ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፡፡
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡
ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም
እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፡፡ / 1ኛ ጴጥ 4፤7/
በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችንና ግድያዎችን ሁሉ እናወግዛለን፡፡ በየቦታው የተከሰቱ ችግሮች እንዲቆሙም በድርጊቱ የሚሳተፉ አካላትን ሁሉ እንማጸናለን፤ እናሳስባለንም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን
የክርስትና ሃይማኖት ማእከላዊ ጉዳዩ ሰው ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆነ፣፤ ሰውም አምላክ ሆነ፣ የሚለው የትምህርቱ አስኳል ዋና ነጥብም የሚያመለክተው የነገራችን ሁሉ ማእከል ሰው መሆኑን ነው፡፡ ይህም ለሰው ሲባል አምላክ እንኳ ራሱን ዝቅ አድርጎ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጡንና በዚሀም ሰውን ከወደቀበት ማንሣቱን፤ ከዚያም በላይ ሰውን በተዋሕዶ ለአምላክነት ክብር ማብቃቱን የሚገልጽ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዐለምአቀፋዊ ሆነው በትልቁ የሚከበሩት የአምላካችን ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት ሁሉ ማእከላዊ ነጥባቸው ሰው ነው፡፡ ሁሉም ነገሮች አምላክ ለሰው ሲባል ያደረጋቸው ናቸውና፡፡
ሌሎች አስተምህሮዎች ሁሉ አሁንም ሰውን ለማስረዳት ሲባል የተለያዩ አርእስት ይሰጣቸው እንጂ ማእከላዊ ነጥባቸው አንድ ነው፤ የሰው ድኅነትና ደኅንነት፡፡ የአንድ ሰው ጽድቁም ኃጢአቱም የሚለካው ለሰው በሚያደርገው ወይም በሰው ላይ በሚያደርገው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህም በምድር ላይ ከሰው በላይ የከበረና ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባው ምንም ፍጥረት የለም፡፡ በምድር ላይ ጥንቃቄና ዕርምት የሚወሰድበት ነገር ሁሉ የመጨረሻ ዓላማው ሰውን ለመጥቀም ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ከሰው የሚጣላ ከአምላኩም ከአጠቃላይ ከፍጡራንም ሁሉ ጋር የሚጣላ ይሆናል፡፡ በሰው ላይ ያልተገባውን ድርጊት የሚፈጽም ሁሉ በፈጣሪው ላይ የሚያደርግ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፤ ፈጣሪ ሰው መሆንን በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኖ ተገልጧልና በሰው የሚደረግ ሁሉ በእርሱ ላይ የሚደረግ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
የክርስትና ሃይማኖት መምህራንና ተቋማት ዋና ዐላማና ተልእኮም ሊመነጭ የሚችለው ከዚህ መሠረታዊ የሰው ክብርና ዋጋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የዓለም ክፍል በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈጸሙ መጥፎ ተግባራት ይልቁንም ከሕግ ማሕቀፍ የወጡትንና በሴራና በተንኮል የሚፈጸሙትን እንደ ማኅበር አብዝተን እናወግዛቸዋለን፤ እንጸየፋቸዋለንም፡፡ ይልቁንም በሀገራችን በኢትዮጵያ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው ንጹሐንን ሰለባ እያደረገ ያለው የተቀነባበረና የተነጣጠረ የሚመስለው ጥቃት በእጅጉ የሚያሳስብ መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