ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መድረስ እንደሚገባ ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ
የልደት ክርስቶስ በዓል የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነፃነትና የእኩልነት በዓል ሊሆን እንደሚገባ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ታኅሣሥ 26 ቀን 2008 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
ማንም ይሁን ማን፣ በየትኛውም ደረጃ ወይም አካባቢ ይኑር፣ ከሰላም ወጭ ጥቅሙን ማረጋገጥ የሚችል የለም፤ ሊኖርም አይችልም፤ በሰላም ውስጥ ሆኖ ግን ሁሉንም ማግኘት እንደሚቻል ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት አየታየው ውጤት ምስክር ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችንም ሆነ አገራችን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዋች በቀላሉ ማምለጥ የሚቻለው ከሁሉ በፊት ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ይዘው ሲጓዙ እንደሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ ገልፀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተመልሶ ሰውን ከሞት ያዳነው ማንንም ሳይጎዳ በሰላም ጎዳና ብቻ ተጉዞ ነው፡፡ ጥላቻና ራስ ወዳድነት ሲያፈርሱ ሲያጠፉ እንጅ ሲያለሙ እና ሲገነቡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ታይተውም፤ ተስምተውም፣ በታሪክ ሲደገፍም አይተን አናውቀም ብለዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በልማትና በዕድገት እየገሠገሰች ያለች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነገ ብሩህ ተስፋ ትሆናለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሀገር ነች፡፡ ይህ ተስፋ እግዚአብሔር ባርኮልን በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም ሳንለያይ መላ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን ያስገኘነው የልማት ፍሬ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡ የተገኘው የልማት ፍሬ እየበረከተና እየደለበ ወደፊት እንዲቀጥልና እንዲያድግ እንጂ በማናቸውም ምክንያት ወደ ኋላ እንዲመለስና ህዝባችን መፍቀድ እንደሌለበት አያይዘው አስገንዝበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መላው ህዝባችን በሚገባ ማጤን ያለበት ነገር ቢኖር ምንጊዜም የችግር መፍትሔ ሰላምና ልማት እንጅ ሌላ አማራጭ መፍትሔ የሌለ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም የአገራችን ህዝቦች የገናን የሰላም መዝሙር እየዘመሩ ለጋራ ዕድገትና ለእኩልነት፤ ለህዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ልማት በፅናት መቆም እንደሚገባ ገለጡ፡፡
በመጨረሻም በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት ለምግብ እጦት የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችን የወገንን እጅ በተስፋ እየጠበቁ ይገኛሉ፤ እነዚህ ወገኖች ግማሽ አካላችን መሆናቸውን ተገንዝበንና ጌታችን እኛን ለመፈለግ ወዳለበት የመጣበትን ፍቅር አብነት አድርገን፤ እኛም ወዳለበት በፍቅር በመሔድ በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና አለን ከጎናችሁ ልንላቸው ይገባናል፡፡ አነሰ ሳንል በወቅቱ ፈጥነን እጃችንን ልንዘርጋላቸውና በአጠገባቸው ሆነን ልናበረታታቸው ይገባል፤ እግዚአብሔር ሁላችንን እንደወደደን እኛም ወንድሞቻችንን በመመገብ፤ በማልበስና ችግራቸውን ሁሉ በመጋራት ለእግዚአብሔርና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ዛሬውኑ በተግባር እንድናሳይ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