ካህናተ ሰማይ

ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ቅዱሳን መላእክት ምሕረትን ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ልጅ፤ ጸሎትን ከሰው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ለዘለዓለም የማይሞቱ ረቂቃን መናፍስት ናቸው፡፡ በመዓርጋቸውና በነገዳቸውም ኪሩቤል፣ ሱራፌል፣ ኃይላት፣ አርባብ፣ መናብርት፣ ሥልጣናት፣ መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ተብለው ይመደባሉ፡፡ ‹‹ወኍልቆሙ ለእሙንቱ መላእክት ወሊቃነ መላእክት መናብርት ወሥልጣናት አጋእዝት ኃይላት ወሊቃናት ኪሩቤል ወሱራፌል›› እንዲል /አንቀጸ ብርሃን፤ ኵሎሙ ዘመላእክት/፡፡

በአቀማመጥም ኪሩቤል፣ ሱራፌልንና ኃይላትን በኢዮር፤ አርባብን፣ መናብርትንና ሥልጣናትን በራማ፤ መኳንንትን፣ ሊቃናትንና መላእክትን በኤረር አስፈሯቸዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በተሰወረባቸው ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹እኔ ነኝ ፈጣሪያችሁ›› በማለቱ መንፈስ ቅዱስ አረጋግቶ ኅቡዕ ስሙ የተጻፈበትን ሠሌዳ ሰጥቷቸው፤ አንድም እሑድ በነግህ የተፈጠረው ብርሃን ዕውቀት ኾኗቸው ቅዱሳን መላእክት ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ›› ብለው ምሥጢረ ሥላሴን አምልተው አስፍተው ተናግረዋል /ኩፋሌ ፪፥፰፤ ኢሳ. ፮፥፫/፡፡ ይህንን ሃይማኖታቸውን ምክንያት አድርጎ በየነገዳቸው አለቃ ሹሞ ቀብቷቸዋል (አክብሯቸዋል)፡፡

በዚህም መሠረት በኢዮር ያሉት መላእክት አራት አለቃ፣ ዐርባ ነገድ ኾነው የተመደቡ ሲኾን ከእነዚህም ዐሥሩ የኪሩቤል፣ ዐሥሩ የሱራፌል ነገድ ነው /መዝ.፳፫፥፯-፲፤ ማቴ.፳፬፥፴፩/፡፡ በቍጥርም ዘጠና ዘጠኝ ነገድ ናቸው፡፡ ‹‹ኀዲጐ ተስዓ ወተስዓተ ነገደ ቆመ ማእከለ ባሕር›› እንዲል /ሰላም ዘጥምቀት፤ ራእ. ፲፪፥፱/፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ሃያ አራት ሊቃነ መላእክትን መርጦ በመንበረ መንግሥት ዙሪያ ክንፍ ለክንፍ አያይዞ አቁሟቸዋል፡፡ የብርሃን ዘውድ (አክሊል) ደፍቶላቸዋል፡፡ የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ አስይዟቸዋል፡፡ እንደዚህ አድርጎ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህም ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ይባላሉ፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እንደምናገኘው በየዓመቱ ኅዳር ፳፬ ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሰማያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የካህናተ ሰማይ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ካህናተ ሰማይ አገልግሎት የሚያስገነዝብ አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ሱራፊ ማለት መልአክ፣ ከካህናተ ሰማይ አንዱ ማለት ነው፡፡ ሱራፌን፣ ሱራፌል፣ ሱራፌም (በፅርዕ ሴራፊም፣ በዕብራይስጥ ስራፊም) ማለት የነገድ ስም፣ ልዑላን መላእክት፣ ሊቃናት፣ የሚያጥኑ፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ቀዳሾች ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፰፻፹፮/፡፡ ከዚህ ላይ ሱራፊ ነጠላ ቍጥርን፤ ሱራፌል ደግሞ ብዙ ቍጥርን ያመለክታል፡፡ ሱራፌል ለቅዱሳን በሰው አምሳል በመገለጣቸው ሽማግሌዎች ተብለው ተጠርተዋል /ኢሳ.፳፬፥፳፫፤ መሳ.፲፫፥፪-፳፭፤ ዳን.፲፥፲፰-፳፩/፡፡ በግእዝ ቋንቋ ደግሞ ካህናተ ሰማይ ይባላሉ፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው የሚሰጡትን ሰማያዊ አገልግሎት የሚያመለክት ስም ነው፡፡

በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንደ ተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ ሰኑይ (ሰኞ) ከኪሩቤል ሠራዊት ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳን፣ ከሱራፌል ሠራዊት ገጸ ንሥርና ገጸ እንስሳን ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት በላይ፣ ከሰማይ ውዱድ በታች ጀርባቸውን ወደ ውስጥ፣ ፊታቸውን ወደ ውጭ አድርጎ አቁሟቸዋል፡፡ ይኸውም ‹‹የኔን የፈጣሪያችሁን ፊት ማየት አይቻላችሁም›› ሲል ነው፡፡ የኪሩቤል አለቃቸው ማለትም ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳ ኪሩብ፤ የሱራፌል አለቃቸው ማለትም ገጸ ነሥርና ገጸ ላሕም ደግሞ ሱራፊ ይባላል /ሥነ ፍጥረት ዘእሑድ/፡፡

ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በዙሪያውም ሃያ ዐራት ካህናት አሉ፡፡ በፊታቸው የበጉን ሥዕል፣ ደምን የተረጨች ልብስንም፣ የታተመ መጽሐፍንም ያያሉ፡፡ መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› /ራእ. ፬፥፮፤ ፭፥፰/ በማለት ስለ ሱራፌል ሰማያዊ አገልግሎት የተናገረ ሲኾን፣ ‹‹በፊታቸው የበጉን ሥዕል ያያሉ›› ማለቱ የክርስቶስን ትስብእት በጌትነት ያዩታል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ወደቁ›› ሲልም መስገዳቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹በግ›› የተባለውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ደምን የተረጨች ልብስ›› ማለቱም ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ መቀበሉን፤ የታተመ መጽሐፍ የክርስቶስ ትስብእት የማይመረመር መኾኑን፤ ‹‹ለበጉ ሥዕል፣ ለታለለችው ልብስና ለታለለው መጽሐፍ ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› ሲልም ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትም በሦስትነትም ለሚመለከው ለክርስቶስ ደግመው ደጋግመው ምስጋና ማቅረባቸውንና መገዛታቸውን ያመለክታል /የሠለስቱ ምእት ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ፣ ፫፥፯-፱/፡፡

ነቢዩ ሕዝቅኤልም ካህናተ ሰማይ ያለ ዘር መገኘታቸውን ሲያመለክት ‹‹በመንበሩ ዙሪያ ቁመው ያሉ ካህናት ኅብራቸው መረግድ የሚባል ዕንቍን ይመስላል›› በማለት ተናግሯል፡፡ ጸጋቸውን ሲገልጽ ደግሞ ‹‹ብሩህ ልብስ ለብሰዋል፤›› ክብራቸውን ሲመሰክርም ‹‹በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተዋል›› ብሏል፡፡ ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የንጽሕናቸውና የቅድስናቸው መገለጫ ሲኾን፣ በራሳቸው ላይ የተቀዳጁት ዘውድ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ዘለዓለማዊ ክብር ያሳያል፡፡ ቍጥራቸው በሃያ አራት መገለጹም ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ኾኗቸው ለሃያ አራት ሰዓታት ሳያቋርጡ ጸሎትና ምስጋናን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡ አንድም የ፲፪ቱ ነገደ እስራኤል እና የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ሲኾን (፲፪ + ፲፪ = ፳፬) ይኸውም የብሉይና የሐዲስ ኪዳን አባቶች በአንድነት ኾነው እንደ ሱራፌል በምድር በቤተ መቅደስ፤ እንደዚሁም በሰማይ በገነት (በመንግሥተ ሰማያት) ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ የሚያመሰግኑ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ በዘመነ ብሉይ ደብተራ ኦሪትንና መቅደሰ ኦሪትን በሃያ አራት ሰሞን ተመድበው ያገለግሉ የነበሩ ካህናትም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌዎች ናቸው /፩ኛዜና. ፳፬፥፩-፲፱፤ ሕዝ. ፩፥፭-፳፪፤ ራእ. ፭፥፰-፲፬/፡፡

ካህናተ ሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሲያቀርቡ አክሊሎቻቸውን ከራሳቸው ላይ አውርደው ያለማቋረጥ ይሰግዳሉ፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ይህንን ሰማያዊ ሥርዓት እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ ‹‹ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ፤ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) በመንበሩ ዙሪያ ቆመው በፊቱ ሲሰግዱ የመለኮት እሳት ሲበርቅ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ፤›› /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡ ይህም ምስጋና በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ የጸሎት ክፍሎች ይገኛል፡፡ ‹‹…. ወባቲ ለዛቲ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ መላእክት አርአያ ዘበሰማያት ቤተ ክርስቲያሰ ትትሜሰል በጽርሐ አርያም ዘላዕሉ ….፤ .… ለዚህች ቤተ ክርስቲያን በሰማያዊው አገልግሎት አምሳል የመላእክት የአገልግሎት ሥርዓት አላት፡፡ ቤተ ክርስቲያንስ በላይኛው (በሰማያዊው) ጽርሐ አርያም ትመሰላለች ….›› እንዳሉ አባ ጊዮርጊስ /ሰዓታት፣ ኵሎሙ ዘዘወትር/፡፡

