ሲያሳድዷችሁና ሲነቅፏችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ፡፡ ማቴ 5፡11

 ጥቅምት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 32ኛው የሰበካ መንሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት 4 ቀን 20006 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡ በጉባኤው ላይ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ አኅጉረ ስብከት እንዲሁም የልዩ ልዩ መምሪያዎች ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡

በአንድ ሀገረ ስብከትም ማኅበረ ቅዱሳንን በሚመለከት የቀረበው ሪፖርት በቦታው የነበሩ አንዳንድ የቤተ ክርሰቲያን አባቶችንና ተሳታፊዎች ላይ ብዥታን ሲፈጥር አስተውለናል፡፡ በተለያየ አጋጣሚም ስለጉዳዩ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት ከሪፖርቱ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራትና ማኅበሩ ላይ የቀረበውን ጉዳይ አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡን ከማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ እየገቡ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ያዳክማሉ በማለት በአንድ ሀገረ ስብከት ዘገባ ላይ ቀርቧል፡፡ ይህንን በሚመለከት ማኅበሩ ምን ምላሽ አለው?

ማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የቤተክርስቲያን ልጆች በሆኑና ቤተ ክርስቲያን ባወጣችው ሕግና ሥርዓት መሠረት በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ወይም በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥkesis semu ተመዝግበው የቤተ ክርስቲያንን መመሪያ የሚያከብሩ ልጆች በማኅበር ተሰባስበው አገልግሎት የሚፈጽሙበት ማኅበር ነው፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በያሉበት ሀገረ ስብከትና አጥቢያ ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ማበርከት ግዴታቸው ነው፡፡ ግዴታቸውንም መወጣት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ምእመን ይህንን ማደረግ መንፈሳዊ ግዴታው ስለሆነ፡፡ በሚያገለግሉበት ወቅት የሰበካው ምእመናን በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ውስጥ አቅሙ እንዳላቸው ሲታመን የቤተ ክርስቲያን አባላት እስከሆኑ ድረስ በሕዝቡ ታይተው ያገለግላሉ ተብለው ይመረጣሉ፤ ያገለግላሉም፡፡ ወይም በሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት ሰንበት ትምህርት ቤትን እንዲመሩ በአገልግሎት አቅም ያላቸው አባላት ሆነው ከተገኙ የመመረጥ መብት አላቸው፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ሓላፊነት በአግባቡና በቅንነት የማገልገል የመፈጸም ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪ በትሩፋት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እፈልጋለሁ ካሉም ተጨማሪ ጊዜያቸውን፤ ገንዘባቸውን፤ ጉልበታቸውን አውጥተው አስፈላጊውን ነገር ለቤተ ክርስቲያን ማዋል ይችላሉ፡፡ የማኅበሩ አባላት እንዲህ በማድረጋቸው የቤተ ክርስቲያንን አቅም ያሳድጋሉ እንጂ ያዳክማሉ ሊባል አይችልም፡፡ እንደውም ጥሩ አደረጋችሁ ተብለው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡

እያንዳንዱ ምእመን በአጥቢያው ቤተ ክርስቲያንን የማገልገል፤ ዐሥራት በኩራት የማውጣት ግዴታ እንዳለባቸው ሁሉ የማኅበሩ አባላትም የሚጠበቅባቸውን የማድረግ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ማኅበራቸውን ለማጠናከር ከራሳቸው ገቢ የአባላት መዋጮ ይከፍላሉ፡፡ ይህንን ሲያደርጉ ለቤተ ክርስቲያን ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ ቀንሰው አይደለም፡፡ የማኅበሩ ዓላማም ይህ አይደለም፡፡ በማንኛውም መንገድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ቤተ ክርስቲያንን ያጠናክራሉ፤ ያሳድጋሉ እንጂ የማዳክም ሥራ ሊሠሩ አይችሉም፡፡

አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ቤተ ክርስቲያንን በአግባቡ ባለማገልገላቸው የማኅበሩን አገልግሎትና አባላቱን እንደ ስጋት እንዲመለከቱት ሲያደርጋቸው ይታያል፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሲጥሱ መቃወሙ እንደ ስጋት ሊቆጠር ይችላል?


