33ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው እንደቀጠለ ነው፡፡
ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 5 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም የተጀመረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቀጥሏል፡፡ በጥቅምት 5 ቀን የከሰዓት ውሎና ጥቅምት 6 ቀን ጠዋት 24 አህጉረ ስብከቶች ሪፓርቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ከቀረቡት ሪፓርቶች በዋናነት ትኩረት የሳቡት
-
ለልማት ሥራ ትኩረት መሰጠቱ
-
አዳዲስ አማንያንን ማጥመቃቸው (ከእናት ቤተ ክርስቲያን የወጡትን የከፋ ቦንጋ ሀገረ ስብከት ብቻ ሪፓርት ቢያደርግም)
-
የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን መጠናከር
-
ሕገ ወጥ ሰባኪያንን እና አጥማቅያንን መቆጣጠር
-
ክህነት የማይገባቸው አላግባብ ክህነት መቀበል ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተግዳሮት መሆን
-
የቅርስና ንብረት ዘረፋ
-
በየሀገረ ስብከቶቹ ሪፓርት ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን እየሰጠ ያለው መንፈሳዊ አገልግሎት ከተነሱት ዋና ዋና የሥራ ፍሬዎች ናቸው፡፡
ከቀረቡት ሪፓርቶች መካከል ማሳሰቢያ የተሰጠባቸው
ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት፡-
“…የመስቀል በዓል አከባበር በዮኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንደተመዘገበ ሁሉ የመስቀሉ ማኅደር የሆነችው ግሸን ደብረ ከርቤም በዮኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ ጥረት እንዲደረግ፣…”
ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት፡-
“…የክርስቲያን ተደላ ደስታ በመንግሥተ ሰማይ ነው፤ ለሥጋ ተድላ ሲባል ያለ አግባብ ሥልጣነ ክህነት መቀበልና የቤተ ክርስቲያንን ሀብት መመዝበር አምላካዊ ፍርድን ይጠብቃል…”