ዛሬም ምድራውያን ካህናት ማዕጠንትና መስቀል ይዘው በመንበሩ ፊት ቆመው ሲያጥኑ የሚሰግዱት፤ እንደዚሁም ኪዳን ሲያደርሱና ወንጌል ሲያነቡ መጠምጠሚያቸውን የሚያወርዱት ከዚህ ሥርዓት በመነሣት ነው፡፡ ሱራፌል በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ማዕጠንት ይዘው፣ እንደሚሰግዱና አክሊላቸውን እንደሚያወርዱ ኾነው በሥዕለ ሥላሴ ግራና ቀኝ የሚሣሉትም ይህንን አገልግሎታቸውን ለማስታዎስ ነው፡፡ እንደ ጸሎተ ዕጣን፣ ቅዳሴ፣ ማኅሌት፣ የመሰሉ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፎች ዅሉ ከካህናተ ሰማይ የተወረሱ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሠረት የኾነው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቱን የተቀበለው ከሱራፌል መኾኑንም ‹‹ሃሌ ሉያ ዋይዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዓ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ፤ ‹ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን፡፡ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ የጌትነትህ ቅድስና በሰማይ በምድር መላ› እያሉ ሲያመሰግኑ በሰማይ ከመላእክት የሰማሁት ዜማ ምንኛ ድንቅ ነው?›› ከሚለው የአርያም ክፍል ከኾነው ጣዕመ ዜማው ለመረዳት እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው፣ በማኅሌቱና በሰዓታቱ የካህናተ ሰማይ አገልግሎታቸውና ስማቸው በሰፊው ሲጠራ ይኖራል፡፡

ሠለስቱ ደቂቅ ‹‹እግዚአብሔርን አራዊትና አንስሳት ዅሉ ያመሰግኑታል›› በማለት እንደ ተናገሩት ካህናተ ሰማይ ሱራፌል ሌሊትና ቀን ምስጋና ሲያቀርቡ የክንፎቻቸውን ድምፅ ሲሰማ ዶሮ እንደሚጮኽና እግዚአብሔርንም እንደሚያመሰግን በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፤ ‹‹ቀን በስድስተኛው ሰዓት የኪሩቤል ልመና ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡ ሌሊት በአራተኛው ሰዓት ሱራፌል ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ በዐሥረኛው ሰዓትም ሰማያት ይከፈታሉ፤ እግዚአብሔርም የሰውን ልጆች ጸሎት ይሰማል፡፡ የለመኑትንም ዅሉ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህችም ሰዓት ከሱራፌል ከክንፎቻቸው ድምፅ የተነሣ ዶሮ ይጮኻል፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናል፤›› /ሥነ ፍጥረት ዘእሑድ/፡፡

እኛ የሰው ልጆችም የተፈጠርንለት ዓላማ የእግዚአብሔርን ስም ለመቀደስ፣ መንግሥቱንም ለመውረስ መኾኑን በማስተዋል ስለ ግሩምና ድንቅ ሥራው ዅሉ ‹‹አቤቱ የኀያላን አምላክ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ሥራህም ድንቅ ነው›› /መዝ. ፵፯፥፪/ እያልን ዘወትር አምላካችንን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ በምድር በቤተ መቅደሱ፣ በሰማይም በመንግሥቱ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያልን እግዚአብሔርን ከቅዱሳን መላእክት ጋር ለማመስገን ያብቃን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ እኛንም በካህናተ ሰማይ ጸሎት ይጠብቀን፤ በረከታቸውም ይደርብን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

