የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት አከበረ
ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩበልዩ በዓል ግንቦት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቦሌ በሚገኘው በድርጅቱ ሕንፃ አከበረ፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶችና የድርጅቱ አባላት ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምእዳን “የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል የቤተ ክርስቲያናችን በተለይም በኢየሩሳሌም ውስጥ ለሚገኙት ገዳማት ታላቅና ታሪካዊ የሆነ በዓል ነው፡፡ 50 ዓመታትን ተስፋ ሳይቆርጡ እዚህ ላደረሱት የድርጅቱ ሓላፊዎችና ምእመናን ሁሉ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት አገልግሎት ወደፊትም ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ከሥሩ ተተኪ ምእመናንን ማፍራት አለበት” ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ድርጅቱን በመምራትና በአባልነት ላገለገሉ ምእመናን ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ድርጅቱ ያዘጋጀላቸውን ስጦታ ተረክበዋል፡፡ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ዴር ሡልጣን ገዳም ታሪካዊ ይዞታና የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅትን የሚዘክር መጽሐፍም ተመርቋል፡፡ የታእካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያሬዳዊ ዝማሬና ቅኔ አቅርበዋል፡፡
የድርጅቱ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አለማየሁ ተስፋዬ የድርጅቱን አመሠራረት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በ1955 ዓ.ም. ሠላሳ አባላት ያሉት የምእመናን ቡድን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ገዳማትን ለመጎብኘት ተጉዘው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ አባላቱ በአውሮፕላኑ ሠራተኞች አማካይነት ወደ ዴር ሱልጣን ገዳም ተወስደው በዴር ሱልጣን ገዳም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ላይ የኮፕት ኦርቶዶክሶች ያደርሱባቸው የነበረውን ከፍተኛ በደል ተመልክተዋል፡፡ መነኮሳቱም ተጎሳቁለው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀው እንዳገኟቸው አቶ አለማየሁ ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡
መነኮሳቱም “እኛ የራበን ሰው ነው፤ ረሃባችን ወገን የሚሆነን ማጣታችን ነው፡፡ እባካችሁ ወደ ሀገራችን ስትሔዱ ኢትዮጵያውያን እንዲጎበኙን አድርጉ” በማለት ነበር በወቅቱ መልእክታቸውን ያስተላለፉት፡፡
ከተጓዦቹ መካከል ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እንደነበሩበት የሚገልጹት አቶ አለማየሁ የጉዳዩ አሳሳቢነት እረፍት ስለነሳቸው እዚያው እያሉ ጥናቶችን በማድረግ አንድ ማኅበር መመሥረት እንዳለበት በመነጋገር ስምምነት ላይ ይደርሳሉ፡፡ በዚህም መሠረት አዲስ አበባ ተመልሰው ለጉዳዩ ትኩረት በመሥጠት ተጨማሪ ሰዎችን በማሰባሰብ ውይይት በማድረግ “የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት” የካቲት 16 ቀን 1956 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ የመጀመሪያውን ጉዞ 85 ምእመናንን በመያዝ በአንድ ሰው 302 ብር በማስከፈል ወደ ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ጉዞ ተደረገ፡፡ ለ50 ዓመታት በተደረገ ያልተቋረጠ ጉዞም ከ15,000 በላይ ምእመናን በድርጅቱ አማካይነት ተጉዘው ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎቹን ለማየት እንደቻሉ አቶ አለማየሁ በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡
የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በሀገር ውስጥ በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማትን ችግር በመከታተልና በመፍታት፤ በተለይም የዴር ሱልጣን ገዳም ወደ ኢትዮጵያ ባለቤትነት ለማስመለስ እንዲሁም ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር መፍትሔ በመፈለግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የዴር ሱልጣን ገዳም ከብዙ ውጣ ውረድና ትግል በኋላ ገዳሙ የኢትዮጵያ ይዞታ እንደሆነ ተረጋግጦ በ1953 ዓ.ም. ቁልፉ ኢትዮጵያውያን እንዲረከቡት ተደርጎ እንደነበር የሚያስረዱት አቶ አለማየሁ ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ብቻ እንደተጠቀሙበት ኢየሩሳሌም የሚገኙት የኮፕት ኦርቶዶክስ አባቶች በወቅቱ የግብጽ መሪ ለነበሩት አቤቱታ አቀረቡ፡፡ ተጨማሪ መረጃዎች አሉን ፍርዱ እንደገና ይታይልን በሚል የተፈረደው ፍርድ እንዲሻር ተደርጓል፡፡ የዴር ሱልጣን ገዳም ጉዳይ ዛሬም ድረስ እንዳልተፈታ የሚገልጹት አቶ አለማየሁ ድርጅቱ በዓመት አንድ ጊዜ በሚያደርገው ጉዞ በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ይገልጻሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን፤ የደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት፤ የአልዓዛር ተክለ ሃይማኖት፤ የኢያሪኮ ቅዱስ ገብርኤል፤ የቤተልሔም ቅዱስ በዓለ ወልድ፤ የኢያሪኮ ቅድስት ሥላሴ /በ6ቱ ቀን ጦርነት የተከማቹ ፈንጂዎች ስለሚገኙበት አገልግሎት አይሰጥም/ የመሳሰሉ ገዳማት ያሏት ሲሆን በነገሥታቱና በመኳንንቱ የተሠሩ ሕንፃዎችም ይገኛሉ፡፡