‹‹አንተ በጎና ታማኝ አገልጋይ›› ማቴ:25

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ 

ህዳር 15 ቀን 2007 ዓ᎐ም

ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በክቡር ዳዊት አድሮ፤ “እከሥት በምሳሌ አፉየ፤ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት፤ አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሌት እናገራለሁ” ብሏል፡፡ /መዝ. 77፡2/
በዚሁ መሠረት ጌታችን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን በልዩ ልዩ ምሳሌ አስተምሯል፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ሁለት ምሳሌያትና አንድ ትንቢት ቀርበዋል፡፡

 

 ከምሳሌያቱ የመጀመሪያው በዐሥሩ ደናግል አንጻር የቀረበው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወጥተው ወርደው ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን ስለሰጠ ነጋዴ የሚናገረው ነው፡፡ ትንቢቱም ስለ ኅልቀተ ዓለም የተነገረ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ዕትማችን ነግደው እንዲያተርፉበት ከጌታቸው የተሰጣቸውን መክሊት ስለተቀበሉት አገልጋዮች እንመለከታለን፡፡ ፈጣሪያችን ለብዎውን ማስተዋሉን ያድለን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን ምሳሌያዊ ትምህርቶችን በሰፊው ተጽፎ እናገኛለን፡፡

የእነዚህ ትምህርታዊ ምሳሌዎች መሠረታዊ ሀሳብና ዓላማ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምናገኝበትን የታማኝነትን ሥራን እንዴት መሥራት እንደሚገባንና እንደምንችል ማስተማር ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ያስተማራቸው ብዙ ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ብዙ ምሳሌዊ ትምህርቶች መካከል በማቴዎስ ወንጌልም 25 ላይ እንዲያተርፉበት መክሊት ስለተሰጣቸውና ወጥተው ወርደው ሌላ አትረፈው በጌታቸው ስለተመሰገኑት ቸርና መልካም አገልጋዮች፣ እንዲሁም መክሊቱን በመቅበሩ ምክንያት በጌታው ስለተወቀሰውና ፍርድን ስለተቀበለው ሰው ታሪክ፣ የታሪኩም ምሥጢር ምን እንደሚመስል ነው፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው በሚከተለው መልኩ ነበር ‹‹ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ ሀገር ወዲውኑ ሄደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄደ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡
ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡

 

አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡- ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡፡ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ገታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት እነሆ መክሊትህ አለህ አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን:: ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር:: እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት:: 

 

ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል:: ከሌላው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት:: በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡›› የሚል ነው፡፡ መክሊት ጥንት የክብደት መለኪያ ነበር:: አንድ መክሊት 30 ኪሎ ግራም ያህል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸውም መክሊት የሚለው ቃል ገንዘብን ያመለክታል፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ እርሱን የምናገለግል ሁላችን አንደየዓቅማችን ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ የአገልግሎት ሥራንና በአገልግሎታችን ውጤታማ በመሆናችንም ከእርሱ የምናገኘውን ዘላለማዊ ክብርና ዋጋን እንዲሁም መሥራት የሚገባንን ባለማድረጋችንም ምክንያት የሚገጥመንን መለኮታዊ ቅጣትን አመልክቶናል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ባለ አምስት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣነው፡፡

 

በተመሳሳይም ባለሁለት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣ ሲሆን ባለአንድ የተባለው ደግሞ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ባለአምስትና ባለሁለት መክሊት የሆኑት ወጥተው ወርደው ደክመው’ መከራ መስቀልን ሳይሰቀቁና ሳይፈሩ’ ነፍሳቸውን ለታመነው አምላክ አደራ በመስጠት የተማሩትን ፍጹም ትምህርት ለሌላው አስተምረው ሌላውን አንደራሳቸው የተማረ አድርገው ሲያወጡ ባለአንድ የተባለው ግን አላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ ከመያዝ በቀር የተማረውን ትምህርት ለሌላው ሊያስተምርና የተሰጠውን አደራንም ሊወጣ አልወደደም፡፡

በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጠው ሌላ አምስትና ሁለት ያተረፉት በተሰጣቸው መክሊት ሌላ ማትረፋቸውን ለጌታቸው በገለጡ ጊዜ የመክሊቱ ባለቤት እጅግ አድርጎ እንዳመሰገናቸው ከላይ አንብበናል፡፡

ይህ የመክሊቱ ባለቤት የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለተወጡት ሁሉ እርሱ ፍጹም ዋጋን የሚሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም ሁኔታ ‹‹ መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› በሚል ተገልጧል፡፡ ይህ ቃል በሃይማኖት ለእግዚአብሔር የታመኑ ሁሉ ወደ ፍጹም ደስታ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለሚያደርጉት ጉዞ እጅግ ተስፋ የሆነ ቃል ነው፡፡

 

በዚህ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም እርሱን የምናገለግልበትንና ለእርሱ በመታመን ዘላለማዊ ክብርን የምናገኝበትን ዕውቀትን ማስተዋልን’ ሀብትን’ ዓቅም ወይም ጉልበትን ሌሎችንም ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለእኛ ለሰው ልጆች እንደየዓቅማችን መጠን ሰጥቶናል፡፡

እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሥጋችንን ምኞት እንድንወጣባቸው የተሰጡ ሳይሆኑ ነፍሳችን የምትከብርበትን መልካም ሥራን የምንሠራባቸው ናቸው፡፡
በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በተሰጠን ነገር ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ ልንሆን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እኛ የተጠራ ነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጅ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢኣት ባሮች ልንሆን አይደለም፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር አንደበት አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ መባልን የመሰለ አስደሳችና አስደናቂ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው ሃይማኖትን በሥራ በመግለጥ እንጅ ሃይማኖትን በልቦና በመያዝ ብቻ አይደለም፡፡ ከእነዚህም እንደ አቅማቸው መክሊት ተሰጥቷቸው ሌላ መክሊት ካተረፉት በጎና ታማኝ አገልጋዮች ከተባሉት የምንማረው እውነታ ይህ ነው፡፡ ስለዚህም በብዙ ለመሾም በጥቂቱ መታመን ግድ ነው፡፡
አንድ መክሊት የተሰጠውን ሰው ስንመለከተው ጌታውን ጨካኝ አድርጎ ከመቁጠር ውጪ በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ሊያተርፍ አልወደደም፡፡ መክሊቱንም ባስረከበ ጊዜ በጌታው ላይ የተናገራቸው ቃላት የእርሱን አለመታዘዝና አመጸኝነት ይገልጡ ነበር፡፡

 

በመሆኑም ይህ ሰው በጥቂቱ መታመን ያቀተውና በአስተሳሰቡ ደካማነት እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ መሠረት ይህ ባለአንድ የተባለው ሰው ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ በማለት ሃይማኖቱን በልቡ ሸሽጎና ቀብሮ ከመያዙ ባሻገር በጌታ ፊት በድፍረት ቆሞ አንተ ሕግ ሳትሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ’ መምህርም ሳትሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ በሠራችሁ ብለህ የምትፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆንክን አውቃለሁና ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ ብየ ፈርቼ ሃይማኖቴን በልቡናየ ይዠዋለው በአዕምሮየ ጠብቄዋለሁ የሚል ሃይማኖቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ሰነፍ ሰውን ያመለክታል፡፡

ለዚህ ዓይነት ሰው የጌታ መልስ ደግሞ በምሳሌው መሠረት የሚከተለው ነው፡፡ እኔ ሕግ ሳልሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ መምህር ሳልሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ አውቃችሁ በሠራችሁት ብየ የምፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን? እንዲህስ ካወቅህ ሹመትክን ልትመልስልኝ ይገባኝ ነበር፡፡ ወጥቶ ወርዶ ለሚያስተምር በሰጠሁት ነበር፡፡ አሁንም የእርሱን መምህርነት ሹመት ነሥታችሁ (ወስዳችሁ) ለዚያ ደርቡለት! እርሱን ግን አውጡት የሚል ነው፡፡ ዛሬም እያንዳንዳችን በዓቅማችን መጠን መክሊት ተሰጥቶናል፡፡ በመሆኑም መክሊቱን እንደቀበረው እንደዚያ ሰው የተሰጠንን ቀብረን ለወቀሳና ለፍርድ እንዳንሰጥ በአገልግሎታችን ልንተጋ ይገባናል፡፡