የጽዮን ምርኮ – ክፍል ሦስት

ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ሰባበረችው /፩ኛ ሳሙ. ፭፥፩-፭/

ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ድል አድርገው ታቦተ ጽዮንን ወደ አዛጦን ወሰዱአት፡፡ በዚያም ከቤተ ጣዖታቸው አስገብተው ዳጎን የተባለውን ጣዖት ከፍ ባለ መቀመጫ አድርገው እርሷን ግን ከታች አስቀመጧት፡፡ ሲነጋም የአዛጦን ሰዎች ማልደው ለጣዖቱ ሊሰግዱ ቢሔዱ ዳጎንን በግምባሩ ወድቆ አገኙት፡፡ አንሥተው ወደ ቦታው መለሱት፤ በነጋ ጊዜ እንደልማዳቸው ቢሔዱም እነሆ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በምድር ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ራሱ፣ እጆቹም ተቈራርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ደረቱ ብቻውን ቀርቶ ነበር፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ንጉሥ በመንግሥቱ ገበሬ በርስቱ እንደማይታገሥ እግዚአብሔርም በአምላክነቱ ከገቡበት አይታገሥም›› እንዲሉ ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦተ ጽዮንን በጣዖት ቤት ከጣዖት እግር ሥር በማስቀመጣቸው እግዚአብሔር በቍጣ ተነሣባቸው፡፡ ኃይሉንም በታቦቱ ላይ አሳረፈ፤ ታቦተ ጽዮንም ዳጎንን ቀጠቀጠችው፤ ሰባበረችው፡፡

ይህ ታሪክ የሐዲስ ኪዳን የማዳን ሥራ ምሳሌነት አለው፡፡ ቀደም ብሎ እንዳየነው ታቦተ ጽዮን የወላዲተ አምላክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ሰባበረችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇን አዝላ ወደ ግብጽ በምታደርገው የስደት ጕዞ በምታቋርጣቸው መንገዶችና መንደሮች ዅሉ ያሉ ጣዖታት ይሰባበሩ ነበር፡፡ በግብጽ ያሉ ጣዖታት ማንም ሳይነካቸው ተሰባብረዋል፤ በውስጣቸው አድረው ሲመለኩ የነበሩ አጋንንትም በአምሳለ ሆባይ (ዝንጀሮ) እየወጡ ሲሔዱ ይታዩ ነበር /ነገረ ማርያም/፡፡ ዳጎን በታቦተ ጸዮን ፊት በግምባሩ እንደ ተደፋ እመቤታችንም በስደቷ በሲና በረሃ ስትጓዝ ያገኟት ሽፍቶች መዝረፋቸውን ትተው በፊቷ ሰግደው ሸኝተዋታል፡፡ ዳግመኛም በዕለተ ዕረፍቷ አስከሬኗን አቃጥላለሁ ብሎ የአልጋውን ሸንኮር የያዘው ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እጁን በሰይፍ በቀጣው ጊዜ እመቤታችን ይቅር ትለውና ትፈውሰው ዘንድ ግምባሩን መሬት አስነክቶ ሰግዶላታል፡፡

እንደዚሁም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦተ ጽዮን ይመሰላል፡፡ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እንደ ተገኘ ጌታችን በሥጋ ሰብእ ተገልጦ ወንጌለ መንግሥት በሚያስተምርበት ዘመንም አጋንንት ‹‹ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ያለ ጊዜያችን አታጥፋን›› እያሉ ይሰግዱለት እንደ ነበር በቅዱስ ወንጌል በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብም ‹‹አጋንንትኒ የአምኑ ቦቱ ወይደነግፁ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤›› በማለት ተናግሯል /ያዕ. ፪፥፲፱/፡፡ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ቀጠቀጠችው (እንደ ሰባበረችው) ዅሉ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ቀጥቅጧቸዋል፡፡ ታቦተ ጸዮን የወርቅ ካሣ ተሰጥቷት ከምድረ ፍልስጥኤም እንደ ወጣች ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወርቀ ደሙ ካሣነት የሲዖልን ነፍሳት ከሲዖል አውጥቷል፡፡