የማኅበሩ አባላት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ይማራሉ፡፡ የተማሩም በመሆናቸው አባቶችን ያከብራሉ፡፡ አባትን ማክበር ምን እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተሻለ ሆኖ፤ የሚያስተምሩ ካህናትና ቀዳስያን ፤ ለቤተ ክርስቲያን ዘወትር የሚደክሙ አባቶች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ፤ ራሳቸውን እንዲችሉ የተቸገሩትን እንዲመጸውቱ እንጂ ተመጽዋች እንዳይሆኑ የማኅበሩ አባላት ጽኑ ምኞት ነው፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲጣስ አባላቱ መናገራቸው እንደ ክፋት መታየት የለበትም፡፡ እንደ ስጋትም የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ አባባል አለ፤ አንዳንድ አገልጋዮችም ሆኑ ምእመናን ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የሆነ ተግባር ሲፈጽሙ የሚገስጽ አካልን “ማኅበረ ቅዱሳን ነህ እንዴ?” ሲባል እናደምጣለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲጣስ መገሰጹ ለቤተ ክርስቲያን ከመቆርቆር የመነጨ እንጂ ለክፋት የሚደረግ ተግባር አይደለም፡፡

አንዳንድ አባላት ከግል ባሕርይ የተነሳ በአነጋገር አባቶችን ሊያስከፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አባት ልጅን ይገስጻል ፤ ይመክራል፡፡ በዚህም ተነጋገሮ መግባባት ይቻላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከናወኑ ከሥርዓት የወጡ ድርጊቶች ሲያጋጥሙ አባላት መቃወማቸውን እንደ ስጋት ማየት አይገባም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ ማኅበሩም ሆነ አባላቱ ስጋት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይልቁንም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማክበራችን ሁላችንንም ተጠቃሚ ነው የሚያደርገን፡፡

ማኅበሩ የበላይ አካላትን መመሪያ አይቀበልም በማለት በአንድ ሀገረ ስብከት ዘገባ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ቀርቦበታል፡፡ ማኅበሩ በዚህ ላይ ምን ይላል?


ቤተ ክርስቲያን የራሷ ሕግና ሥርዓት አላት፡፡ ሕጓን የምታስፈጽምባቸው ልዩ ልዩ የአስተዳደር መዋቅርም አላት ይህንን የሚያስፈጽሙም አገልጋዮችም አሏት፡፡ ለአፈጻፀሙ መመሪያ የሚሆን ቃለ ዓዋዲው አለ፡፡ ይህንንም የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በግቢ ጉባኤ ውስጥ እንደ አንድ ትምህርት ይማሩታል፤ ያውቁታልም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የማኅበረ ቅዱሳንን ደንብ መመሪያ ሲያወጣ ከቃለ ዓዋዲ፤ ደንብ፤ ከቤተ ክርሰቲያን የአስተዳደር ሥርዓት ጋር በሚጣጣም መልኩ አይቶና አገናዝቦ አጥንቶ ያጸደቀው ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ማእከላት የሚሠሩት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር በመነጋገር ነው፡፡ ከሀገረ ስብከቱ መመሪያ በመቀበል ሲፈቀድላቸው ነው የሚያገለግሉት፡፡ ገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን መርዳት፤ ፕሮጀክቶችን ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ማዘጋጀትና ሌሎችም ሥራዎች የሚከናወኑት ለሀገረ ስብከቱ አሳውቀው ነው፡፡ አባቶች መመሪያ አስተላልፈው የማይፈጽሙ አባላትም ሆኑ የማእከላት ሓላፊዎች የሉንም፡፡ የደረሰን ሪፖርትም የለም፡፡ እኛም በየጊዜው ክትትል እናደርጋለን፡፡

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ወንጪ ወረዳ የማኅበሩ አባላት ማኅበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ ወደ ጎን በመተው ቤተ ክርስቲያን የራሷ መተዳደሪያ ቃለ ዓዋዲ እያላት ቃለ ዓወዲ አሻሽለው ሌላ መተዳደሪያ ደንብ በአማርኛና በኦሮምኛ አውጥተዋል የሚል ሪፖርት ቀርቧል፡፡ አባላቱ ይህን የማድረግ ሥልጣን አላቸው?


