሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚያጋጥሙን ፈተናዎችን ለመቋቋም እኛ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናት የጌታችን የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ለመፈጸም በአንድነት ሆነን መጸለይና መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የአሌክሳንድርያ ቤተ ክርስቲያን ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያለንን የጠበቀ ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ይገባናል” ብለዋል፡፡

 

በበዓለ ሢመቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት የክቡር አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መልእክት የቀረበ ሲሆን ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ክቡር አቶ አባ ዱላ ገመዳ የኢፌዲሪ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ንግግር አድርገዋል፡፡ ባስተላለፉት መልእክትም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ብቻ ሳትሆን የአገራችን ታሪክ አካል ናት” ብለዋል፡፡ በዚሁ በዓለ ሢመት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን የአርመንና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

ከአኀት ቤተ ክርስቲያናት የተዘጋጁ ስጦታዎችን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃማኖት የተሰጡ ሲሆን የፖርቱጋል አምባሳደር በ1622 እ. ኤ. አ. በፖርቱጋል ቋንቋ ተጽፎ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውን “የኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘውን ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ በስጦታ አበርክተዋል፡፡

 

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ4-bealesimet ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ባለው መንፈሳዊ ሥልጣን ምርጫው እንዲፈጸም ባሳለፈው ውሳኔ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ተጨምሮበት ምርጫው ተከናውኗል፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራው በሰው ላይ አድሮ ነው፡፡ ሓላፊነቱና ሸክሙ ከባድ ቢሆንም እንደ ፈቃድህ ይሁን በማለት የእግዚአብሔርን ጥሪ በትሕትና ተቀብዬዋለሁ፡፡ መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣልና፡፡ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለቤተ ክርስቲያኔ እታዘዛለሁ፡፡ አልችልም ማለት እችል ነበር ነገር ግን የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ አልቀበልም ማለት መሥዋዕትነትን መሸሽ ሆነ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ሥልጣን የክርስቶስ መከራ መስቀልን ተሸክሞ ለመሥዋዕትነት መሰለፍ እንጂ ለክብርና ለልዕልና እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ሁላችሁም እንደምትረዱኝም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይርዳኝ፡፡ ጸሎታችሁና ትብብራችሁ አይለየኝ፡፡ ይህንን ታላቅ ሓላፊነት  ከእግዚአብሔር እርዳታ ጋር ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጭምር እንጂ የእኔ ብቻ ሊሆን ስለማይችል በጋራ እንወጣዋለን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ” ብለዋል፡፡

 

በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚደረገውን የእርቀ ሰላም ሂደት በማስመልከት “ለረጅም ጊዜ ሲያወዛግብ የከረመው የእርቅና የሰላም ጉዳይ ለጊዜው ባይሳካም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ጥረቱ ይቀጥላል፡፡ ተስፋ አንቆርጥም” ብለዋል፡፡

 

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በሐምሌ 2002 ዓ.ም. በየካቲት 2004 ዓ.ም. እንዲሁም በኅዳር 2005 ዓ.ም. ለሦስት ጊዜያት  እርቀ ሰላም ለማካሔድ ጥረቶች መደረጋቸው ይታወሳል፡፡