ጌታችን ለድኅነተ ዓለም በመስቀል ተሰቅሎ አዳምን ወክሎ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምንት ኀደገኒ)፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› በማለት ሲጣራ ሰምቶ ዲያብሎስ ‹‹ሥጋውን ወደ መቃብር፣ ነፍሱን ወደ ሲዖል ላውርድ›› ብሎ ቀረበ፡፡ የጌታ ጩኸትም አንድም ለአቅርቦተ ሰይጣን ነውና ሰይጣንን በአውታረ ነፋስ /ሥልጣነ መለኮት/ ወጥሮ ያዘው፤ ያን ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹መኑ ውእቱ መኑ ውእቱ፤ ማነው ማነው›› እያለ መለፍለፍ ጀመረ /ትምህርተ ኅቡአት/፡፡ ከብዙ መቀባጠር በኋላም ‹‹አቤቱ ጌታዬ በድዬሃለሁ፤ ነገረ ልደትህን የተናገሩትን ነቢያት እነ ኢሳይያስን በምናሴ አድሬ በመጋዝ አስተርትሬአለሁ፤ ለበደሌ የሚኾን ካሣ የለኝም፤ የሲዖልን ነፍሳት በሙሉ እንደ ካሣ አድርገህ ውሰድ፡፡ እኔንም ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ›› በማለት አጥብቆ ለመነው፡፡ ጌታችንም ዲያብሎስን አስሮ ከአዳም ጀምሮ በሲዖል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ የሲዖል ኃይላት ተሰባበሩ፤ ከመለኮቱ ብርሃን የተነሣም የሲዖል ጨለማ ተወገደ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን፣ ሊቃነ አጋንንትን፣ ሠራዊተ አጋንንትን፣ የሲዖልን ኃይላትን አጥፍቶልናልና ቅዱስ ዳዊት ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት ‹‹እስመ ሰበረ ኆኃተ ብርት ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘኀፂን፤ የናሱን ደጆች ሰብሯልና፡፡ የብረቱንም መወርወሪያ ቀጥቅጧል፤›› በማለት ዘመረ /መዝ. ፻፮፥፲፮/፡፡ ነቢዩ አጋንንትን ኆኀተ ብርት (የነሐስ ደጆች) ብሎአቸዋል፡፡ የነሐስ መዝጊያ ጠንካራ እንደ ኾነ አጋንንትም በአዳምና ልጆቹ ላይ መከራ አንጽተውባቸው ነበር፡፡ የአጋንንት ክንድ በሰው ልጆች ላይ ከብዶ ነበርና ሊቃነ አጋንንትን መናሥግተ ኀፂን (የብርት መወርወሪያ ወይም ቍልፍ) ብሏቸዋል፡፡ ቤት በብርት መወርወሪያ (ቍልፍ) ከተዘጋ እንደማይከፈት ሲዖልም ለ፶፭፻ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ) ዘመን ተዘግታ የነፍሳት ወኅኒ ቤት ኾና ኖራለችና አዳሪውን በማደሪያው ጠራው፡፡ ከመዝጊያው መወርወሪያው (ቍልፉ) እንዲጠነክር ወይም መዝጊያ በቍልፍ እንዲጠነክር ከአጋንንት አለቆች (ሊቃነ አጋንንት) ይበረታሉና መናሥግተ ኀፂን (የብረት መወርወሪያ) አላቸው፡፡ አምስቱ የፍልስጥኤም ነገሥታት ሲሰግዱለት የነበረውን ዳጎንን ታቦተ ጽዮን እንደ ቀጠቀጠችው ዅሉ መድኀኒታችን ክርስቶስም ለ፶፭፻ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ) ዘመን የተደራጀውን የአጋንንት ኃይል በሥልጣኑ ሰባብሮታል፡፡

ለታቦተ ጽዮን ካሣ እንደ ተሰጣት /፩ኛ ሳሙ. ፮፥፩-፱/

የእግዚአብሔር እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ በረታችባው፤ ሰዎቹንም በእባጭ ቍስልም መታቻቸው፤ አጠፋቻቸው፡፡ ታቦተ ጽዮንን ወደ አስቀሎና በወሰዷት ጊዜም አስቀሎናውያንንም በእባጭ መታቻቸው፡፡ ምድራቸውም በአይጦች መንጋ ተወረረ፡፡ እጅግ ዋይታና ጩኸት ኾነ፣ ታቦተ ጽዮን በፍልጥኤማውያን ላይ መቅሠፍት እንዳበዛችባቸው ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ በኀይል ወርዶባቸዋልና አምስቱ የፍልስጥኤም ነገሥታት (አዛጦን፣ አስቀሎና፣ አቃሮን፣ ጌትና ጋዛ) ከካህናተ ጣዖትና ከሟርተኞች ጋር እንዲህ በማለት ተማከሩ፤ ‹‹የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰዱ የበደል መሥዋዕት መልሱ እንጂ ባዶውን አትስደዱት፡፡ በዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፡፡ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደኾነ ታውቃላችሁ፤›› /፩ኛ ሳሙ. ፮፥፫/፡፡