አባላት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ሲመጡ ምን ላይ ማገልገል እንዳለባቸው አምነውበትና ተረድተው ነው የሚመጡት፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ያወጣችውን ቃለ ዓዋዲ መሠረት አድርገው ነው የሚያገለግሉት፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ደንብን አያሻሽሉም፤መመሪያም አያወጡም፡፡ እንኳን ቃለ ዓዋዲውን ይቅርና በግለሰቦች ፈቃድ የማኅበረ ቅዱሳንን ደንብ የማሻሻል ሥልጣን የላቸውም፡፡ ሕግ የሚወጣበት የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፡፡ የሚጸድቅበትም ሥርዓት አለው፡፡ ይህንን የሚረዱ አባላት በየአጥቢያው ያለውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ቃለ ዓዋዲውን የሚሽር መመሪያ ያወጣሉ ብሎ ማሰብ ትክክል ያልሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ለሰው ለመስጠትና ለማደናገር የተደረገ ነው፡፡

በወንጪ ወረዳ የማኅበሩ ሰብሳቢ ቃለ ዓዋዲውን በአማርኛና በኦሮምኛ ተርጉሞ አሻሽሏል በሚል የቀረበውን ሪፖርት እኛም ሰምተናል፡፡ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 12 ቁጥር 21 መሠረት እንዴት ሥራ ላይ እንደሚያውሉት ሲገልጽ “የዚህን ቃለ ዓዋዲ መሠረታዊ ሐሳብ ሳይለቅ ለሰበካው ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን የውስጥ መተዳደሪያ ደንብና መመሪያ እንዲሁም የሥራ ዕቅድ አዘጋጅቶ የአጥቢያው ካህናትና ምእመናን ጠቅላላ ጉባኤው አውቆት ሲስማማበት እንዲፈቀድ በወረዳው ቤተ ክህነት በኩል ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡” ይላል፡፡ የውስጥ መተዳደሪያ ደንባቸው በዘፈቀደ እንዳይተገብሩት የውስጥ ደንባቸውን ከተፈራረሙበት በኋላ በወረዳው ቤተ ክህነት አማካይነት ለሀገረ ስብከቱ ያስገባሉ፡፡ በወንጪም የሆነው ነገር እንዳጣራነው በአንድ አጥቢያ ያለ ሰበካ ጉባኤ ከላይ የተጠቀሰውን አንቀጽ መሠረት በማድረግ በአማርኛና በኦሮምኛ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅተው በወረዳው ቤተ ክህነት በኩል ለሀገረ ስብከቱ አቅርበዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱም ይህንን ማድረግ አትችሉም በማለት በደብዳቤ መልሶላቸዋል፡፡ የማኅበሩ የወንጪ ወረዳ ማእከል ሰብሳቢ የአጥቢያው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጸሐፊ በመሆን ነው የተባለው ግን ትክክል አይደለም፡፡ የወረዳ ማእከሉ ሰብሳቢ የአጥቢያው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባል አይደለም፡፡ ይህንንም አላዘጋጀም፡፡ ማኅበሩም ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡

የማኅበሩ አባላት ምእመናን ዐሥራት በኩራት ለቤተ ክርስቲያን እንዳይከፍሉ ይቀሰቅሳሉ በማለት ሥራ አስኪያጁ በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ቢሰጡን?

የማኅበሩ አባላት አንድ ምእመን ካለው ላይ ለቤተ ክርስቲያን ከዐሥር አንድ እንዲሰጥ ያበረታታሉ፤ ያስተምራሉ፡፡ ይህንንም የማኅበሩ አባላት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ተግባራዊም ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም አልፈው ዐሥራታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ካወጡ በኋላ ማኅበሩ አገልግሎት የሚሰጠው አባላት በሚከፍሉት መዋጮ ስለሆነ ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው ተጠቃሚ የምትሆነው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ክስ በሀገረ ስብከቱ የነበሩ አባቶች አቅርበው አያውቁም፡፡ እውነት ተፈጥሮ ከሆነ እስከ ዛሬ የት ነበሩ? በማንስ አስመከሩ፡፡ ክሱም ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ የሚመነጨው የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎትን ካለመረዳት የተነሣ ሊሆን ይችላል፡፡

ማኅበሩ ሥራ ፈት ወጣቶችን በማደራጀት ሁከትን ለመፍጠር ይቀሰቅሳል በማለት ለቀረበው ጉዳይ ምላሽዎ ምንድነው?


