ከ 3000 በላይ ምዕመናን ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ መንፈሳዊ ጉዞ ተዘጋጀ
በተ/ሥላሴ ፀጋ ኪሮስ
ሰኔ 15 ቀን 2003 ዓ.ም
ከ6 ወራት በፊት ተዘጋጅቶ እንደነበረው በርካታ ምእመናን የሚሳተፉበት መንፈሳዊ ጉዞ ተዘጋጀ፡፡ ሐዊረ ሕይወት ቁጥር 2 የሚል ስያሜ ያለው ይህ ጉዞ ሰኔ 19 ቀን 2003 ዓ.ም ይከናወናል፡፡
ከአዲስ አበባ 108 ኪ.ሜ ርቆ ፍቼ ከተማ ወደ ሚገኘው መካነ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ገዳም የሚደረገው ይህ ጉዞ መንፈሳዊ ሕይወታችን የምናጠነክርበት ይህም ከሆነ ዘንድ በቤተ ክርስቲያን የእኛ ድርሻ ምንድን ነው? ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅና ኃላፊነታችንን እንድንወጣ የሚያስችል እንደሆነ የጉዞው አስተባባሪ ቀሲስ አንተነህ ጌጡ ተናግረዋል፡፡
ሐዊረ ሕይወት ምእመናን ከመኖሪያና ከሥራ ቦታቸው ራቅ ብለው በተሰበሰበ ልቡና የቅዱሳን ሰማዕታትና የጻድቃን በረከት በሚገኝበት ቦታ ተረጋግቶ ራስን እንዲያዩ የሚያስችል፣ የአበውን ተጋድሎ በመመልከትና በማስታወስ ከፍ ወደ አለ ሥነ ልቡና የሚያደርስና የቤተ ክርስቲያንን ጣዕም የሚያሳይ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሆን ታስቦ እየተዘጋጀ እንደሆነ በአስተባባሪዎቹ ተያይዞ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ አንድና ብቸኛ ወደ ሆነው የአቡነ ጴጥሮስ ገዳም በሚደረገው ጉዞ በሐዊረ ሕይወት ቁጥር አንድ ጉዞ ወቅት ተነስተው ላልተመለሱና አሁንም ለሚነሱ ጥያቄዎች ሰፋ ባለ ሁኔታ በአበው ሊቃውንት መልስ የሚሰጥበት የምክረ አበውን ዝግጅት በድጋሚ አካቷል፡፡ ባለፈው ከነበሩ መምህራንና ሊቃውንት በተጨማሪም ሌሎች በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተለይም ይህ ጉዞ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ተረድተን መፍትሔ ፍለጋ ለመሄድ አቅጣጫ የሚሰጥ እንደሆነ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡
“ገዳሙ አንድና ብቸኛ መሆኑና ከአካባቢው ምእመናን በስተቀር በብዙው ኅብረተሰብ ዘንድ አይታወቅም በአሁኑ ጉዞ ወደ 3000 ምእመናን ይዘን እንጓዛለን ብለን እናስባለን” ያሉት ቀሲስ አንተነህ የሄዱት ምእመናን ለሌሎች ስለሚያስተላልፉ ገዳሙን በቀላሉ ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡ በዚህም ምዕመናን የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለገዳሙ እንዲያበረክቱ ያደርጋል ሲሉ ሌላኛውን አላማ ተናግረዋል፡፡
ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ጦር ሀገራችን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት አርበኞችን በማስተባበር በጀግንነት ያዋጉ ሲሆን በጦርነቱ መሃል ተይዘው ስለሃይማኖታቸው በመመስከር የሀገራቸውን መሬትም ለፋሽስት እንዳትገዛ በመገዘት ሐምሌ 22 ቀን 1928 በሰማዕትነት ያረፉ አባት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ2001 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ ጽላት ተቀርጾላቸው እንዲሁም በስማቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በትውልድ ሀገራቸው ሰርታ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ እያለች ታከብራቸዋልች፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት መጠንከር ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ የተለያዩ መንፈስዊ ጉዞዎችን እንደሚያዘጋጁ የገለፁት ቀሲስ አንተነህ በቅርብ ጊዜ የአዲስ አበባ ማዕከል ባዘጋጀው መንፈሳዊ ጉዞ ከ3000 በላይ ምእመናንን የማኅበረሩን አባላት ሌሎች ማኅበራችንና ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ይዞ ወደ ደብር ቅዱስ ደብር ጽጌ ማርያም ገዳም ያደረገውን የሐዊረ ሕይወት ቁጥር አንድ ጉዞን ተጠቃሽ አድርገዋል፡፡