በዚህ ተስማምተው በአምስቱ የፍልስጥኤም ግዛቶች ቍጥር አምስት የወርቅ አይጦችንና አምስት የወርቅ እባጮችን ቅርፅ አዘጋጁ፡፡ ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት የሚያጠቡ ላሞንም ጠምደው በሠረገላ ከተዘጋጀው ወርቅ ጋር ታቦተ ጽዮንን ጫኑ፡፡ ሠረገላውን እየጐተቱ ከፍልስጥኤም ወጥተው ወደ ቤትሳሚስ ሔዱ፡፡ ሠረገላውም ወደ ቤትሳምሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ በደረሰ ጊዜ በዚያ ቆመ፡፡ የዚያ አገር ሰዎችም ታቦቱና ወርቁ የተጫነበትን ሣጥን ሲያወርዱ ወደ እግዚአብሔር ታቦት የተመለከቱ ሰባ ሰዎች በመቀሠፋቸው ምክንያት ቤትሳምሳውያን በፍርሃት ተዋጡ፡፡ የቂርያትይዓሪ ሰዎችም ታቦተ ጽዮንን በአሚናዳብ ቤት አኖሯት፤ አልዓዛር ወልደ አሚናዳብም ታቦቷን እንዲያገለግል ተደረገ፡፡ በዚያም ታቦተ ጽዮን ለሃያ ዓመት ኖረች፡፡ ከዚህ ታሪክ ለሐዲስ ኪዳን ምሳሌዎች የሚኾኑ ትምህርቶችን እናገኛለን፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ዮሐንስ በነበረችበት ዘመን ወደ ቀራንዮ እየወጣች በልጇ መቃብር ላይ ትጸልይ ነበር፡፡ ጸሎቷም በሲዖል ያሉ ነፍሳትንና በሕይወተ ሥጋ ያሉ ኃጥአንን ማርልኝ በማለት ነበር እንጂ ስለራሷ ተድላ ደስታ አልነበረም፡፡ ‹‹ወእምአሜሃ ነበረት እግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ እንዘ ተኀዝን ወትስእል በእንተ ኵሎሙ ኃጥአን ዘከመ ዛቲ ዕለት አመ ፲ወ፮ ለየካቲት በከመ ልማዳ ቆመት መካነ ቀራንዮ ወሰአለቶ ለወልዳ፤ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን በዚያች በየካቲት ፲፮ ቀን ቀራንዮ በሚባል ቦታ ቆማ ልጅዋን እንደ ልማዷ ስትለምን ኖረች›› እንዲል ተአምረ ማርያም፡፡

እንኳን የእናቱን ልመና የኀጥኡን ጸሎት የሚሰማ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክትን፣ ቅዱሳን አበውን አስከትሎ ወረደና ‹‹ይኩን በከመ ትቤሊ እፌጽም ለኪ ኲሎ መፍቅደኪ አኮኑ ተሰባእኩ በእንተ ዝንቱ፤ የለመንሽው ዅሉ ይደረግልሽ፤ የምትወጂውን ዅሉ እፈጽምልሻለሁ፡፡ የለመንሽውን ዅሉ ላደርግልሽ ሰው ኾኛለሁና›› በማለት ታላቅ የምሕረት ኪዳን ሰጣት፡፡ በዚህ የምሕረት ኪዳንም እጅግ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡ እስከ ምጽአትም ድረስ በቃል ኪዳኗ የሚታመኑ ምእመናን ከሲዖል ይወጣሉ፡፡ ታቦተ ጽዮን ከምድረ ፍልስጥኤም የወርቅ አይጦችና እባጮች ካሣ ተሰጥቷት እንደ ወጣች እመቤታችንም ሞተ ሥጋን የተቀበለችው በሞቷ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል እንደሚወጡ ቃል ኪዳን ተሰጥቷት ነበርና በዕለተ ዕረፍቷ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡ ለእመቤታችን የሞት ካሣ ኾነው የኀጥአን ነፍሳት ተሰጥተዋታል፡፡ ማለትም በሞቷ የኀጥአን ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡

ይቆየን፡፡

የጽዮን ምርኮ – ክፍል ሁለት

ኅዳር ፳፪ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

 የአፍኒንና ፊንሐስ ኀጢአት ….