የማኅበሩ አባላት ሥራ የሌላቸው ሳይሆኑ ሥራ እየሰሩ በትርፍ ጊዜያቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ሲሆኑ፤ ሥራ የሌላቸውም ምእመናን ቢሆኑ ቤተ ክርስቲያን አስተምራ ሥራ ፈጣሪ ማደረግ ይገባል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ማንንም አደራጅቶ ሁከትን አይፈጥርም፤ ዓላማውም፤ ተልእኮውም አይደለም፡፡ ሐሰት ቢደጋገም እውነት አይሆን፡፡ ሀሰት ምን ጊዜም ሐሰት ነው፡፡ “ሲያሳድዷችሁና ሲነቅፏችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ፡፡” ማቴ 5፡11/ እንዲል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለብፁዓን አባቶችና መነኮሳት ስጋት ነው የሚለው በቀረበው ሪፖርት ከተካተቱት አሳቦች አንዱ ነው፡፡ ማኅበሩ በዚህ ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

አባቶችም ሆኑ ምእመናን የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት የሚያውቁት ነው፡፡ ማኅበራችን የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ፤ ቅዱሳት መካናት የበለጠ እንዲያድጉ፤ ገዳማት አቅማቸውን አሳድገው ሌሎችን መርዳት እንዲችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ሠርቶ ማስረከቡን፤ ድጋፍ ማድረጉን ሁሉም የሚረዳው ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አባቶች የሚያግዝና ክብራቸውን ከፍ ለማድረግ የሚጥር ማኅበር እንጂ በምንም መልኩ ለአባቶች ስጋት የሚሆን አይደለም፡፡

ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያንን ተጠግተው የሚዘርፉ፤ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትጠፋ በውስጥ ሆነው የሚሠሩትን፤ ሥራቸውን ስለሚያጋልጥባቸው ማኅበሩ ለእነዚህ ሰዎች ስጋት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም በቀናው መንገድ የሚጓዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተረካቢ ስላገኙ ደስ ይላቸዋል፡፡

በጉባኤው ላይ ማኅበሩን በተመለከተ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ ማኅበሩ የሒሳብ ምርመራውን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ባለሙያዎች ከማስደረግ ይልቅ በውጭ ኦዲተሮች ያስደርጋል የሚል ነው፡፡ የማኅበሩ ምላሽ ምንድነው?

