ኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት 49ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አከበረ፡፡
የካቲት 9/2004 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም የካቲት 4 ቀን 2004ዓ.ም የተመሠረተበት 49ኛ ዓመት በዓል ለድርጅቱን መሥራች ክብር አቶ መኮንን ዘውዴ የመታሰቢያ ሐውልት ቦሌ ሩዋንዳ በሚገኘው መሰብሰቢያ አዳራሽ በር ላይ በማቆም ጭምር ተከብሯል፡፡
በ1955 ዓ.ም. ሚያዝያ 3 ቀን ከሠላሳ በማይበልጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እንደተመሠረተ የሚነገረው መታሰቢያ ድርጅቱ በክብር አቶ መኮንን ዘውዴ ጠንሳሽነትና አሰባሳቢነት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ ቅዱሳን መካናትን ለመሳለም ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሔደው የምእመናን ቡድን በዚያ ያለውን ችግርና በገዳማቱ የሚኖሩ አባቶችና እናቶችን በደልና ስቃይ ተመልክቶ የነበረ ሲሆን በተለይ የዴር ሱልጣን ገዳማችን ወደ ጥንቱ ይዞታ ለመመለስ ካልተቻለበት ምክንያቶች አንዱ ከኢትዮጵያ ገዳማውያንን ለመጎብኘት የሚመጣ ሰው የለም የሚል ምክንያት እንደሚሰጥ መረዳታቸው ለድርጅቱ መመሥረት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ክብረ በዓሉን በንግግር የከፈቱት የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ኮሎኔል ተፈራ ይገዙ “የድርጅታችን የተመሠረተበትን 49ኛ ዓመት በምናከብርበትና በተልይም የታሪኩ ባለቤት ለሆኑት ክቡር አቶ መኮንን ዘውዴ የተሠራውን የመታሰቢያ ሐውልት በሚመረቅበት በዚህ ዕለት የተሰማንን ከፍተኛ መንፈሳዊ ደስታ ስንገልጽ ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡ “ሰው ለታሪክ የተፈጠረ እንጂ ታሪክ ለሰው አልተፈጠረም ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሩ በ1955 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ገዳማት የሚደርሰው በደል አሳዛኝ ታሪክ መነሻነት በብሔራዊና በመንፈሳዊ ስሜት በመቆርቆር ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ በርካታ አባላትን በማሰበሳብና የገዳማችንን ታሪክ በማስረዳት ለዚህ የቀደሰ ዓላማ ድጋፍ ለመስጠት ቃል የገቡትን ሰዎች ይዘው የኢየሩሳሌምን መታሰቢያ ድረጅትን የመሠረት ድንጋይ ሚያዝያ 16 ቀን 1956 ዓ.ም ያስቀመጡ የመጀመሪያው ታላቅ ሰው ከመሆናቸውም በላይ የድርጅቱን ዓላማ በተግባር በማዋል ከምንም አንስተው አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስና በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅና እንዲያገኝ ያደረጉ ታላቅ አባት ናቸው” ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ መኮንን ዘውዴ በተለይ የዴርስልጣን ገዳማችንን በተመለከተ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተቃዋሚ ወገኖች አጋጣሚ እየጠበቁ ሁከትና ውዝግብ በሚፈጥሩበት ወቅት ፈጥኖ በመድረስና በየቀጠሮም ቀን ከገዳም አባቶች ጋር በእስራኤልአገር ፍርድ ቤት በመገኘትና ከአባቶች ጎን በመቆም ከፍተኛ የሞራልና የገንዘብ እርዳታ በየጊዜው ለገዳሙ እንዲሰጥ በማድረግ የሀገርና የቤተክርስቲያን ባለውለታ መሆናቸው ተወስቷል፡፡
በመክፈቻው ንግግራቸው ምክትል ሊቀመንበሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ድርጅቱ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት የገለፁ ሲሆን “በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን ለማስተማርና በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደራጀት በቤተ ክርስቲያን የተነደፈውን እቅድ በመደገፍ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ችግር ለማስወገድ መንግሥት በልማት እንዲሳተፉ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የ700,000 ብር ድጋፍ በመንግሥትና በህዝብ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውን የሕዳሴ ግድብ ሥራ የግማሽ ሚሊዮን ብር ቦንድ ያለ ወለድ ግዥ በማድረግ ድርጅቱ በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይወሰን በአገር ውስጥም ለታሪክና መንፈሳዊ ሥራዎች ድጋፍ በመስጠት ላይ ነው” ብለው በተለይ በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን አሰባስቦ በረጲ፣ በአለም ከተማ፣ በደብረ ብርሃን የሕፃናትን በማስተማርና በመንከባከብና በአሁኑ ወቅት ዘላቂነት ያለው ሥራ ለመሥራት የ800,000 ብር ፕሮጀክት በመቅረጽ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ኘሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሠላም የክብር ኘሬዝዳንት “ክቡር አቶ መኮንን ዘውዴን የማውቃቸው የትምህርት ሚኒስቴር በነበሩበት ወቅት ነው፤ ያስተማሩኝ፣ በአዳሪ ትምህርት ቤትም እንድንማር ያደረጉኝ ታላቅ ሰው ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው ለትውልድ ታሪክንና ክብርን ላቆዩ ስሞች ክብር ይገባቸዋል ለእኝህ አባት መታሰቢያ ሐውልት እንዲያቆምላቸው ድርጅቱ መወሰኑና ታሪክን ለትውልድ እንዲቆይ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ መልካምነታቸውን ለትውልድ ልናስተላልፍ ይገባናል) ድርጅቱም አገልግሎቱን አጠናክሮ በመላው ዓለም ጽ/ቤት ከፍቶ ሊሠራ ይገባል” ብለዋል፡፡
የክቡር አቶ መኮንን ዘውዴ የመታሰቢያ ሐውልት ምረቃ ላይ ቅዱስ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች፣ የክቡር አቶ መኮንን ባለቤት ከነ ቤተሰቦቻቸው፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የድርጅቱ አባላት ተገኝተዋል፡፡ በበዓሉ ላይም የቅዱስ ኡራኤል ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌምን በማስመልከት ትምህርት ተሰጥቷል፡፡