፬ኛ የአባታቸውን ምክር አለመስማታቸው

ካህኑ ዔሊ ልጆቹ ያደረጉትን ኃጢአት ዅሉ ሰምቶ ‹‹ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሰምቻለሁና ስለምን እንደዚህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? ልጆቼ ሆይ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይኾንም፡፡ ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፡፡ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማነው?›› በማለት ቢመክራቸውም ‹‹ልጥፋ ያለች ከተማ ነጋሪት ቢጐሰምም አትሰማም›› እንዲል የአበው ብሂል አፍኒንና ፊንሐስ የአባታቸውን ቃል አልሰሙም ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፫-፳፭/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ደዊት ‹‹ዘይሴሰይ እክልየ አንሥአ ሰኰናሁ ላዕሌየ፤ እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ›› /መዝ.፵፥፱/ እንዳለው ዛሬም የአባቶችን ትምህርትና ተግሣፅ የማይሰሙ፤ የቤተ ክርስቲያንን እክለ ትምህርት ተመግበው አድገው ጠላቶቿ የኾኑ ውሉደ አፍኒን ወፊንሐስ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ከትእዛዛተ እግዚአብሔር አንደኛው ‹‹አባትና እናትህን አክብር›› የሚለው ነው፡፡ መቼም አባት ሲባል ማን ማንን እንደሚመለከት የማያውቅ የለም፡፡ በሐዋርያት እግር የተተኩ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳትን እያቃለሉ ‹‹በቅዱስ ሲኖዶስ አንመራም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አርጅታለች፤ እናድሳት፤›› በማለት በክርስቶስ ደም የተመሠረተች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የሚጥሱ ራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ›› እያሉ የሚጠሩ ምናምንቴዎች እጣ ፈንታቸው እንደ አፍኒንና ፊንሐስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አረጀች ከተባለ የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም፣ በሐዋርያት ስብከት ነውና ክርስቶስ አርጅቷል፤ የሐዋርያትም ትምህርት ጊዜው አልፏል ማለት ነዋ? ለአንዲት ቃል እንኳን ትርጕም መስጠት የማይችሉ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስን እንተረጕማለን፤ ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን›› በማለት የሚያሳዩት ድፍረት ለእነርሱ ዕውቀታቸው መኾኑ ነው፡፡ ‹‹የሰነፍ ዕውቀቱ ድፍረቱ›› እንዲል የአበው ብሂል፡፡

ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ‹‹ተሰአሎ ለአቡከ ወይነግረከ ወለሊቃውንቲከ ይዜንዉከ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ያስታውቅህማል፡፡ ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ይነግሩህማል›› /ዘዳ. ፴፪፥፯/ በማለት እንደ ተናገረው አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚናገሩትን፣ ሊቃውንቱ የሚያስተምሩትን የሚሰማና በትምርታቸው የሚመራ ከስሐትት ይድናል፡፡ የዔሊ ልጆች የአባታቸውን ቃል ሰምተው ተጸጽተው ቢኾን ኖሮ በኢሎፍላውያን ሰይፍ ባልወደቁም ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን እክለ ትምህርቷን ተመግበው ያደጉ ልጆቿ ሲጠፉባት ታዝናለች፡፡ ስለዚህም ‹‹አብዳነ አጥብብ፤ ሰነፎችን አለብም›› እያለች ትጸልያለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ የራሷን ልጆች ከመጠበቅ ባገሻገር ከውጭ ያሉትንም ወደ ውስጥ ማስገባት ነውና፡፡ ‹‹ከዚህም በረት ያልኾኑ ሌሎች በጐች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፡፡ ድምፄንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይኾናሉ፤ እረኛውም አንድ›› እንዳለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ /ዮሐ. ፲፥፲፮/፡፡

የካህኑ ዔሊ አለመታዘዝ

እግዚአብሔር አምላክ ዔሊን ምስፍናን ከክህነት ጋር አስተባብሮ በእስራኤል ላይ ለዐርባ ዓመት እንዲያገለግል አክብሮት ነበር፡፡ ዔሊ ግን ከእግዚአብሔር ይልቅ ለልጆቹ አደላ፡፡ የኀጥኡን ድኅነት እንጂ ጥፋቱን የማይወደው እግዚአብሔር ዔሊን በነቢዩ ላይ አድሮ መክሮት ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፯-፴፯/፡፡ ዳግመኛም ልጆቹ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የሚያደርጉት ነውር በብላቴናው በሳሙኤል ተነግሮት ነበር፡፡ የዔሊ ትልቁ ጥፋት ልጆቹን ከሥልጣናቸው አለመሻሩ ነበር፡፡ ምክር ለማይሰማ እርምጃ መውሰድ ግድ ነውና፡፡ ስለዚሀም ካህኑ ዔሊ ‹‹ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ?›› ተብሎ በእግዚአብሔር ተወቀሰ /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፱/፡፡ ‹‹ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊኾን አይገባውም›› /ማቴ. ፲፥፴፯/ እንዳለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል፡፡