ማኅበረ ቅዱሳን በፈቃደኝነት የተመሠረተ ማኅበር ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ የተሰጠውን ደንብና አሠራር ተከትሎ ስለመሥራቱ የሚያረጋግጥ የውስጥ ቁጥጥር ወይም ኦዲትና ኢንስፔክሽን አለው፡፡ ይህ ክፍል በተገቢው መንገድ መሠራቱን ይከታተላል፡፡ በዓመቱ መጨረሻም በደንቡ መሠረት ለጠቅላላው ጉባኤ ያቀርባል፡፡ ግድፈትም ካለ እንዲታረም ያደርጋል፡፡ ሪፖርቱ ተጠናቅሮ በየዓመቱ ለሚመለከተው የበላይ አካል ማለትም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ያስገባል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ማኅበሩን በበላይነት የሚመራ አካል እንደመሆኑ መጠን የቀረበለትን ኦዲት አላሳመነኝምና ባለሙያ ልኬ የአሠራርም ሆነ የሒሳብ ቁጥጥር ላድርግ ብሎ አያውቅም፡፡ እኛም ይህ አሳብ መጥቶ እምቢ አላልንም፡፡ በ2002 ዓ.ም. የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ የነበሩት ማኅበሩ ኦዲት ተደርጎ አያውቅም፣ የማኅበሩን የዐሥር ዓመት የሒሳብ እንቅስቃሴ ኦዲት ማድረግ እንፈልጋለን በማለት ጠየቁን፡፡ ከዚያ በፊት መስከረም 2002 ዓ.ም. በሚመለከተው የመንግሥት አካል ተጠይቀን ስለነበር ለጠቅላላ ጉባኤው አስወስነን በጀት አጽድቀን በመንግሥት አካል ተቀባይነት ያለው ገለልተኛ የውጭ ኦዲተሮችን አወዳድረን አስመርምረናል፡፡ ለሚመለከታቸው የመንግሥትም ሆነ የቤተ ክርስቲያን አካላት የኦዲት ሪፖርቱን አስገብተናል፡፡ ተጨማሪ ኦዲት ማድረግ ከፈለጋችሁ ሰነዶች አሉን፤ ማኅበሩ ለተጨማሪ ኦዲት የያዘው በጀት ስለሌለው ወጪውን ችላችሁ ማስመርመር ትችላላችሁ ፈቃደኞች ነን በማለት አቀረብን፡፡ ነገር ግን ማደራጃ መምሪያው ማስመርመር አልቻለም፡፡ እንደ አሠራር አንድ ሕጋዊ ኦዲተር የመረመረውን እንደገና መመርመርም ትክክለኛ አሠራር ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ከዚያ በኋላ ባሉት ሦስት ዓመታት ጠይቆን አያውቅም፡፡ አሁንም በውጭ ኦዲተር በየዓመቱ ያስመረመርነውን ሪፖርት በማቅረብ ላይ ነን፡፡ የ2004 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርታችንም እየተጠናቀቀ ስለሆነ እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበሩን አሠራርም ሆነ የሒሳብ ሪፖርት መመርመር እፈልጋለሁ ካለ በእኛ በኩል ፈቃደኞች ነን፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቁጥጥር አገልግሎት ክፍል ማኅበሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረሰኝን ለምን አይጠቀምም በሚል ጥያቄ አንስቷል፡፡ ማኅበሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረሰኝ መጠቀም ያልቻለበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው?

ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ የአስተዳደር መዋቅር አላት፡፡ በዚህ አስተዳደር መዋቅር መሠረት የሚሠሩ አገልጋዮቸም አሏት፡፡ ሥራዋን ለማከናወን ደግሞ ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡ ገንዘቡንም ከስዕለት፤ ከዐሥራት በኩራት፤ ከልማት ሥራዎች ባላት የአሠራር መዋቅር መሠረት ታገኛለች፡፡ ይህንንም መልሳ ለአገልግሎት ታውለዋለች፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም በፈቃደኝነት በተሰባሰቡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የተመሠረተ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ከምትጠብቅበት ማንኛውም አስተዋጽኦ በተጨማሪ ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል ብሎ አምኖ በዕውቀትም፤ በገንዘብም ሆነ በጉልበት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል አለብኝ ብሎ አምኖ ይንቀሳቀሳል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ማኅበሩን ሲያቋቁም ገንዘብ እንዴት እንደሚሰበስብ፤ ከአባላቱ እንዴት አስተዋጽኦ እንደሚሰበስብ፤ እንዴት ወጪ እንደሚያደርግ በደንቡ ላይ በትክክል አስቀምጦታል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑን ደረሰኝ ሳይሆን የራሱን የገቢና ወጪ ደረሰኝ አሳትሞ እንዲጠቀም በትክክል ተገልጧል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቃለ ዓዋዲ ያጸደቀው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳንን ደንብ ያጸደቀው ራሱ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ይህንንም ሲያደርግ በሚገባ በባለሙያ አስጠንቶ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለመርዳት ሰዎች በፈቃዳቸው በማኅበር ተደራጅተው ሲመጡ፤ ለአገልግሎት ያወጡት ገንዘብ ወደ አንድ ቋት ማለትም ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ገብቶ እንደገና በጀት ይበጀትልኝ ብለው የሚጠይቁ ከሆነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሆን አይችልም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በጠቅላይ ቤተክህነት በጀት አይበጀትለትም፡፡ ምንም ዓይነት ፈሰስ አይደረግለትም፡፡ የሚሠራውንም ሥራ በዘፈቀደ የሚሠራ ሳይሆን አባላት በሚፈጽሙት የትሩፋት አገልግሎት ከአባላት በሚያገኘው ገንዘብ ነው፡፡ የሚሠራውንም ሥራ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ሥራ እንደሆነ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ሆኑ በገዳማት የሚገኙ አባቶች የሚያውቁት ጉዳይ ነው፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