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ሲገልጥ ‹‹አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግሥና ይስጥ›› (ሮሜ12፥7) በማለት ተናግሯል፡፡ ለመሆኑ ዛሬ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ…›› ተብሎ በእግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችል ማን ይሆን? በእውነት በዘመናችን እንዲህ ተብሎ የሚመሰገን በጎና ታማኝ ካህን’ ታማኝ መምህርና ሰባኪ’ ታማኝ ዘማሪ የመሳሰለውን ማግኘት ይቻል ይሆንን? ትልቅ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው ጥያቄ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ስለ ታማኝነት የሁላችንንም ሕይወት የሚዳስስና ሁላችንንም የሚመለከት ነውና፡፡

 

በእርግጥም ዛሬም ቢሆን እንደ አባቶቻችን ማለትም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት’ በትዕግስት በፍቅር’ በትህትናና በትጋት በማገልገል የተሰጣቸውን መክሊት የሚያበዙ አገልጋዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ክብራቸው በምድርም በሰማይም እጅግ የበዛና ራሳቸውን አስመስለው በትምህርት የወለዷቸው ልጆቻቸውም ለቤተክርስቲያን ውድ ልጆች ናቸው፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን’ ቅዱስ ጳውሎስም ጢሞቴዎስን አፍርተዋል፡፡

 

ሌሎችም አበው ቅዱሳን በወንጌል ቃል መንፈሳውያንና ትጉሃን የሆኑ ምእመናንን በሚገባ አፍርተዋል፡፡ ያላመኑትንም አሳምነው ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመመለስ ለዘላለማዊ ክብር የበቁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል፡፡ በመሆኑም በክርስቶስ በደሙ የተከፈለውን ወደር የሌለውን ዋጋ ዓለም አምኖና አውቆ በክርስትና ሃይማኖት እንዲድንበትና እዲጠቀምበት በማድረግ እንዲሁም በታማኝነት ሥራቸው ጥንትም ዛሬም ላለችዋና ወደፊትም ለምትኖርዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ድምቀትም ውበትም የሆኑት ቅዱሳን አበው ሊገኙ የቻሉት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ደስ ለማሰኘት በመድከማቸው ሳይሆን የተጠሩበትን ዓላማና የጠራቸውን እርሱን በሚገባ አውቀውና ከልብ ተረድተው ለዘላለማዊ ህይወት ተግተው በመሥራታቸው ነው፡፡ (ገላ1፥10)

ዛሬም በዚህ ዘመን ያለንና በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን የተጠራን ሁላችንም የተሰጠንን መክሊት (ጸጋ) አውቀን ለእግዚአብሔር ለአምላካችን በመታመን ወጥተን ወርደን ሌላ ልናተርፍ ይገባናል፡፡ በተለይ ደግሞ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ያለ ሰው ከምንም በላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ኃላፊነት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖትም በሥነምግባርም ለሌላው ዓርዓያ በመሆን እንደ እርሱ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር አስተባብረው የያዙ ምእመናንን ማፍራት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ልንባል የምንችለው፡፡ 

 

አሁን ባለንበት በዘመናችን ብዙ ፈታኝ የሆኑ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ኃላፊነትን መዘንጋት ናቸው፡፡ በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደ ቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡

 

ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በህይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅሰን የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› (ማቴ24፥42) ብሎናል፡፡

እንግዲህ ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በደሙም መፍሰስ ህይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘላለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላክ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመታመን እርሱ ያዘዘንን ሁሉ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ምን ጊዜም ትጉህ ሠራተኛ ደግሞ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል፡፡