ካህኑ ዔሊ ከእግዚአብሔር ፍቅር ተለየ፡፡ ልጆቹን የማይገሥፅ እርሱ ልጆቹን አይወድምና፡፡ ‹‹በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድ ግን ተግቶ ይገሥፀዋል›› /ምሳ. ፲፫፥፳፬/ እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን፡፡ በበትር መምታት ማለት ጽኑዕ ተግሣፅ ማለት ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ተግተው የማይገሥፁ፣ ውሏቸውንም የማይከታተሉ ከኾነ ጉዳቱ ከራሳቸው አልፎ ለአገርም ይተርፋል፡፡ በምግባር፣ በሃይማኖት ኰትኵተው የሚያሳድጉ ወላጆች ተተኪ የቤተ ክርስቲያን ትውልድ፤ አገር ተረካቢ ዜጎችን ያፈራሉ፡፡ ዔሊ ልጆቹን ተግቶ ባለመገሠፁ ራሱንም ልጆቹንም አጥቷል፡፡ ዛሬም መንፈሳዊ ተልእኮአቸውን በአግባቡ የማይወጡ አገልጋዮችን የማይገሥፁ አባቶች ከዔሊ ውድቀት ሊማሩ ይገባቸዋል፡፡ እለእስክንድሮስ ከሐዲውን አርዮስን እንደ ገሠፀው እና ከስሕተቱ አልመለስም ባለ ጊዜም እንዳወገዘው ዅሉ ዛሬም አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚጥሱ ካህናትን ሊገሥፁና ሊያስተካክሏቸው ይገባል፡፡

በዔሊ ልጆች እኩይ ተግባርና ካህኑ ዔሊም ልጆቹን ተግቶ ባለመገሠፁ ልጆቹ በኢሎፍላውያን ጦር ወደቁ፤ እርሱም በታቦተ ጽዮን መማረክና በልጆቹ ሞት ደንግጦ ከወንበሩ ላይ ወድቆ ሞተ፡፡ የፊንሐስ ሚስት በድንጋጤ የወለደችውን ልጅ ‹ክብር ከእስራኤል ለቀቀ› ስትል ‹ኢካቦድ› ብላ ጠራችው፡፡ የእስራኤል ክብራቸው ሞገሳቸው የነበረችው ታቦተ ጽዮን ተማርካለችና፡፡ በዔሊ ልጆች ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ኃይልና ሞገስን ከጽዮን አነሣ፡፡ መፈራትንም ከኃያላኑ ገፈፈ፡፡ ለዚህም ነው የፊንሐስ ሚስት ልጇን ኢካቦድ በማለት የጠራችው፡፡ ታቦተ ጽዮን እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጥባት የትእዛዛቱ ጽላት፤ ሕዝበ እስራኤልን ከጠላት፣ ከአባር፣ ከቸነፈር፣ ከመቅሠፍት የሚያድንባት ማደሪያው ናት፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹እስመ ኀረያ እግዚአብሔር ለጽዮን ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፤ ማደሪያውም ትኾነው ዘንድ ወዶአታልና›› /መዝ. ፻፴፩፥፲፫/ በማለት የዘመረው ለጊዜው ስለ ታቦተ ጽዮን ነው፤ ፍጻሜው ግን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡

ታቦተ ጽዮን የእግዚአብሔር ትእዛዝ መቀመጫ እንደ ነበረች እመቤታችንም አማናዊትና ዘለዓለማዊት የእግዚአብሔር ማደሪያ ናትና፡፡ ‹‹ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለዓለም፤ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት›› እንዲል /መዝ. ፻፴፩፥፲፬/፡፡ ታቦተ ጽዮን በዔሊ ልጆች ኀጢአት ምክንያት ተማርካ ወደ ምድረ ፍልስጥኤም ተሰዳለች፤ እመቤታችንም በክፉው ሄሮድስ ከምድረ እስራኤል ወደ ግብጽ ተሰዳለች፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ታቦተ ጽዮን የምእመናን ምሳሌ ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ እንደ ኾነች ዅሉ፣ ምእመናንም የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ናቸውና፡፡ ‹‹ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ኾነ አታውቁምን?›› እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ /፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፱-፳/፡፡ በዔሊ ልጆች ኃጢአት ታቦተ ጽዮን እንደ ተማረከች ምእመናን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲወጡ የእግዚአብሔር ጸጋ ይለያቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮን በኢሎፍላውያን እንደ ተማረከች፣ ምእመናንም ራሳቸውን ለዲያብሎስ ምርኮ አሳልፈው ይሰጣሉና፡፡

ይቆየን፡፡