3ኛው ዓመታዊ የጥናት ጉባኤ ቅዳሜ ይጀመራል።
ዲ/ን ተስፋየ አእምሮ
የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው 3ኛው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ከነሐሴ 28 እስከ 29 ቀን 2003 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ይከናወናል።
የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር ዲ/ን መንግስቱ ጎበዜ እንደገለጹት ዓመታዊ ዓውደ ጥናቱ “ጥናትና ምርምር ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መጠናከር” በሚል መሪ ቃል ይከናወናል።
የዓውደ ጥናቱ ዋና ዓላማም መሠረታዊ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመጠቆም የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ ነው ብለዋል።
በሁለቱም ቀናት አምስት ጥናቶች የሚቀርብ ሲሆን፥ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት አስፈላጊነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰው ኃይልና የገንዘብ አስተዳደር ሥርዐት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የውጭ ሀገር ሰዎች ተደራሽነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ማርያም በድርሳነ ጽዮን፣ እንዲሁም ይምርሃነ ክርስቶስ ዘመን ተሻጋሪው ሥልጣኔ የሚሉት ርዕሶች ተመርጠው እንደቀረቡ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ጥናቶቹ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚያስተምሩ ምሁራንና ሌሎች ተመራማሪዎች የተዘጋጁ ሲሆን የውይይት መሪዎችም ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ያላቸው ታዋቂ ምሁራን መሆናቸው ተገልጿል። በዓውደ ጥናቱ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ሁሉ እንዲገኙ ዳይሬክተሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።